ገደል ግቡ

መናደዴን ደርሰኩበት። ቁጣዬን አሰብኩበት። ለካ ኢትዮጵያዊነት መናደድ ነው። ዝምብሎ ብድግ ብሎ መናደድ ነው። ስናድግ በቁጣ ነው። ኢትዮያዊ በቤቱም በአገሩም ቁጣ አለበት። ወላጆች ልጆቻቸውን ይቆጣሉ። ልጆችም ታናናሾቻቸው ላይ ይጮኻሉ። እንዲህ ታደገና የቀበሌና የፖለቲካ ሊቀመንበሮችም ህዝብ ላይ ሲጮኹ አየሁ። የአገር መሪዎችማ ስለ አበባና ስለአየር ሁኔታ እንኳ ሲያወሩ እየደነፉ ነው። ለነገሩማ “ባሌ ዥለጥ ሲያደርገኝ ነው ደስ የሚለኝ” ፣ “ወንድ ልጅ ኮስተር ቆጣ ሲል ነው እንጂ..” ይባል ነበር። ከቆፍጣናው መሪያችን ጓድ መንግሥቱ ኃ/ማርያም አብዮታዊ ቁጣ ጋር ወደፊት መባሉም ታሪክ ነው። የዜናዊ መለስ እንደ እባብ መለሳለስና እንደወይዘሮ መቅለስለስ ወንድነት አልመስል ብሎ አስቀየመ እንጂ ዱላውስ ደስ ይላል- ባህል ነዋ!

እነ ብርቱካን ሚደቅሳ ከመጡ በኋላ ግን ባህል ተበላሸ። እንደጾታዋ ሴት የሆነች ብርቱካን ተንስታ ሁሉንም በትህትና በወግና በህግ ላድርገው ብላ ዋጋዋን አገኘች። ህዝብም መሪም አልተቀበላትም። ትንሽ ያጉረመረሙ ደጋፊዎቿ ተነሱና ጠፉ። ተረሳች። እንደሌሎቹ የፖለቲካ መሪዎች መቆጣትና መደንፋት ብትችል ግን አትረሳም ነበር። ቴዲ አፍሮ ጎሮወሻባዬ ወይም ሽለላና ቀረርቶ መጫወት ሲገባው ያስተሰርያል ብሎ አልጫ ዘፈን ሲያላዝን የሞተ ሰው ገጨ ተብሎ ታሰረ። ከንቀታቸው ብዛት በህይወት የነበረ ሰው እንኳ እንዲገጭ አላደረጉትም። ታረቁ ተስማሙ እስላምና ክርስቲያን አብራችሁ ኑሩ… የሚል አልጫ ዘፈን ለጀግኖቻችን አይስማማቸውም። ትግሉን ጭር ያደርገዋል። ሰላማዊው ፕሮፌሰር መስፍን ደህና መጥተው መጥተው ከተጋጋሉ በኋላ እንደገና ተመልሰው ጸሎት ምናምን ሲሉ ተጋዳላዮቹ ጀግኖች በሰደፍ ወገሯቸው። ምን ማለት ነው? ሰው ትግሉ ሁሉ በተፋፋመበት ጊዜ ጸሎት ምናምን ይላል እንዴ? ወያኔዎች አበዱ። ሰላማዊ ትግል አይሰራም ያሉት ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ሳይቀር ደስ አላቸው።

ስለዚህ ባህላችንም አስተዳደጋችንም ፕሮፌሰር መስፍን እንደሚሉት ኃይልና ጠመንጃ የሞላበት ነው። ስለሆነም ሰው እኔነቱን ባህልና ወጉን አይስትምና

በኃይል ተቆጥቶ መጻፍ ወግ ነው። ዘመኑም ሀሳብን በነጻነት መግለጽ ነው እንጂ ስለ አገለላለጹ አይጨነቅምና እንደፈለጉ መጻፍ ዲሞክራሲያዊ መብት ነው። ስለዚህ ስለንዴታዊ ጽሑፌ ይህን ያህል ካልኩ በቀጥታ ወደ ቁጣዬ እገባለሁ!

