ልዩ ዘገባ

ኢኮኖሚው አማርኛ መናገር ጀምሯል!

ባለግሮሰሪዎች፣ የሬስቶራንት ባለቤቶች፣ ባለታክሲዎችና
የመሳሰሉት ምን ብለዋል?
ልዩ ዘገባ በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ

ቨርጂኒያ ስካይላይን በሚገኝ ሥጋና ምግብ ቤት ውስጥ ሥጋ ቆራጭ የሆነው ደበበ ደሳለኝ ከኢትዮጵያ በዲቪ ከመጣ ገና 8 ወሩ ነው። እሱን የሚገርመው ወደ አሜሪካ የመጣበት አጋጣሚ ኢኮሚኖሚው በወደቀበት ጊዜ መሆኑ ብቻ አይደለም። ኢኮኖሚውም ደህና ቢሆን ስለ አሜሪካ በትክክል ያልተነገሩት ብዙ ነገሮች ያሉ መሆኑን ለዘኢትዮጵያ ተናግሯል።

“ለምሳሌ እኔ ስመጣ ይህን ሁሉ አልሰማሁም። ” ያለው ደበበ “እዚህ አሜሪካ ሁሉነገር አልጋ ባልጋ መሆኑ ነበር የተነገረኝ አሁን አየሁት። ለካ አልጋውን የምትዘረጋው ራስህ ነህ! ቤት ይሰጣኻል፣ ት/ቤት ትገባለህ ተብዬ ነበር። መንግሥት ብድር ይሰጣኻል፣ መንገዱን ያመቻቻሃል ብለው ነበር የነገሩኝ። የጠበቀኝ ግን ሌላ ነው። ለመማር መስራት አለብህ። ከሥራህ ደግሞ በማናቸውም ሰዓት ድንገት ልትባረር ትችላለህ። እና እኔንም የውጭ አገር ሰዎች የሆኑ ቀጣሪዮቼ ባንድ ወር አባረሩኝ! ሥራ ፍለጋ ብዙ ተጎሳቅያለሁ። በኋላ ላይ ጤና አዳም አስጠጋችኝ። የተወሰነ ጊዜ ሰራኹ። ቀለብም ሰፈረችልኝ። ከዚያ መኖሪያ ቤት ፍለጋ ቀጠልኩኝ። በ250 ብር ደባልነት አገኘኹ። አንዲት ክፍል ለሁለት ገብቼ መኖር ጀመርኩኝ ። መውጫ መግቢያውን እስካውቅ እንደዚያ ቆየሁ። አሁን እግዚአብሔር ይመስገን ዳኙ ይቺን ሥራ ሠጥቶኛል። ኢኮኖሚው ግን ይኸው እንደምታየው ወደቀ እያሉ ነው።”

ደበበ የኢኮኖሚው ነገር ያሳሰበው መሆኑ ያስታውቃል። ደበበ ኢኮኖሚውን የሚከታተለው በቴሌቪዝን አንብቦ ሳይሆን በሚቆርጠው ሥጋ ልክ ነው። እሱ ወደሚሰራበት የኢትዮጵያውያን የገበያ መደብር የሚመጡት ኢትዮጵያውያን ሥጋ ሸማቾችም ጥሩ መመዘኛዎቹ ናቸው። “ “ቁጥራቸው እየቀነሰ ነው። ወደ ገበያው የሚመጡበትም እንደ ቀድሞ በተለያዩ ቀናት ሳይሆን በሳምንት አንድ ቀን ብቻ እየሆነ ነው።

ደበበ ከሚሰራበት አካባቢ እልፍ ብሎ፣ እዚያው ቨርጂኒያ ስካይላይን የገበያ ማእከል ውስጥ ከሚገኘው፣ ሌላኛው የጤና አዳም ገበያም ያለው ችግር ተመሳሳይ መሆኑም ይህንኑ የሚያጠናክር ይመስላል። የግሮሰሪ ገበያው ባለቤት ወ/ሮ ጤና አዳም ይልማ እዚያ ቦታ ላይ ቢዝነስ መስራት ከጀመሩ 5 ዓመት ሆኗቸዋል። እንደዚህ ያለ ነገር አይተው አያውቁም። “ሽያጫችን በግማሽ ወርዷል። ያውም ይህ የበዓል ሰሞን ሆኖ ነው። ሰው የፈራ ይመስለኛል።” በማለት በታንክስ ጊቪንግ እና በገና በዓላት ሰሞን የታዩትን ቀዝቃዛ ለውጦች ገልጸዋል። እንደሳቸው አገላለጽ ሰው በፊት ያደርገው እንደነበረው እንደልቡ መግዛት አቁሟል። ለምሳሌ እንጀራ አንድ ቀን ከገዙ ሳምንቱን ሙሉ አይገዙም።

