መላከ ገነት ውቡ ተከበሩ

በዋሽንግተን ዲሲ የመጀመሪያው ቤክተክርስቲያን ካህንና መስራች በመሆን ለ27 ዓመታት ያህል ያገልገሉት መንፈሳዊው አዛውንት መላካ ገነት ውቡ እግዚአብሔርን ባከበሩበት ቤት ክብርን ከምእመናን አግኝተዋል። ሥርዓተ ክብሩ የተካሄደው ጁላይ 16/2006 ቀን በደብረ ገነት መድኃኒዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ነው። ሥነ ሥርዓቱ “የተከበሩ አባታችን ላለፈው እናመስግንዎታለን ቀሪውን ደግሞ ለቀሪው ህይወትዎ ሳይጨነቁ የሚኖሩበትን እንክብካቤ እናንደርግልዎታለን” የሚል ይዘት ነበረው። ካህኑም በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ1976-1998 ድረስ ላበረክቱት አገልግሎት የመታሰቢያ ሽልማት በቤተክርሲያኒቱ ቦርድ ተሰጥቷቸዋል። ብዙ ምስክርነቶችም ተሰምተዋል።

“እሳቸው ከመምጣታቸው በፊት አንድ አባት ነበሩ። አልተመቸናቸውም መሰል ሄዱ። መላከ ገነት ግን ባንመቻቸውም ሁላችንንም እንደጠባያችን ይዘውን ኖረዋል።” ያሉት ወ/ሮ ሠርካለም ነበሩ። ከእሳቸው ቀጥለው ሌሎችም እንደተናገሩት፣ መላከ ገነት ውቡ፣ ንዋይና ምድራዊ ሹመት ሳይደልላቸው፣ የራሳቸው መኖሪያ ቤት ንብረት ሳይኖራቸው፣ መንፈሳዊ አባትነቱን በክብር ተወጥተዋል። የቤተክርስቲያኒቱ ቦርድ ሊቃነመናብርት ከነበሩት መካከል አቶ ገበየሁ ወ/ማርያም እና አቶ ንጋቱ ጥላሁን ፣ ስደት በበረታበትና ካህንም ሆነ ምንም ባልነበረበት ከዚያ ዘመን (1979) አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ መላከ ገነት ያደረጉትን ጥረትና አገልግሎት ዘርዝረዋል።

መላከ ገነት ውቡ፣ ቄስ፣ የደብር አስተዳዳሪ፣ ቦርድ አባል፣ መምህር የነበሩ ካህን ናቸው። በሠርግ፣ በክርስትና፣ ጸሎተ ፍትሃት በመስጠት ከማንም በላይ አገልግሎት ስጥተዋል። ከ11 በላይ አድባራት የሚገኙበትን የገዳመ ተ/ሃይማኖት የመጽሐፍ ቅዱስ ማህበር እንዲመሰረት ያደረጉ መሆናቸውም በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተነግሮላቸዋል። በመንፈሳዊ ህይወትና የሳቸውን ፊደል ቆጥረው ኮሌጅ የበጠሱ ልጆችም በመቅደላዊት አማካይነት “እኛም አደግንልዎ!” ብለዋቸዋል።

ለየት ባለ ውዳሴ “የተቀኙላቸው” አቶ አንዳርጌ በላቸው፣ መላከ ነገት” የግሪክ ቋንቋ አንብበው መተርጎም ብቻ ሳይሆን፣ ግሪክ ነዋሪ በነበሩ ጊዜ፣ የግሪክን ህዝብ በራሱ በቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስን ሲስብኩለት” እንደነበር ተናግረዋል። ግዕዝን አማርኛን እንግሊዝኛና ግሪክኛን አቀላጥፈው ይናገራሉም ተብሎላቸዋል። “በቅጽል ስሙ አንጋፋው መድኃኒ ዓለም ለማስባል የበቁ” እና “የደመራ በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ በአሜሪካን አገር እንዲከበር ያደረጉ” መሆናቸውንም አቶ አንዳርጌ ገልጸዋል።

ከሚኒያፖልስ ደብዳቤ የላኩላቸው ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌም ” መላከ ገንት የቤተክርስቲያንን ልጆች እንጂ የወንዛቸውን ልጆች ለይተው እንደማይሰበስቡ” ከመግለጽ ጋር ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ዓለማዊው ሹመት ሽልማት ሊያጓጓቸው ቀርቶ፣ ቤት አልባ የነበሩትን ካህን ማረፊያ በማጋራት፣ መላከ ገነትን በአባትነት ሲንከባከቧችው የኖሩትና በአርአያነታቸው የተመረጡ ባልና ሚስትም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ሽልማቱ፣ አቶ ሞገስ እና ወ/ሮ ከባድ ወርቅ የተባሉትን በጎ አድራጊዎች ያደረጉትን በማሰብ ከፍ ካለ መንፈሳዊ ምስጋና ጋር ከመድኃኒ ዓለም ቤተርክርስቲያን ቦርድ የተበረከተላቸው መሆኑን የወቅቱ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ዳዊት ተክሉ ገልጸዋል።
በመምህር ዘበነ ለማ በተመራው በዚህ ፕሮግራሙ ላይ ብጹእ አቡነ ገብርኤልን ጨምሮ ከቴለያዩ አድባራት የመጡ ኃላፊዎች ካህናትና ምእመናን ተገኝተዋል። የጉባዔ ቤሪያ መዘምራንም መንፈሳዊ መዝሙር አስምተዋል።

በመጨረሻም መላከ ገንት “አሁን የተነገረው ሁሉ ሕልም እንጂ እውነት አይመስልም…ኮርቻለሁ ኮርቼባችኋለሁ” ከማለት ሌላ ምንም አልተናገሩም። ያሉት ነገር ቢኖር ” እግዚአብሔር ይመስገን” የሚል ብቻ ነበር። (ዘኢትዮጵያ)