ምነው ሸዋ! አሁንስ በዛ! ገደል ግቡ! ሁላችሁም አንዳችሁም እንዳትተርፉ! የዚህነኝ የዚያነኝ ሳትሉ ገደል ግቡ። የናንተን ህዝብነት ቀቅላችሁ ብሉት። አቧራ እሚያገሳ ክፍለሀገራችሁን ተኩራሩበት። ሲረገጥ የሚያንኮራፋ ህዝባችሁን አልቅሱለት። እኔን ግን ተውኝ።

እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ። ኢትዮጵያዊነቴ የማህበር ብቻም ሳይሆን የግሌ ነው። እዚያች አገር ተወልጃለሁ። ሰሜን ደቡብ ምእራብ ምስራቅ አድጌያለሁ። አብሮ አደግ ጓደኞቼ ከሁሉም አካባቢ የመጡ ነበሩ። ሁሉም የጎሳ ዝባንዝኬያቸውን ቋንቋ ምናምናቸውን ቤታቸው ትተው ነበር የሚመጡት። በሚያግባባን ቋንቋ እናወራለን። አፈር ፈጭተን ለማውራት ጨርቅ ኳስ ለመጫወት የቋንቋ ምርጫ አልነበረንም። ስብሰባ አድርገን የወሰነው ነገር የለም። ሳንነጋገር ምንነቱን ሳናውቀው የሚያግባባን ቋንቋን ይኖረናል- ከዚያ እንጫወታለን። ስናድግ ክፋትም አብሮን አደገና ጎሳ ምናምን ተባብለን ተለያየን።

ያኔ ግን ሰው በግሉ እንጂ በማህበር አይሞትም። ጎሳ እየተለቀመ ሲታሰር ሲገደል አይቼ አላውቅም። ሁሉም የገዛ ጎሳውን ሲገድል ግን አይቻለሁ። ያኛውም የዚህኛውን ይኽኛውም የዚያኛውን ገድሏል። ትግሬዎች በተኙበት ተገዳድለዋል። የወያኔዎቹ ታሪክ ይመርመር። ዛሬም ቢሆን ያው ነው። የምን ነገር ማዳነቅ ነው። ስዬ ለመለስ መለስ ለስዬ አብርሃ አይተኙም። አንድናቸው ብሎ ነገር ምንድነው? ደርጎች ደርጎችን ቀርጥፈው በልተዋል። አዳራሽ ውስጥ ተረሻሸነዋል። አብረው የታሰሩት ቅንጅቶች ከእስር ቤት ለመፈታት የቸኮሉት ሊበላሉ ነበር። እናም ተበላሉ። አፈር አባታቸው ይብሉና ተስፋና ህልሜን ቀርጥፈው በሉ። እንደ አንቀልባ እሽኮኮ የሚላቸው ሁሉ ጭንቅላቴ ላይ እንዲወጡ አደረጋቸው። በዚህ የተነሳ በህዝብነቴ አላከበሩኝም። ንቀታቸው ወደር የለውም። ይሉኝታ የሚባል አልፈጠረባቸውም። ማፈሪያ ናቸው። ኤዲያ ወደዚያ! መታሰር ምንድነው? ኦነግም ሻእቢያም ወያኔም ልደቱም ክህደቱም ታስረዋል። የፈለገ ለምን ባፍጢሙ አይደፋም። ይህን አረፍተ ነገር እደግመዋለሁ ማፈሪያ ናቸው። ሌላ በትር ያነሳብኝ እንደሁ እንጂ ይህን በትሬን ማን አባቱ ይቀማኛል!

ደግሞ የብሔር ጭቆና ምናም የሚሉ ገልቱዎች ሰለችተውኛል። ኑሮን ማሸነፍ አቅቷችሁ የበታችነት ስሜት ከደቆሳችሁ የራሳችሁ ጉዳይ ነው። አማርኛ የማይችል አፉን ያዝ የሚያደርገው ሰው ሊኖር ይችላል። ታዲያ ምን ይጠበስ? አማራው ምን ይፍጠር? ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የተማሩ ናቸው። ዶ/ር ላጲሶ የታሪክ ምሁር ናቸው። ገና ለገና አማርኛ ያዝ ያደርጋቸዋልና አንድ የአማራ ገልቱ እበልጣቸዋለሁ ቢለኝስ ለምን ይደንቀኛል? ጫካ ካልገባሁ ነጻ ካልወጣሁ ማለትን ምን አመጣው? እንግሊዝኛ እየተኮላተፉ የሚኖሩበት እንደሸዋትዝኔገር የካሊፎርኒያ ገዢ የሚሆኑበት አገር ተቀምጦ የምን ቋንቋ ምናምን ነው። ባራክን ያየ አባቱ ኦባማን ደግሞ ኬንያ ድረስ ወርዶ ይመለከታል። ኦባማ ግን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነ እንጂ የጥቁሮች ብቻ ነኝ አላለም። አሁን እንዲህ በደቀቀ ዘመን ዓለም ግራ በገባው ጊዜ ሰው ኦሮሞ አማራ ትግሬ ምናምን ነኝ እያለ እዚያ ታች ወርዶ ሬስቶራንት ዘግቶ ብቻውን የሚበላበት፣ መንበረ ታቦት አሳንጾ የሚሳለምበት ዘመን ነው?