የደበበም አገላለጽ ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት አለው። “ድሮ ዓርብ ቅዳሜና እሁድ ብዙ ሥራ ነበረን። አሁን ግን እሁድ ብቻ እየሆነ ነው” በማለት ከፕሬዚዳንታዊው ምርጫ በፊትና በኋላ እንኳ ትልቅ ለውጥ ማየቱን ገልጿል። ወ/ሮ ጤና አዳምም “ባለፉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ እየታየ ነው”ብለዋል። ለዚህ ምክንያት ይሆናል ብለው የገመቱት ብዙ ኢትዮጵያውያን ከሥራ እየተቀነሱ ነው። ብዙዎች ሞርጌጅ ችግር ሆኖባቸው ቤቶቻቸውን ለቀው እስከመውጣት እየደረሱ ነው። ያሉትም እየታገሉ ነው። ” በሚል በስፋት እየተነገረ ያለውንና ሌሎችም እንደሳቸው ያቀረቡልንን ምክንያትና ግምት ነው። ከሥራ የተቀነሰው አቅም ሲያጣ፣ ሥራ ላይ ያለውም እባረር ይሆን እንዴ ብሎ መስጋቱ አልቀረም። አቶ ደበበም “ስጋትማ መች ይቀራል ፣ታዲያ ገበያ ከሌለ ባለቤቱ ከየት አምጥቶ ሊያሠራኝና ሊከፍለኝ ይችላል?” በማለት ጭንቅ የገባው መሆኑን መግለጹ ለዚህ ይመስላል።

የዛሬዪቱ አሜሪካ እንደ ደበበ ላለውና ገና ከመጣ ዓመት እንኳ ላልሞላመው ሰው ቀርቶ፣ 30 ዓመት ሊሞላቸው ለተቃረቡት በርካታ ኢትዮጵያውያን ሳይቀር ለውጡና አስቸጋሪነቱ እየታየ መሆኑ በኮሙዩኒቲው ዘንድ እየተነገረ ነው። ለምሳሌ የዳማ ኬክ ቤትና ሬስቶራንት ባለቤቶችና ሥራ አስኪያጅ ከሆኑት አንዱ አቶ ኃይሉ ዳማ አሜሪካን አገር ከመጡ ወደ 28 ዓመት አልፏቸዋል። እነ ደበበ ገና የሚያሳልፉትን ሁሉ እሳቸው ድሮ አሳልፈው እዚህ ደረጃ ቢደርሱም ደረጃው ይለያይ እንጂ በቀውሱ ማእበል ከመመታት የዳኑ አይመስልም። 10 ዓመት ከቆየው ቢዝነሳቸው ላይ በቀላሉ ከ20 እስከ 30 ከመቶ የሚደርስ ቅናሽ ሊታይ መቻሉን ገልጸው “ይህ በቢዝነስ ዓለም ትልቅ ጉዳት ነው” ብለዋል። ይህ መሆኑ ብቻ ሳይሆን “ይህ ጅምር ሲሆን ወደፊት ምን ሊከተል እንደሚችል አይታወቅም። መፍትሄው በትክክል ይህ ነው ብሎ 99 ከመቶ እርግጠኛ ሆኖ ያስረዳንም ኢኮኖሚስት የለም። እና ይህ ነገር የት እንደሚቆምና እስከመቼ እንደሚቀጥል አይታወቅም። አዲሱ ፕሬዚዳንት ኦባማ ጥርት ያለ ፖሊሲ ይዘው መጥተዋል ቢባል ወይም ሊመጡ ይችላሉ እንኳ ቢባል ቢያንስ አንድ ዓመት ተኩል መውሰዱ አይቀርም፤ ይሄ ያጭር ጊዜ ችግር አይመስለኝም” ብለዋል።

የዛሬይቷ አሜሪካ “ኢትዮጵያውያን ዛሬ እንደድሮ ሻንጣችንን አዘጋጅተን ከዛሬ ነገር አገራችን እንገባለን እያልን የምንኖርባት አገር አይደለችም” ያሉት አቶ ኃይሉ፣ “ዛሬ ልክ እንደአገራችን ሙሉ ልባችንን አሳርፈን እግራችንን ተክለን የምንኖርበት አገር ሆኗል። እንደ እንግዳ ሳይሆን ኑሯችንን ገንብተን ቤታችንን ሠርተን ልጆችና የልጅ ልጆች አፍርተርን የምንኖርበት አገር ሆኗል። (ሀበሻው ሜይን ስትሪም ውስጥ ገብቷል። ) ሰለዚህ በአሜሪካ የሚሆነው ነገር ሁሉ ይነካናል። የልጃችን የኮሌጅ ትምህርት ቤት ማሰብ አለ። እንደማንኛውም አሜሪካዊ ከሥራ እንባረራለን። ድሮ ከሥራ የተባረረ ሀበሻ ማየት ከባድ ነበር። ድሮ ከኢትዮጵያ የመጣ ሰው ሥራ ማስቀጠር በጣም ቀላል ነበር። በሰው በሰው ሥራ ይገኛል። ሰዎች ከኢትዮጵያ በመጡ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ሥራ ማስያዝ ቀላል ነበር። አሁን ወር ሁለት ወር ውስጥ አይገኝም። ያሉትንም ማበረር ይዘዋል። ይህ የነበርነውንም አዲስ የሚመጡትንም ይነካል።” በማለት ትሥሥሩን ገልጸዋል።

