የጥላቻ ፖለቲካ ብሎ ነገር

በሚያስጠላው የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ የጥላቻ ፖለቲካ የሚል ነገር አልፎ አልፎ መሰማቱ አልቀረም። በተለይ ያስጠሊታው ዘመን ዘመንተኞች ደጋግማችሁ ስታወሩት ይሰማል።አባባላችሁ እውነትነት አለው። ውሸትም ደግሞ ሞልቶታል። የቱ እንደሚበዛ ሚዛን ይዘው ነገር ለሚያደላድሉት እንተውና የማታስወሉትን ነገር እንጨወዋወት። “የጥላቻ ፖለቲካ” ማለታችሁ እውነት ነው አንዳንዴ ይሰራል። ሁሉንም ነገር ግን ሁል ጊዜም እንደዚያው ነው ብሎ መደምደሙ ልክ ካለመሆኑም አልፎ አፋችሁ ላይ ስትናገሩት የሚያስጠላበት ጊዜ ደግሞ አለ። አንዳንድ ጊዜ ነገሩን ከሰዎች ነጥዬ ሀሳቡን ብቻ ልጫወትበት ስል እምቢ ብሎ አሸንፎ ይወጣብኝና እነዚህ ሰዎች አንዳንዴ ወደራሳቸውም ጭምር የሚያሳያቸው ይሉኝታ የሚባል ነገር የላቸውም ያስብለኛል። እናም እንዲህ ያስጠይቀኛል። ከዚያም ጥላቻ እንዳይሆንብኝ ሰግቼ የቀባበርኩትንና ያፈንኩትን ነገር ሁሉ እያነሳሁና እየገለጥኩ ስሄድ ውስጤ በቁጣ ሲቃጠል እሰማዋለሁ።ትገርሙኝማላችሁ!

ለምሳሌ ብላቴናው ቴዲ አፍሮ፣ ከሚኒልክ ሆስፒታል ሌሊቱን ነቅቶ ያመለጠውን አስክሬን ገጭቶ ገደለ ስትሉኝ ይህንም ምክንያት አድርጋችሁ በተንተባተበው ፍርድ ቤታችሁ ስትፈርዱ እንዴት አድርጌ ላፍቅራችሁ። ፖለቲካዬስ እንዴት አድርጌ ላጣፍጣው? እሺ ቴዲስ አስክሬኑን ይግጭ ዘፈኑ ደግሞ ማንን ገጨ? ስለምንስ ከሬዲዮ እንዲወገድ አደረጋችሁት? አጋጣሚ ነው አይደል? ብርትኳንን በሶስት ቀን ማስጠንቀቂያ ስታስሯት ቴዲ አፍሮ ላይ ክስ ለመመስረት ለምን አንድ ዓመት ተኩል ፈጀባችሁ? አጋጣሚ ነው አይደል! በነገራችሁ ላይ አቶ አማረ አረጋዊን የደበደቡትን ሰዎች ከቃሊት አንስቶ ፍርድ ቤት ለማድረስ ስንት ቀን ይፈጃል? ወይስ ገና መንገድ አልጀመሩም?…
ሊገርማችሁስ የሚገባው ባልጠላችሁ ነበር። ክቡራትን ክቡራን ወንድሞቼ አልፎ አልፎ በመየካከሉ በድርጊታችሁ ማጉረምረማችን ሲያስከፋችሁ አያለሁ። አሁንስ በዛ! ያልን እንድሆነ ባለጌ ልጅ ሲቆጡት ያለቅሳል ትሆኑብኛላችሁ።

