ምን አለበት ብሎ ነገር!

ለአዲስ ዓመት አዲስ አበባ የተገኙና ዘመኑ ደስ ያላቸው ሁሉ አዲሱን ዓመት በቴሌቪዥን በተላለፈ የሸራተኑ ርችትና የምሽት ፈንጠዚያ ተቀብለዋል። ለራሳቸው ወይም ለህዝቡ እንኳን አደረሳችሁ ለመንግሥት ደግሞ “እንኳን አተረፋችሁ!” ማለት የፈለጉ ሁሉ፣ በዓሉን እንደየ ስሜትና ፍላጎታቸው አክብረውታል። በዓልነቱ ሽቀላና ገቢ የሆናቸውም አሉ። የግድያና የአፈናውን ዘመን የሚቃወሙትንም “እንኳን ብግን ቅጥል አደረጋችሁ” ለማለት ብቻም የተገኙም ነበሩ።

ኢህአዴግ ቅንጅትን ሲከስ “ ህዝቡ እኛን ጠልቶ ነው እንጂ እናንተን ወዶ አይመስለችሁ!” ማለቱ የምርጫ ሰሞን መነጋገሪያ ነበር። ሕዝብ ይጠላኛል የሚል መንግሥት ለምን ሥልጣን ላይ መቆየት እንደሚፈልግ ግልጽ ባይሆንም፣ ተሳስተሃል “እኛ ሕይወታችንን እስከ መስጠት እንወድሃለን” የሚሉ ወገኖች መኖራቸውን እያየን ነው። ለወያኔ ያላቸው ፍቅር ሳይሆን ለተቃዋሚዎች ያላቸው ጥላቻ የበለጠባቸውንም አይተናል። ከሙዚቃው ስልት በላይ የሚዘሉ ወይም የእንግሊዝኛው ሙዚቃ ትግርኛ እስኪያስደንሳቸው ድረስ ወያኔን “እንወድሃለን” ለማለት የሚዳዳቸው ስዎች መኖራቸውን ከማስተዋል ጋር ነው አዲሱን ዓመት የተቀበልነው። የትግራይ ህዝብ ግን ወያኔን ያፋጠጠበት እንጂ አብሮ የጨፈረበትን ዘመን አናስታውስም።

በአንጻራዊ መልኩ መንግሥት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ገጽታ ነበረው በተባለበት ጊዜ፣ መንግሥትን ሲወቅስና ሲረግም የኖረ ሰው ወይም ጋዜጣ ፣ መንግሥት ጨርቁን ጥሎ ለይቶለት ፣ዓይን አውጥቶ ሲገድልና ሲያስር፣ ሲያፍንና ሲያባርር ዴሞክራሲያዊነቱን የሚመስክር ከሆነ ምስክርነቱ በአሽቃባጭነት ብቻ የሚመዘገብ ተራ ክህደት አይደለም። አባቶች ወደ ጠበል ምሁራን ወደ ሳያካትሪስት ወስደው የሚያሳክሙት በሽታ ነው። አንዳንዶች በርግጥ ታመዋል!

ወያኔ መሆን ለወያኔዎች የሚያሳፍር ነገር አይደለም። እነ አቶ መለስ፣ እነ አቶ ስዩም መስፍን በወያኔነታቸው አያፍሩም። አቶ አዲሱ ለገሠ (አንዳንዶች ም/ጠቅላይ ምኒስትር ይሏቸዋል) ይሰነዘርባቸው የነበረውን ስድብ ሁሉ እንደ አዝማሪ ግጥም ቆመው ይኮመኩሙት የነበረው ከወያኔ ስለሆኑ ነው። ወያኔዎች አያፍሩም። መግደል ካለባቸው ይገድላሉ። መስረቅ ካለባቸው ይሰርቃሉ። ደሞክራሲያዊ መሆን ሲፈልጉ ንግሩን ስደቡን ይላሉ። አምባገነን ሲሆኑ ደግሞ ሹክሹክታም ይደብራቸዋል። እንደፈለጉ ነው። ትልቅ አገር ለማስገንጠል ይዋጋሉ። ሌላ ጊዜ ደግሞ ባድመን ለምታክል ቦታ ሉዓላዊነታችን ብለው ይዋጋሉ። አገር ይክዳሉ። በአገር ክህደት ይከሳሉ። ጠባብ ይሆናሉ። ጠባቦች ብለው ይሳደባሉ። ቀይ ሽብር ይላሉ። ቀለም የሌለው ሽብር ያካሂዳሉ…እና ወያኔዎች አቋማቸው ተገለባባጭ ይሁን እንጂ እብደታቸው ቋሚና ግልጽ ነው። ግልጽ ያልሆነውስ ከኛ መካከል ድንገት ብደግ ብለው ያንን የእብደት መንደር ሲቀላቀሉ የምናያቸው የወንድሞቻችን ነገር ነው።