መቆየትና አዲስ መጪ መሆን ከችግሩ የማያድን መሆኑን የገለጹት አቶ ኃይሉ እንዲያውም የቆዩት ኢትዮጵያውያን ላይ ችግሩ የበረታ መሆኑን ለመጥቀስ የቤትና የሞርጌጅ ሁኔታን አንስተዋል። “ እስኪ ይታይህ ለጡረታ የቀረበ ሰው ትልቁ ሀብቱና ኢንቭስትመንቱ ቤቱ ነው። ቤቱ ቅርሱ ነው። አንድ ነገር ቢመጣ ቤቴን ሸጬ እሄዳለሁ ይላል። ምክንያቱም ለብዙ ዓመታት እዚያ ቤት ላይ ሲከፍልና ተስፋ ሲያደርግ ኖሯል። የቤት ዋጋም በአዲስ ገዢዎችና በነባሮቹ መካከል ትልቅ የዋጋ ልዩነት ፈጥሮ ስለነበር አንዳንዱ ብዙም እያወጣበት ሲኖር አንዳንዱ ደግሞ ጥሪቱን (ኤኩቲውን) 100ሺም እስከ 200ሺም ቢሆን ከላዩ ላይ ሲያነሳለት ኖሯል። አሁን ግን ነገሩ ሁሉ ሌላ ሆነ ተባለ። ለምሳሌ እኔ አንድ ጎረቤቴን አውቃለሁ። ለቤቱ 710ሺ ብር ተሰጥቶት ነበር። አሁን ልሽጠው ሲል 500 ሺውንም በስንት መከራ ነው ያገኘው። 200ሺ ብር አጥቷል ማለት ነው። እዚህ ላይ ስታይ በወረቀት ላይ ብቻ የጠፋ ነገር ብቻ ሊታይህ ይችላል ግን የሚያደርሰው ስነልቦና ጫና ከፍተኛ ነው። መጦሪያዬ ነው ብሎ ቤቱን ተማምኖ የኖረ ሰው በእንዲህ ያለ ጊዜ ምንድነው የሚያደርገው? ያለው ምርጫ ወደፊት ደግሞ ምን ሊመጣ ይችላል በሚል በእጁ ያለውን ነገር ብቻ መያዝ ነው።
አቶ ኃይሉ ዳማ እንዳሉትም በአካባቢው የሚገኙ ቢዝነስ ድርጅቶች ደንበኛ የሆኑት ኢትዮጵያውያን ስለመጪው እርግጠኝ ስላልሆኑ በወጪዎቻቸው ላይ የተቆጠቡ መስለዋል። ዘኢትዮጵያ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው የተለያዩ የቢዝነስ ድርጅቶችም ይህንኑ አጠናክረዋል። ኢትዮጵያውያን ከወጪ የተቆጠቡት በበርካታ ዘርፎች በመሆኑ የቢዝነስ ድርጅቶችና አገልግሎት ሰጪዎች እየተነኩ ነው። ለምሳሌ ከአካባቢው ካሉት ጥቂት ታዋቂ ፎቶግራፈሮች መካከል አንዱ የሚባለው አቶ ደረጀ ዘውዴ ላለፉት 16 ዓመታት “ዲጄ ፎቶግራፊ” በሚል አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። በተለይ በዋነኛነት ከያዛቸው ሥራዎቹ ውስጥ አንዱ የሠርግ ዝግጅቶች ናቸው። “በዋሽንግተን ሜሪላንድና ቨርጂኒያ አካባቢዎች ባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ፣ በኢኮኖሚው ችግር ምክንያት የደረሰ፣ የጋብቻ ፕሮግራም ለውጥ፣ ወይም የተጋቢዎች ቁጥር መቀነስ የታየ ይመስልሃል?” የሚል ጥያቄ ከዘኢትዮጵያ ቀርቦለት ነበር። “እኔ መቸም ኢኮኖሚውን የማየው በአይኔ ሳይሆን በካሜራ ነው!” ከሚል ቀልድ ጋር ለውጡ አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል። “አየህ ሰው መጋባቱን ይጋባል። ይህን መቸም የሚያቆም አይመስለኝም። ለምሳሌ አሁን ያለንበት ወር ጃንዋሪ ነው። በዚህ ወር ድሮ ከ10 እስከ 12 የሚደርሱ የሠርግ ኮንትራቶች ይኖሩኝ ነበር። አሁን ያሉኝ አምስት ብቻ ናቸው ይህ በጣም አሳሳቢ ይመስለኛል” ብሏል። የዚህ ምክንያቱ ኢኮኖሚው መሆኑ ግልጽ ቢሆንም ሰዎች እንደ ቀለበት ባሉ መጠነኛ ድግሶች ወይም ወደ አነስተኛ ወጪዎች ዝቅ ብለው እንደሆን ወይም በሌላ ምክንያት ባይታወቅም ለውጥ መኖሩ ግን ግልጽ መሆኑን ገልጿል።