ወያኔ ብታልም ትግሬነቷን ነው። ለትግራይ ግን ጠብ የሚል ነገር የለም። ያቺን አሮጊት ኢትዮጵያዬን ብቻ ሳይሆን ያቺን ያልታዳለች ትግራይ ቢጠቅሟት እንኳ አንድ ነገር ነበር። እኔስ ትግራይ አለፈለላት ብዬ አይናቸው ደም እንደሚለብስ ቀናተኞች አይደለሁም። ጎሰኝነትን ጎሰኛ ሆኜ የምዋጋም አይደለሁም። ግን ወያኔዎቹና ጀሌዎቻቸው ምኞታቸው ከአቅማቸው በላይ ሆነ። አለቅጥ ሆዳቸውን ወደዱ። አብረው የሞቱላትን አገር አብረው እየገደሏት ነው። ዝም ብሎ በባዶ ተቀናባት እንጂ ትግራይስ እዚያው ናት። ደግሞም ሊገዳደሉ ይፈላለጋሉ። እግዚኦ ማለት ነው። ከወያኔ በላይ አብሮ የሞተ የት ይገኛል? ማንስ እንደነሱ አብሮ ሊያብር ይችላል። ግን እነሱን እንኳ ሳይቀር ገንዘብ ጮማና የከተማ ጭን አስክሮ ከፋፈላቸው። ዘር ካየው ምን ለየው ሆነና ወረዳ ከፋፈላቸው። አድዋ ሊቅ ተንቤን ሊጥ ሆኑ። መቀሌዎች ከቁጥር አይገቡም። ሽሬዎች እንደሽሮ ናቸው። እንዲህ እያሉ ይሰዳደባሉ። ዛሬ መለስ ለብቻው ሄዷል-የገዛ ክህደትና ይሉኝታ ቢስነቱ አሳብዶታል። ስዬ አብርሃ አድብቷል። ገብሩ አስራት ተቆጭቶ መለስን ለበቀል ያሳድደዋል ። ተወልደና አለምሰገድ ዝንብ እያባረሩ ሲተክዙ ይውላሉ። ጄኔራሎቻቸው ምናምን የሚቀባቡ ሴት ወይዘሮዎች ሆነዋል። ተራሮችን ያንቀጠቀጠ የሚለው ተረት ባዶ ቀርቷል። ምድረ ወያኔን ወዲ አለማሹ መለስ ያንቀጠቅጠዋል። አምቼዎች ከቤተመንግሥቱ ሆነው ያላግጡባቸዋል። ጀግንነታቸው የታለ? ድሮም አስተሳስሮ ያጀገናቸው ጥላቻ ነው።እነሱም ሰፈር እንደኛው ሱሪውን ዘቅዝቆ ያጠለቀው በዛ። ስለዚህ አዳሜ ወያኔ በቁሙ መሞቱን ማየት ተስኖታል። ሁሉም እየተነሳ አርባውን ሲቀባጥሩ ከሚውሉ ከአርባ የፖለቲካ ድርጅቶቹ ጋር ሆኖ አርባውን ይቀባጥራል። ወሬ! ወሬ! ወሬ! የኢንተርኔት ቀረርቶ-