ወጣቷ ብርቱካን የምትሰብኩትን ሰላማዊ ትግል መርጣ በሰላም ልታገላችሁ ስትል፣ ያልወደድነውን ተናገረች ብላችሁ እስር ቤት ስትወረውሯት በሷ ነጻነት ላይ ተረማምጄ እንዴት አድርጌ ላፍቅራችሁ? ጠልቼያችሁ በሆነለኝ። ጉልበታችሁ እሱ ነው። ጥላቻ አይሆንልኝም። በባህሌም በአካባቢዬም በአስተዳደጌም ይሉኝታን አውቃለሁ። ከሁሉም በላይ በታሪኬ ደግሞ የአንድነት ውሉ ይገባኛል። እናንተ እንደነጠላችሁኝ አልነጥላኳችሁም። የለሌለብኝን ከዬት አመጣዋላሁ። በተሳካልኝና በነጠልኳችሁ። በተሰካልኝና እንናተ የምትጠሉኝን ሩብ በጠላኋችሁ። በተሰካልኝና እናንተ ተጠራርታችሁ እንደተቧደናችሁብኝ፣ ለነገር እንደሸመቃችሁብኝ፣ በልባችሁ እንደመዘታችሁብኝ እኔም ሆኖልኝ በዘመትኩባችሁ። ግን አይሆንማ- አንሆንማ- አይደለንማ- ድክመታችን ይህ ነው። ድላችሁ ከዚህ ድክመታችን ከመነጨ ጭካኔያችሁ የተቀዳ ነው። ጨካኞች ናችሁ። ጭካኔያቸሁ ከፍርሃታችሁም ይመነጫል። ፍርሃታችሁም ከገዛ ጥላቻችሁ የተወለደ ነው። መንጋዎቻችሁ የዚህ ጥላቻ አጋፋሪዎች ናቸው። ይህን ባልኩ እንደባለጌ ልጅ አታልቅሱ! ለነገሩማ ልጅ ባለጌም ቢሆን ያው የገዛ አካል ነውና ልጅ ነው። እኔን ግን ከገላችሁ ነጥላችሁ የምታገኙት ነጻነት ምን ምን ይላችኋል?

አዛውንቱን ፕሮፌሰር መስፍን “ዝም በል አንተ!” ብላችሁ፣ አፋችሁም እጃችሁም ባልጎ፣ በሰደፍ ስትወቅጧቸው እንዴት አድርጌ ልውደዳችሁ? የፍቅርን ፖለቲካ ንገሩኝ? የጣልያኑን ግራዚያኒ ማርኮ እንደጣለ ሞስሎኒን እንዳገኘ ሂትለርን አሳዶ እንደያዘ ጀግና አንዲት ፍሬ ልጅ ብርቱካንን ይዤ አሰርኩ ብሎ የሚፎክረውን ይህን እቡይ ጠቅላይ ሚኒስትራችሁን እንዴት አድርጌ ልውደደው! የህጻናትን ጭንቅላት በሰደፍ የሚወግርን ፌደራላችሁን ገዳይ ተጋዳላያችሁን እንዴት አድርጌ ላፍቅረው?

ልጆቼን እንዴት አድርጌ ታሪክ ላስተምራቸው? አያችሁ ልጆች ኢትዮጵያ ድሮ ካርታዋ ይህን ይመስል ነበር። አሁን ግን ተቆርጣለች። እንዲህ የሆነችው ልክ እንደ ይሁዳ ኢትዮጵያን አሳልፎ የሚሰጥ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ የሚባል ድርጅት እስከነ ደጋፊዎቹ ኢትዮጵያ ላይ ነግሦ ነበር… እያልኩ ላስተምራቸው? እንኳን ይህ ዘመን መጪው ዘመን ከጥላቻ ፖለቲካ መውጣቱን እንጃላችሁ! አይንካችሁ አይደርስባችሁ እንጂ ይህን በማድረጋችሁ ትውልድ ሲያፍርባችሁ ይኖራል። እናንተ ስል መቼም አንድ ሰው አይደላችሁም። ሁለቱም ሶስትም አስርም አይደላችሁም። ከዚያ በላይ ብዙ ናችሁ። ይህን ቢያንስ አውቃለሁ። ቁጣዬን ላንድ ሰው ማድረግ አልችልም። ቁጥራችሁ የፈለገውን ያህል ይሁን። ይህ ጽሁፍ የሚለው እኔን ነው፣ ይመለከተኛል- የሚለውን ሰው ሁሉ ይመለከታል። ዓላማውም እሱን እንዲመለከት ነው። ስለዚህ ይመለከተናል ካላችሁ ፍረጡ ተገልበጡ። እናንተ ገዳያችሁን ስለደገፋችሁ ታዲያ እኔ ምን ላድርጋችሁ! እናንተ በድጋፋችሁ ካላፈራችሁ እኔም በተቃውሞዬ አላፍርም። መግደል፣ ማሰር፣ ማባራር፣ ማስፈራራት ምርጫችሁ ከሆነ ምርጫችሁን አልወደውም። አልወደውም ብቻ ሳይሆን እጠለዋለሁ። እናንተ ደጋፊዎች ፍቅራችሁ ከዚህ ግፍ ከሆነ ይህን ግፍ ከሚጠላ ፖለቲካ ፍቅር ይይዘኛልና ተጠንቀቁ!