አቶ ደረጀ ዘውዴ በዚህ የፎቶግራፍ ሥራ ብቻ ሳይሆን ከሌሎቹ ጋር በመሆን ሐበሻ ምግብ ቤት በሚል በዋሽንግተን ዲሲ ዘጠነኛው መንገድ ላይ ያለውን የቢዝነስ ድርጅት ይመራል። ይህም በመሆኑ ጭምር ይመስላል ደረጀ ኢኮኖሚውንና ኢትዮጵያውያንን የሚያየው ከተፈጠረው ቀውስ ጋር ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል በታክሲ አሽከርካሪዎች ላይ ከተደረገው የአሠራር ለውጥ ጋር አያይዞ ነው። “ በታክሲ አሽከርካሪዎች ላይ በተደረገው የዋጋ ለውጥ ኢትዮጵያውያኑ ሲያማርሩ ነበር። እንደገና ደግሞ አሁን ኢኮኖሚው ተጨመረና የባሰ መጣ። እኛ 80 ከመቶ የሚሆኑት ደንበኞቻችን ባለታክሲዎች ናቸው። እነሱ በተነኩ ቁጥር ደግሞ የኛም ገበያ መነካቱ አይቀርም።” ብሏል።

ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ብቻ ወደ 7ሺ የሚሆኑ የታክሲ አሽከርካሪዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል 4ሺ 500 የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነውና ስሙ እንዲገለጽ ያልፈለገው የግራንድ ካብ ካምፓኒ ባለታክሲ ይህንኑ አጠናክሯል። እኔ በዋሽንግተን ዲሲ ላለፉት 10 ዓመታት ታክሲ አገልግሎት ስሰጥ ቆይቻለሁ፣ እንደዚህ ያለ ነገር አጋጥሞኝ አያውቅም። እኛ የተመታነው ታክሲ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱ (ሲስተሙ) ሲለውጥ ነው። የዞንና የሜትር ለውጡ ሲደረግ ድሮ እናገኝ ከነበረው ገቢ 30 እና 40 ከመቶ የሚሆነው ቀንሶብናል። በዚያ ላይ አሁን በተፈጠረው ቀውስ ደንበኛ የማግኘት እድላችን ቀንሷል። ለምሳሌ ድሮ ከ15 እስከ 25 ደቂቃ ባለ ጊዜ ውስጥ አንድ ሰው እናነሳለን። አሁን 30 እና 45 ደቂቃ እንኳ ቆይተን ስው የማናገኝበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው።” ብሏል።

“በሥራዬ የተነሳ አሜሪካውያኑ ትክክለኛ ሪሰሼን ላይ የገቡ መሆኑን እያየሁ ነው ማለት እችላለሁ” በማለት፣ በሰሞኑ ዓመት በዓል ያየውን በምሳሌነት አንስቷል። “ለምሳሌ ሌላውን ሁሉ ትተህ የዘንድሮውን አዲስ ዓመት ዋዜማ (ኢቭ) ብታይ ይገርምሃል። በዚያ ቀን ቢያንስ ደህና ሰው እናገኛለን የሚል ተስፋ ነበረን። ግን አዲስ ዓመት መሆኑ ቀርቶ ትንሽ ሞቅ ካለች አንድ አርብ ምሽት ያነሰ ቀን መስሎ ነው ያለፈው። ድሮ እስከ ንጋቱ 5 ሰዓት ሳይቀር ሰው መንገድ ላይ እያለፍን ነበር የምንሄደው፣ ዛሬ ሰዎቹ ገና በጊዜ ወደየቤታቸው ትተውን ይሄዳሉ።”

በተለይ ዋሽግንተን አካባቢ የሚገኙ ሬስቶራንቶችና የኢትዮጵያውያን ቢዝነስ ተቋማት ምሶሶ መሆናቸው የሚነግርላቸው ባለታክሲዎች ኢኮኖሚው ገቢያቸውን ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ህይወታቸውንም እየነካ መሆኑን እንዲህ በማለት ገልጿል “እኛ በሥራ መካከል ማታ ላይ አንድ ሬስቶራንት ተገኛተን የምንጨዋወትበት፣ ራት በልተን ቡና ጠጥተን የምንገባበዝበት የእረፍት ሰዓት ነበረን፣ አሁን ትተነዋል። ምክንያቱም ወጪውንም ሰዓቱንም ማባከን አንችልም። እንደዚሁም ዕሁድ ዕሁድ የምንጥለው እቁብ ነበረን አሁን ሁሉም ዕቁብ የተዘጋ ይመስለኛል።”

