የጸሐፊና ጋዜጠኛ ሌ/ኮሎኔል ጌታቸው መኮንን እረፍት

ለአምስት ዓመታት ያህል የፖሊስና እርምጃው ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነበሩ።
ከዚይም የግል ፕሬሶች በብዛት መውጣት በጀመሩበት ዘመን የፈለግ- ጎዳናው- እውነተኛ ፍቅር- ሳላይሽ- መቅደላ- ታደለች- የፍቅር ቀን የመሳሰሉት በርካታ ጋዜጦችና መጽሔቶች አሳታሚ ሆነው ለራሳቸው ብእር ብቻ ሳይሆን ለበርካታ ጋዜጠኞችና ጸሐፊዎች የሙያ መድረክ ፈጥረዋል።
ኮ/ል ጌታቸው እንደ አጋታ ክርስቲ ዳንኤላ ስቲል ሸልደን ሲግል የመሳስሉ ደራሲዎችን መጽሐፍት ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ በመተርጎም ከ65 በላይ የሚሆኑ የትርጉም ሥራዎችን አስነብበዋል። ከነዚህ በተጨማሪ የበርካታ ብእር ስሞች ባለቤት የሆኑት ታዋቂው ጸሐፊና ተርጓሚ ሌ/ኮሎኔል ጌታቸው መኮንን አርፈዋል። እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር መስከረም 2/2001 በ59 ዓመታቸው ባደረባቸው ህመም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ሌ/ኮሎኔል ጌታቸው መኮንን ባለትዳርና የ3ልጆች አባት ነበሩ።

የእኚህ ታዋቂ ጋዜጠኛ ጸሐፊና ተርጓሚ ታናሽ እህት የሆኑት ወ/ሮ ጽጌ መኮንን ለዘኢትዮጵያ ጋዜጣ እንደገለጹት ኮ/ል ጌታቸው ያረፉት ላለፉት 20 ዓመታ አብሯቸው የኖረው የስኳር ህመም ያስከተለባቸውን የጤና መታወክ ለመታከም ወደ ህንድ አገር ለመሄድ በዝግጅት ላይ እንዳሉ ነበር።

እንደ ወ/ሮ ጽጌ ገለጻ ኮሎኔሉ የተወለዱትም ሆነ የተቀበሩት ወሎ ደሴ ከተማ ነው።የተወለዱት በ1945 አካባቢ ሲሆን እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በደሴ ወ/ሮ ስህን ትምህርት ቤት ነበር። ጌታቸው የስነጽሑፍ ዝንባሌው ያደረባቸውና ችሎታቸውም መታየት የጀመረው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንደነበር ወ/ሮ ጽጌ ተናግረዋል።

ወንድማቸው በትምህርት ቤቱ ውስጥ ይካሄድ የነበረው የክርክር ክለብ ፕሬዚደንት የነበሩ ሲሆን በክፍል ውስጥም ግጥሞችን በመጻፍ ያነቡ እንደነበር መስክረውላቸዋል።

ኮ/ል ጌታቸው መኮንን ፖሊስ ሠራዊት ከተቀጠሩ በኋላም በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች አገልግለዋል። ከአባዲና ኮሌጅ እንደወጡ በፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ውስጥ መስራታቸውን ጠቅሰዋል። ጌታቸው ለ5 ዓመታት ያህል የፖሊሲና እርምጃ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በመሆን ተወዳጅ የሆነውን ጋዜጣ ሲያስነብቡ ከመቆየታቸውም በላይ በኣዘገጃጀቱ የተለይ ሆኖ ስርጭቱ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ ማድረጋቸው ይነገርላቸዋል።

ኮ/ል ጌታቸው ምንም እንኳ ሁልጊዜም ከንባብ ያልተለዩ ሰው ቢሆኑም ራሳቸውን በዘመናዊ ትምህርት ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ እንደኖሩ እህታቸው ወ/ሮ ጽጌ መስክረውላቸዋል። ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም በመግባት በዓለም አቀፍ የፖለቲካ ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በላይብረሪ ሳይንስ ዲፖሎማ ከዚያም ህግ ተምረው በህግ ዲፕሎማ እንዲሁም በጋዜጠኝነት ዲፕሎም ከማግኘታቸውም በላይ በተለያዩ የትምህርት መስኮች የሚሰጡ ዎርክሾፖችን መሳተፋቸውን ከእህታቸው ገለጻ ያገኘነው የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።” ጋሽዬ ሁሉንም የትምህርት ዘርፎች በማእረግ አልፎ ተሸላሚ የሆነ ነው። “ያሉት ወ/ሮ ጽጌ መማር የሚሰለቸው ሰው አይደለም።” ብለዋል። ጌታቸው በጀርመን ሩሲያና ፈረነሳይ በመሳሰሉ አገሮች የሥራ ጉብኝቶችን ያደረጉና አጫጭር ሥልጠናዎችንም የወሰዱ መሆናቸውም ታውቋል።