መውደድ ብቻ ሳይሆን የኔም የናንተም እውነት እንዲሰማ የምጥር ነበርኩ። አብሬያችሁ በነበርኩበት በዚያች ቅጽበት እንኳ ከጀርባዬ ስትንሾኳሾኩብኝ እሰማችሁ ነበር። በቀርብኳችሁ ቁጥር ስትርቁኝ አስተውያለሁ። ሰው ይጠላናል አትበሉ። በኢትዮጵያዊነታችሁ ወድጄያችሁ አይቻችኋለሁ። ያው ናችሁ። ፍቅሬን እንደቂም ኳስ አንጥራችሁ መለሳችሁት። ለመወደድ እንኳ የገዛ ደማችሁ ካልሆነ በጅ አትሉም። እናንተን ለመቃወም ቀርቶ ልክ በሆናችሁበት ነገር ሁሉ ለመደገፍ እንኳ ከናንተ አንዱ ካልሆነ አትፈቅዱለትም። ጥላቻ ብቻ ሳይሆን ፍቅር በልባችሁ እንዳይገባ በቂም ጥርጣሬና ጥላቻ የገነባችሁት ግድግዳ እሺ አይልም። ስንቱን አንጥሮ መልሷል።

ስለዚህ ስሙ ይህን እኔ! እኔ! እኔ! የምትሉትን ነገር ተውት። እናንተ ከማንም አታንሱም- ደግሞም አትበልጡም። የትዝብት አይን ይፈጃችኋል። ታሪክ ይተፋችኋል። ልብ አድርጉ መሪዎቻችሁ ከናንተ የተሻሉ ናቸው። እነሱ እናንተን ጎሰኞች አደረጉ እንጂ እነሱ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ለጥቅም ብለው ተቧደኑ እንጂ ከሁሉም ብሄረሰቦች ጋር ይሰራሉ። የሚበሉ የሚጠጡት ሁሉ አማርኛ ነው። የሚኖሩት አዲስ አበባ ነው። እንኳን አዲስ አበባን አስመራን አልከዷትም። እናንተን አስካዷችሁ እንጂ እነሱ ከሚጠቅማቸው ጋር ሁሉ መብላት ይችሉበታል። እነሱ ይሄ እናንተ የምታላዝኑትን ብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ አያዉቁትም። ቢያውቁትም ትተውታል። ትግላቸው ለገንዘብ ነው። ገንዘብንም ለሥልጣን ይፈልጉታል። ሥልጣንም እንደናንተ ያሉትን ጯኺ ባሮች መንጃ ይሆናቸዋል። ዝም ብላችሁ ትጮኻላችሁ! ተበላችሁ እንጂ እንደነሱ አልበላችሁም! ለነሱ መከታ ሆናችሁ ወገኖቻችሁን አስፈጃችሁ። እናንተ ባትጨመሩበት ይህ ቡድን እንኳን ሰው ዶሮ ማሰር አይችልም። ጋዜጠኛችሁ በአደባባይ ሲወገር አያችሁ አይደል! ታጋያችሁ ስዬ እስከነቤተሰቡ ሲቀለድበት አስተዋላችሁ አይደል! ተራሮችን ያንቀጠቀጡ ያላችኋቸው ታጋይ ጄኔራሎቻችሁ ጓሮ ለጓሮ እየዞሩ ሱሪያቸው በፍርሃት ሲንቀጠቀጥ ተመለከታችሁ አይደል! ጦርነት መሥራት በሚያስፈልግበት ጊዜ ጦርነት ሲያቅት ተመለከታችሁ አይደል። አያችሁት እናንተም እንደኛው ተራ ዜጋና ህዝብ ስትሆኑ ባዶ ናችሁ። አሁንም ይግባችሁ ችግሩ የጎሳ የብሄር ቅብጥርስ ሳይሆን የሥልጣንና የጥቅም ነው። በዛሬይቷ ኢትዮጵያ ኃይልና ሥልጣን የኛም የናንተም አይደለችም- የአምባገነኖች ናት! ዝምብላችሁ አለንበት አትበሉኝ። አለንበት ካላችሁኝ ደግሞ አምባገነንትና ግፍን እጠላለሁና ይህን የሚደግፈውን ሁሉ እጠላ ዘንድ ተውኝ!