ይህ የሆነበት ምናልባት ገንዘቡ ስለጠፋም ብቻ ሳይሆን ካሹን መጠቀም ስላልተፈለገም ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየት የሰጡንም አሉ። ኢትዮጵያውያን የገንዘብ አወጣጣቸው ብቻ ሳይሆን አጠቃቀማቸው ራሱ ተቀይሯል። ከኢኮኖሚው ቀውስ ወዲህ አብዛኛዎቹ ካሽ ሳይሆን ክሬዲት መጠቀም መጀመራቸውንም አረጋግጠናል። ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈልጉ አንድ የሬስቶራንት ሥራ አስኪያጅ “ደንበኞቻችን 90 ከመቶ ያህል ካሽ ሳይሆን ክሬዲት ካርድ መጠቀም ጀምረዋል።” ብለውናል። የግሮሰሪ ባለቤቶችም ይህን አረጋግጠውልናል። ካሽ ያለማውጣቱ ነገር በጥቃቅን ግዢዎችም ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አልቀረም። ለምሳሌ አሁን 15 እና 20 እንጀራ ድረስ ሳይሸጥ የሚያድርበት ጊዜ አለ። አምባሻው ሳምቡሳው ሁሉ ማደር ጀምሯል።

እንጎቻ የሚያካክሉ 10 እንጀራዎችን የያዘው አንድ ጥቅል ከ4.50 እስከ ከ4.75 ለባለሱቆቹ ይደርሳል። እነሱ እስከ 6ብር ይሸጡታል። “ሀበሻ እንኳ በእንጀራ አይጨክንም ይህ የሆነው በሌላ ምክንያት ነው” የሚል ሌላ ምክንያት የነገሩንም አሉ። እንደነሱ አባባል እንጀራ የሚያድረው የእንጀራዎቹ ዓይነት ከ10 በላይ በመድረሳቸው ምክንያት ከመጣ ፉክክርም ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ዛሬ ሰቨን ኢሊቨን ውስጥ ሳይቀር እንጀራን በየአካባቢው መሸጥና ማከፋፈል ስለተጀመረ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያውያን ግሮሰሪዎች እንደድሮ መምጣታቸውን ቀንሰዋል ብለው ስጋታቸውን የገለጡልንም አጋጥመውናል።

“እኔ የምሠራው ቨርጂኒያ ውስጥ ነው።” ያለን አቶ ብርሃን አወል በቨርጀኒያ ታክሲ አሽከርካሪዎችም ላይ ተመሣሳይ ችግር መኖሩን ገልጿል። “ አሁን እንደድሮ መንገደኛ አታገኝም። ሰው እስከተወሰነ ድረስ ይነዳና ከዚያ ሜትሮ መጠቀም ጀምሯል። ፓርኪንግ 15 ብር ላለመክፈል በ6ብር ሜትሮ ከፍሎ ይሄዳል። ድሮ ከደንበኞቻችን ውስጥ በስም የምናውቃቸው እንኳ ነበሩ። አሁን እነሱ የሉም። በፊት እስከ ዳላስ ኤርፖርት ድረስ ታክሲ ይዘው የሚሄዱ ነበሩ። ቶሎ ቶሎ ጥሪ ነበረን። አሁን አንድ ሰዓት እንደዚህ ቆይተን ነው ጥሪ የምናገኘው።” በማለት ለውጡን አስረድቷል። ስሙን ያልገለጸ ሌላ ባለታክሲም እንዲሁ “ ቨርጂኒያ ውስጥ ብቻ ድሮ 5 ኤም ወጥተን ለግማሽ ቀን ማለትም እስከ እኩሉ ቀን 12 ሠዓት ድረስ ብንሠራ ቢያንስ በትንሹ 200 ዶላር እንሰራ ነበር። አሁን ያንን ለማግኘት ቀኑን ሙሉ መሥራት ይኖርብናል።” ብሎናል።

ከታክሲ ሌላ ቨርጂኒያው ውስጥ የሚገኘውን ኤንሪኮ የሚባለውን ኬክና ቁርስ ቤት ከከፈትኩ አራት ወራት ሞልተውኛል የሚለው ብርሃን አወል “አላስተዋልነውም እንጂ ኢኮኖሚው ላይ ፍርሃት መለቀቅ የተጀመረው ከ2007 ጀምሮ ነው” ብሏል። “ይሁን እንጂ አሁን እኔን ብትመለከት እስካሁን በአኗኗሬ ላይ ምንም የተለወጠ ነገር የለም።” አንዳንዶቹንም ሲመለከት ተመሳሳይ ነገር እንደሚታየው ገልጿል። ከኢኮኖሚው ጋር በተያያዘ ብዙ የባህርይ ለውጦችን ማድረግ ያለብን መሆኑን አስታውቋል። ያለ እቅድ ማውጣት፣ የግድ አስፈላጊ ያልሆነን ነገር በፉክክር መግዛትና ለ እዳ መዳረግም በራስ ኃላፊነት ጭምር የሚመጡ ችግሮች መሆናቸውን አስረድቷል።