ኮ/ል ጌታቸው መኮንን ወደ 65 የሚደርሱ መጽሐፍትን ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ተርጉመዋል። ከተረጓሟቸው መጻሕፍት መካከል አብዛኞቹ የአጋታ ክርስቲ መጻሕፍት ነበሩ። ትርጉም በሚመለከት ወ/ሮ ጽጌ የወንድማቸውን የንባብና የጽሁፍ ፍቅር የሚያስታውሱበት አንድ አጋጣሚ አላቸው። “ በአንድ ወቅት የዳንኤላ ስቲል Fine Things’ የተባለውን መጽሐፍ አነበብኩትና ወደድኩት። ከዚያ ይህን ነገር ጋሽዬም ቢያነበው ብዬ ላኩለት። ወዲያው አንብቦት “የተካሰ ፍቅር” ብሎ ተረጎመውና መታሰቢያነቱን ለእህቴ ይሁንልኝ ብሎ የኔን ስም አስገባበት።” በማለት ” ጋሽዬ እንደዚህ ያለ ወንድማችን ነበር።” ብለዋል።

ኮ/ል ጌታቸው ከ6 እስከ 7 የሚደርሱ ጋዜጦችንና መጽሄቶችን ያሳተሙ ሲሆን ስያሜዎቻቸውን የሰጧቸው ከራሳቸው ሕይወት ጋር እያያዙ ነው ብለዋል። “ለምሳሌ ታደለች” ያለው ታደለች የ እናታችን ስም ነው። “ሳላይሽ” ያለው ደግሞ ወሎ ደሴ እሱ የተወለደበትና ያደገበት ስፈር ስም ነው።”

የተለያዩ ግጥሞችና ጥናታዊ ጽሁፎችን እንደዚሁም ተውኔቶችን በመጻፍ በሬዲዮና በቴአትር ቤት መድረኮች ያቀርቡ እንደነበር የሚነገርላቸው ኮ/ል ጌታቸው በአንድ ጊዜ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት በአጭር ጊዜ በርክታ የህትመት ውጤቶችን በማውጣት የታወቁ ጠንካራ ሰው በመሆን ይታወቃሉ።

ወንድሜ በነበረው ሁሉን አቀፍ ጥረትና ድንቅ ችሎታ ሁሌም እገረም ነበር። አንባቢነቱ ጠንክራ ሠራተኝነቱ ለበርካቶች እንደ ጥሩ ምሳሌ የሚታይ ልምድ ሆኖ ይቆጠራል።

ከ20 ዓመት በፊት አንስቶ ሲያጠቃው የኖረው የስኳር ህመም ባለፉት ሶስት ዓመታት በርትቶበት በህንድና ደቡብ አፍሪካ ሄዶ ቢታከምም ሊተርፍ አልቻለም። በዚህ ስቃይ መካከል እንኳ ሆኖ የአሳታሚ ቢሮዎቹና አልዘጋቸውም የጀመራቸውን ሶስት የትርጉም ሥራዎች አላቋረጠም ሁልጊዜም ይሰራ ነበር። ደሴ አማተር ጋዜጠኞች እንዲጠናከሩና ክለብ ፈጥረው እንዲቀንሳቀሱ አድርጓል። በአዲስ አበባም ራሱ የሚረዳቸው የስፖርት ክለቦች ነበሩ። በማለት ስለ ወንድማቸው ሁለገብ ተሳትፎ አስረድተዋል። በቅርቡ በተለይም በተወለዱበትና አጽማቸው ባረፈበት ወሎ ደሴ ከተማ ውስጥ ኮ/ል ጌታቸውን የሚዘክር ዝግጅት እሳቸው ባቋቋሟቸው የአማተር ጋዜጠኞችና የሙያ ወዳጆቻቸው አማካይነት ሊካሄድ እንደሚችል ወ/ሮ ጽጌ ገልጸዋል።