ጠቅላይሚኒስትርነታቸው አቶ አቶ መለስ ዜናዊ “ተቃዋሚው የስኒ ውስጥ ማእበል ነው!” አሉ ፤ እውነታቸውን ነው። ከክፍለሀገር ልጅነት ስኒ ውስጥ ያልወጣ ዓለምን በሱሪው ቁመት የለካ ጎሰኛ ሁሉ ሲጠላም ሲወድም አይሆንለትም። ወይ ክፍለሀገሬ የሚለውን አልምቶ ሰማይ አላደረሰውም። ወይም ክፍለ ሀገራቸው እያለ ጥርሱን የሚያፋጭበትን አላፈረሰውም። ጎሰኞች ክፍለአገርተኞች የዚህ አካባቢ የዚያ ክፍለአገር ልጅ ነን ባዮች የአገሬ ኢትዮጵያ ካንሰሮች ናቸው። ብሄረሰብ ብሎ ነገር ምንድነው? ዘፈን፣ የአቡጀዲና ጥብቆ ጋጋታ የሞላበት አለበባሰ ወይም ግፋ ቢል ምግብ ነው። ሌላ ምን እውቀት ምን ጥበብ ምን ቴክኖሎጂ አገኘንበት? ምን የረባ ባህል ቀዳንበት? ቢጨምቁት ወሬ ነው። ተረት ሥነቃል አፈታሪክ ነው። አግቦ፣ ግልጽነት የጎደለው ፍርሃት የወለደው ቅኔ ነው። ፊት ለፊት ያልሆነ የጓዳ ንግግር የተመሳጣጠረ ነገር ምንድነው? ህዝብ ራሱን እየፈራ በገዢዎቹ ላይ ሲንሾኳሾክ የኖረበትን ባህል እንደ ቅኔ ሲቀኘው መዋሉ ምንድነው? በተራና ቀላል አማርኛ መግባባት አቅቶን ሳለ ቅኔ ምን ያደርጋል? በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ…

አመድ በዱቄት ይስቃል። አህያ ለአህያ ይራገጣል። ዝምብሎ መሳደብ ነው። ያም ተነስቶ እገሌኮ ወያኔ፣ ያም ተነስቶ እገሌኮ ምንትስ ነው ይላል። ደናቁርቶች አስራ አምስት ቦታ ተከፋፍለው ቆመው ወያኔነህ ወያኔነሽ እየተባባሉ ይሰዳደባሉ። “ስድብሽና ስድቤ እኩል ነው ትርፉ ሰው መስማቱ ነው” እንዳለችይቷ ወይዘሮ ሆነ። እናም ወያኔ ይሰማል። አዝብጤ ጎንጤን ወያኔ ነህ ሲለው- አብርሃ ይስቃል። ዘበርጋ ገመቹን ሻእቢያ ነህ ሲለው ተስፋጽዮን ይስቃል። በሀሳብ መለየት ስድብ ነው። የተከተፈ አፍ በዛ። አገር ለምግብም ለወሬም አፉን ከፍቶ እንዴት ይሆናል?

በሉ ደግሞ እኔንም አበደ ወነበደ በሉ ። ቅጽል ፈልጉለት። ወይም ይሄን ያለው ይህን አስቦ ነው። ይሄን ያለው ተልእኮ ቢኖረው ነው ብላችሁ ነገር ተርትሩ። ለራሳችሁ ዋጋ ከመስጠታችሁ ብዛት ሁሌም ሰው እናንተን ፈርቶ ወይም ለናንተን ዋጋ ሰጥቶ ሰላይና ቀስቃሽ የሚልክባችሁ ይመስላችኋል ። በዚህ የተነሳም ከጆሯችሁ ምላሳችሁ ይፈጥናል። ሰፊው ህዝብ ምናምን እየተባባላችሁ ስትሸነጋገሉ ሁለት ሰው ሆናችሁ እንኳ ማውራት የማትችሉ መሆኑን አታስታውሉትም። የገዛ ድምጻቸውን ብቻ መልሰው ለመስማት እንደሚያወሩትም ሆናችኋል። ቅራቅንቦ ወዳጅ፣ ንዋይ አሳዳጅ ሆኖችሁ፣ ኑሮ አገር ሆኖባችሁ፣ የገዛ እንቶፈንቶ ምኞታችሁ ሸክም ሆኖ የሚያንገዳግዳችሁ፣ የገዛ ጥላቻችሁ የሚያሳድዳችሁ ትመስሉኛላችሁ። እብደትም ከናንተ ጋር ናት። ጭካኔያችሁም ከዚያ እብደታችሁ ይመነጫል። ይቅርታ መስጠት የሚችል መሃሪ ልብ እንዳለው ሰው ይቅርታ ልንጠየቅ ይገባል ማለት አፍ መዝጊያ ቋንቋችሁ ነውና በዚያው ቋንቋችሁ ተናግሬ በዚህ ጽሁፍ ላልኩት ሁሉ ነገር ይቅርታችሁን እጠይቃለሁ!

ነገር ቢያበዙት በናንተ አይጫንምና በዚሁ ይብቃኝ!

ገደል ግቡልኝ!