የሲልቨር ስፕሪንግ ሜሪላንዱ አቡሽ ሳሙኤል ቀን ቀን እየሠራ ማታ ትምህርት ቤት የሚሄድ የ27 ዓመት ወጣት ነው። እኔና ጓደኞቼ የምናምነው እንደዚህ ነው ብሏል” ሪሴሽን ወይም የኢኮኖሚ ቀውሱ ገና ሀበሻውጋ አልደረሰም፣ ሀበሻ ሪሴሽን መኖሮኑም የሰማ አይመስለኝም። አሁንም ጥሬ ሥጋ የሚቆርጡ ውድ መኪኖቹን የሚነዱ አሉ። አሁንም ቤትና መኪናን በፉክክር የሚገዙ ጓደኞች አሉኝ። ፕሮፌሽናል ሥራና ትምህርት ከሌለህ ከሥራ የተባረረክ ቀን አስቸጋሪ ነው። ከተማርክ ጭንቅላትህን እንደያዝከው ትቆያለህ ገንዘብህ ማለት ነው። ካለበለዚያ ጠንካራና ታታሪ ሠራተኛ መሆን አለብህ። ታክሲም ነድተው ፓርኪንግም ቆመው ራሳቸውን ያሻሻሉ የተሳካላቸው አሉ። ምኑንም ሳያደርጉ እንዲሁ እንደዘለሉ የተባረሩም ለቀው የወጡም አሉ።

አቡሽ “እኛ ወጣቶቹ ራሳችን ቀውስ ውስጥ ከገባን ቆይተናል። ሌላ ሪሴሽን አያስፈልገንም ቢመጣም አይገባንም” የሚል እምነት ያለው መሆኑን ደጋግሞ ይገልጻል። እንደሱ አባባል ውስጣችን ካልተስተካከለ የውጪው ኢኮኖሚ ብቻውን ለውጥ አያመጣም። ከራሴ ጓደኞች ታሪክና ከማየው የታዘብኩትን የሚለው አስተያየቱን ሲገልጽ እንደዚህ ብሏል። ” ወንዶቹ ፓርኪግን ላይ ሴቶቹ ሞል ውስጥ ከሠሩ ደህና ኑሮ እንደሚኖራቸው ይገመታል። ሴቶችን ለማባባልና እነሱ ዘንድ ለመደነቅ ወንዶቹ በሌላቸው ገንዘብ ውድ መኪና ይገዛሉ። አንዳንዶቹ እንዲያውም እየገዙ ይሰጣሉ። አንዳንድ ገንዘብ በሴቷ እጅ ቢወጣም ገንዘቡ የወንድየው ነው ማለት ትችላለህ። ያለ አማቅማቸው ቤት እንዲገዛ የሚገፋፉ ሴቶች አሉ። ገና ሳይዘጋጁ ትዳር ውስጥ የሚወድቁም ብዙ ናቸው። በተለይ ሴቶቹ እድሜ ሳይገፋ ማግባት ይፈልጋሉ። “አንተ ምን ችግረህ ወንድነህ፣ እኔ ግን አልችልም፣” በማለት ፍቅርና ትውውቅ ኖረም አልኖረም ዘለው ይጋባሉ። ስለዘላቂ ግንኙነታቸው አያስቡም። ከዚያ በኋላ በፉክክር ቤትና መኪና መግዛት ይመጣል። ቀልጦ መቅረት ይከተላል። ሪሴሽኑ ብቻ ሳይሆን የአኗኗር ጠባያችንም ችግር እያመጣ ነው። እንዲህም ሆኖ የሚጎዳው ወንዱ ነው። ክሬዲትካርድ እንኳ ብትመለከት ከሴትዋ ይልቅ የወንዱ በጣም የተበላሸ ነው። እኔ አሜሪካ አገር የሴት እብድ አይቼ አላውቅም የሚያብደው ሁሉ፣ ወንዱ ነው፤ ለምን ይመስልሃል?” ካለ በኋላ “ ያበደች ሀበሻ ሴት አይተህ ታውቃለህ?”

እንዲህ ያለው ጣጣ ውስጥ ሳይገቡ ጥርሳቸውን ነክሰው ኑሮን የገጠሙና ከዚያም አልፈው ለቤተሰቦቻቸው ወደ አገር ቤት ገንዘብ መላክ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችና ታታሪ ሠራተኞችም አሉ። ለምሳሌ የሉካንዳ ቤቱ ባለሟል ደበበ ሥጋ ቆርጦ ከሚያገኘው ገንዘብ የተወሰነውን ቆርጦ ወደ አገሩ ይልካል።

እኔ ወደ ኢትዮጵያ እንደምልከው ገንዘብ ሰው ከላከ ጥሩ ነው። እስካሁን ለቤተሰቦቼ በኢትዮጵያ አንድ ሶስት ሺ የኢትዮጵያ ብር ልኬያለሁ። ለእህቴ ልጆችና አለአባቴ አንድ 1ሺ400 የኢትዮጵያ ብር፣ እንዲመርቁኝ ብዬ ደግሞ ለአካባቢው ሰው 250 የኢትዮጵያ ብር ልኬያለሁ። ባልሠራና ባላጠራቅም ኖሮ እዚህ ባለ ኑሮ ውድነት ይህ አይቻልም። ግን እዚያ ያለው ሰው ደግሞ ከኔ የባሰ ተቸግሯል ብዬ አስባለሁ። ወደፊት ግን ይህን እንዴት እንደምቀጥል አላውቅም ብሏል። ደበበ ይህን የያደረገው ገና በመጣ 5 እና 6 ወር ጊዜ ውስጥ ነው። በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ መላክ በብዙዎች ዘንድ የተለመደና እያደር የሚዘነጋ ቢሆንም ቋሚነት ባይኖረውም በርካታ ሰዎች ገንዘብ እንደሚልኩ ይታወቃል።