ስዎችና ሹማምንቶች የወያኔን የእብደት አዳራሽ እየለቁቁ አገር እየጣሉ ሲሸሹ፣ ባላቀ ስዓት እነሱን ለመቀላቀል፣ በተቀቃራኒው ወደ ወያኔ የሚሮጡት ደግሞ ይገርማሉ። የስዎቹ ሩጫ አስገራሚ የሚሆነው ያልተጠበቀ ስለሆነ አይደለም። ግን የሯጩ ቁጥር እየበዛ ከሄደ እብደትም እየበዛ ይመጣና ባህላችን ይጠፋል። ገዢው ህሊናችን ይረክሳል። መንፈሳዊው ጥንካሬያችን ዘላቂ በመሰለን ጊዚያዊ ጥቅማ ጥቅም ይሸራሸራል። ከዘቅጥነው በላይ መዝቀጥ ይመጣል። “ስው ቢገደል ምናለበት -እኛ የለንበትም ፤”…፣ “ጋዜጠኛ ቢታሰር ምናለበት- እኛ አርቲስቶች ነን፤ ” “ፖለቲከኞች በአደባባይ ቢረሸኑ ምን አገባን እኛ ሐኪሞች ነን’ “አገር ቢፈርስስ ታዲያ ምን አለበት እኛኮ መኖሪያ ቤት እየሰራን ነው… ስው ቢደኸይ፣ ቢያጣ ቢነጣ፣ ለማኝ ቢበዛ ምን አለበት -አዳዲሶቹ ፎቆችኮ ያማምራሉ…ህዝቡ የአውቶብስ መክፈያ አጣ፣ ነዳጅ ሰማይ ወጣ፣ ብለው ለምን ያማርራሉ? ለምን የተሰሩትን መንገዶች አይመለከቱም…ህዝቡ በፍርሃት አፉን እንዲይዝ ቢታፈን ታዲያ ምን ይጠበስ? አገር እንደሆነ ሰላም ነው…
ምንም ነገር ማስተዋል ለማይፈልጉት ምንም ነገር አይታያቸውም። ስለዚህ እዚያ ሰላም ነው ምንም ነገር የለም፣ ወሬና ሽብር ሁሉ ያለው ውጭ አገር ነው ይላሉ። ቃሊቲ ከሸራተን ምን ያህል ማይል እንደሚርቅ በእርገጠኝነት ለመናገር ያቅት ይሆናል። ቃሊቲ እስር ቤት ግን ዋሽንግተን ሳይሆን አዲስ አበባ ውስጥ መሆኑን ማን አባቱ ይክዳል?

አንዳንዶች “ሆዳም ከርሳም!” ብለው የሚሳደቡት ይህን ዓይነቱን አነጻጻሪ ለማለት ፈልገው ይሆናል። ግን እሱም ዓይነቱ ስድብ ማንንም የትም አያደርስም። ማንንም ከየትም አይመልስም። እንዲያውም እልህ ውስጥ እየከተተ ስውንም አገሩንም ወደባሰ ማጥ ውስጥ ይከታል። ወያኔን ሲታገሉ ኖረው በመውደቂያው ስዓት አብረው ለመውድቅ “መብታችን ነው ምናለበት እያሉ?” ወደሱ የሚሮጡት ስዎች ሞራል ግን አጠራጣሪ ነው። ስጋቱ የሚመነጨውም ወያኔን የመደገፍ መብታቸውን ካለማክበር አይደለም። “ ይሄ ምን አለበት?” የሚባለው ቫይረስ የመስፋፋቱ ነገር አሳሳቢ ስለሆነ ነው። ቀስ በቀስ ሥር እየሰደደ የመጣ ይመስላል። “የትም አይደርስም!” ብለው የሚጽናኑ ሊኖሩ ይችላሉ። ቫይረሱ ግን ውሎ ሲያድር እንደ ኤድስ መድኃኒት የማይገኝለት ይሆንና ችግር እንዳይፈጥር ያሰጋል። በዚያ ላይ ደግሞ ወንድሞቻችን አንዳንድ ነገር እየጣፈጣቸው ይመስላል። ጎበዝ የኤድስ ምንጩኮ የሚጣፍጥ ነገር ነው። (ዘኢትዮጵያ)