በሰውም ሆነ እንደ ዌስተርን ዩኒየን፣ ኢ.ኤም.ቲና መኒ ግራም፣ በመሳሰሉ የገንዘብ ላኪ ተቋምት አማካይነት በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ገንዘብ ይልካሉ። ይህ እያቃሰተ ያለውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ በመደጎም ረገድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቢሆንም እሱም እየተመናመነ መሆኑ እየተሰማ ነው። መንስኤው በዓለም በተለይም በአሜሪካ የመጣው የኢኮኖሚ ቀውስ መሆኑ እየተነገረ ነው።
አንድ የባንክ ባለሙያ ለዘኢትዮጵያ እንደገለጹት፣ “በባንክ አማካይነት ብቻ ወደ ኢትዮጵያ ይገባል የሚባለው 220 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ነው። 200 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው በሰው እጅ የሚገባው ወይም የሚላከው ነው። በአጠቃይ ኢትዮጵያ በዓመት ወደ 500 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ከመላው ዓለም ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን” እንድምታገኝ ይነገራል። የኢትዮጵያ መንግሥት ግን እስከ ጁላይ 2008 ድረስ 1 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን በቅርቡ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። ከዚያ በፊት በነበረው ዓመት ማለትም በ2007 ግን 633 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ገልጾ ነበር። እንደመንግሥት ብሔራዊ ባንክ ገለጻ ባንድ ዓመት ውስጥ የ400 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ መጥቷል ማለት ነው። በዚህ ጉዳይ አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁት የባንኩ ባለሙያ የሰጡት መልስ “ፈገግታ” ብቻ ነበር።

ሪፖርተር ጋዜጣ አንድ የባንክ ኤክስፐርት ጠቅሶ ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ ኢትዮጵያ “ከወጪ ንግድ ዓመታዊ ገቢዋ በላይ በውጪ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚልኩት ሐዋላ ገንዘብ እንደሚበልጥ አስታውሶ፣ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በተከሰተው የፋይናንስ ቀውስ ጋር በተያያዘ ዲያስፖራው የሚልከው ገንዘብ መቀነሱ ለውጪ ምንዛሪ እጦት አንድ ምክንያት እንደሚሆን “ ኤክስፐርቱ መናገራቸውን ዘግቧል፡፡ ባንድ መግልጫ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ዶላር መጨመሩን በሌላው ደግሞ የውጭ ምንዛሪ መጥፋቱን የሚነገረው ዘገባም ግራ ማጋባቱ አልቀረም።

የሆኖ ሆኖ በውጭ በተለይም አሜሪካ አገር ከዚያም ዋሽግንተን ዲሲ አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በቁጥር በጣም ከፍተኛውን ሥፍራ ይዘው ይገኛሉ። ከነዚህ ሁሉ ወደኢትዮጵያ የሚላክው ገንዘብ ቀላል አለመሆኑን የሚገምቱ አሉ። የባንክ ባለሙያ ግን በዚህ አይስማሙም።”ብዙ ሰው አለና ብዙ ገንዘብ ይላካል የሚለው አስተሳሰብ በጣም የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው።” ባይ ናቸው።” “አንደኛ ነገር እዚህ አካባቢ ያለው የኢትዮጵያውያን ቁጥር እኛ እንደምናስበው በጣም የተጋገነነ አይደለም። ሁለተኛ በኔ ግምት እዚህ ካለው ኢትዮጵያዊ ወደ አገሩ ገንዘብ የሚልከው 30 ከመቶ አይሞላም። ገንዘብ ይልካሉ ከሚባሉትም መካከል ስንቶቹ ምን ያህል ይልካሉ የሚለው መታየት አለበት። ገንዘብ መላክ ብቻ ሳይሆን አንድ ሰው በዓመት ምን ያህል ጊዜ ደጋግሞ ይልካል የሚለው ሁሉ ይታያል።”

ሌላው ነጥብ እዚህ ያለው ኢትዮጵያዊ ባብዛኛው በድህነት ወለል በሚባለው ክልል ውስጥ የሚኖር ነው። እንደሳቸው አባባል በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ አማካይ ገቢው በወር 1500 ዶላር ነው። ከራሱ ተርፎ የሚልከው ብዙም ነገር አይኖረውም።
“እንግዲህ ኢኮኖሚው ተጽእኖ ማሳደር የጀመረው ደግሞ እዚህ እውነታ ላይ ነው። ኢትዮጵያ ድሮ በዓመት ሁለቴ እልክ እንደሆነ አሁን አንዴ ብቻ እንድልክ ያደርገኛል። ያኔ ለአባቴ 500 ዶላር እልክ ከነበር አሁን 200 ዶላር ብቻ እልካለሁያኔ ኢትዮጵያ ቤት መሥራት አስቤ ከነበር አሁን አላስብም።”ብለዋል የባንኩ ኤክስፐርቱ።

አንድ ኢትዮጵያዊ ወደዚህ አገር በመጣበት የመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ገንዘብ ይልካል። ከዚያም እየቀነሰ ይመጣና በመጨረሻ እስከነጭራሹ ያቆማል። ይህ የተመለደ ነገር ነው።

ባለሙያው ያነሱትና ዋነኛ ነው የሚሉት የኢትዮጵያ መንግሥትም ኢትዮጵያውያን ገንዘብ እንዲልኩ አያበረታታም። እንደ ህንድ የመሳሰሉ አገሮች እንዳደረጉት ሌላው ዓለም እንደሚያደርገው ለምሳሌ ህንድ ባንግላዴሽ እንደሚያደርጉት የተለያዩ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች ያስፈልጋሉ። አገራቸው የማይክሮ ኢኮኖሚ ፋንይናስ ሥርዓቱ ጥሩ ነው። ኢንስትመንቱን ይስባል። አንተ እዚህ ሆነህ አገርህ ላይ ብድርን እንድታገኝ አድርገዋል።
እዚህም ሆነህ አገርህ ላይ የውጭ ምንዛሪ እንድትጠቀም። ኢንተርኔት ላይ ሆነህ አካውንትና ባላንስህን ማየት ትችላለህ። እዚህ ሆነህ እዚያ መንግሥትን ማነጋገር ትችላለህ በሩ ክፍት ነው። 24 ሰዓት ክፍት ናቸው። እዚህ ሆነው ህንድ ያለውን የውሃ ቢልህን መክፈል ትችላለህ። ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ማድረግ ፍላጎቱ ያለው አይመስልም።

ከባለሙያው ተጨማሪ ገለጻዎች መረዳት እንደተቻለው ኢትዮጵያውያን እዚህ ሆነው አገራቸውን መርዳት እንደሚችሉት ኢትዮጵያም እዚያ ሆና እዚህ ያሉ ዜጎቿን መርዳት የምትችልበት እድሎችን መፍጠር ይቻል ነበር። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግን ኢትዮጵያውያን የሁለት ቀውስ ሰለባዎች የሆኑ ይመስላል። ወደ ኢትዮጵያ እየተመላለሱ አንዳንድ ነገር የመሞከር አዝማሚያም እየቀነሰ መምጣቱን የሚገልጹ አሉ። በዋሽንግተን ዲሲ አንድ የጎዞ ወኪል (የትራቭል ኤጀንት) ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ለዘኢትዮጵያ ጋዜጣ እንደገለጹት ከዚህ ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገው የበረራ ቁጥር ቀንሷል። ድሮ በሳምንት 6 ጊዜ ይሄድ የነበረው አሁን 4 ብቻ ሆኗል። ምክንያቱም መንገደኛ ቀንሷል። አንደኛ ሰው ሥራ እያጣ ነው ሁለተኛ ሥራ ላይ ያለውም መሄድ አይፈልግም። ቫኬሽን ለጊዜ ቆም ብሏል። ምክንያቱም ቫኬሽን ማለት ወር ወይም 15 ቀን ያህል ነው። አሁን ያን ያህል ጊዜ ደፍሮ የሚወስድ የለም ተመልሰው ሲመጡ ሥራቸውን ላያገኙት ይችላሉ።

ከዚህ አባባልና ከጠቅላላው ዘገባ ሂደት መረዳት እንደተቻለው ሥራ ላይ ያለውም የተፈናቀለውም ሆነ ሥራ የሌለው አንዳች ጭንቀት ውስጥ መኖሩ ግልጽ ይመስላል። የአንድ ሬስቶራንት ሥራ አስኪያጅ እንደነገሩንም በሁለትና ሶስት ቀን ውስጥ ቢያንስ ከ10 እስከ 15 የሚደርሱ የሥራ ፈላጊ ወጣቶችን ጥያቄዎች እየተቀበሉ ነው።

በመጨረሻም በአብዛኛው በዋሽንግተን ዲሲና ቨርጅኒያ አካባቢ የተጠናቀረው ዘገባ እንደ ሜሪላንድ ያሉ አካባቢዎችን ጨምሮ በርካታ ቢዝነስ ድርጅቶችን ያላደረሰ ቢሆንም በአካባቢው ስላለው ሁኔታ ጥቂት ፍንጭ ይሰጣል የሚል ግምት አለ። በተለይ የቨርጂኒያው አቶ ኃይሉ ዳማ እንደሚሉት ደግሞ “ያለውን ሁኔታ ማየት ብቻ ሳይሆን በዚህ ቀውስ የተጎዱ ወገኖቾቻንን እንዴት ልንረዳና ልንደጋገፍ እንደንምችል የምንወያይበት መድረክ መፈጠር አስፈላጊ ነው” የሚልም ጥሪ ቀርቧል። ( ዘኢትዮጵያ)