ጎሽ የኔ አንበሳ አንተኮ ፖለቲካ አትወድም!

ዴሞክራትን ያየ በቅንጅት አይጫወትም!

In time of war, the truth is so precious it must be attended by a bodyguard of lies.”

በፕሬዚዳንት ሬጋን ጊዜ አሜሪካ ሊቢያን ለምን እንደ ደበደበደች ተጠይቀው የሐሰት ምክንያት የሰጡት የወቅቱ የወጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆርጅ ሹልትዝ “የአሜሪካን ድብደባ እውነተኛ ምክንያት እያወቁ ለምንድነው ሌላ የቅጥፈት ምክንያት መስጠት ያስፍለገዎት?” ተብለው ተጠየቁ። ጋዜጠኞች ያፋጡጧቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም ሲመልሱ ዊንስተን ቸርችልን ጠቅሰው እንዲህ አሉ። “በጦርነት ጊዜ እውነት ማለት እጅግ በጣም ውድና አስፈላጊ ነገር ናት። ሰለሆነችም በብዙ የውሸት ቦዲጋርዶች መጠበቅ አለባት።” ይህ በጆርጅ ሹልትዝ የተደገመው የቸርችል አባባል በወቅቱ ብዙዎችን የሚያስደንቅ ሆኗል።

“እውነት በጣም አስፈላጊና እንቁ ነገር ስለሆነች በብዙ የውሸት ቦዲጋርዶች መታጀብና መከበብ አለባት” ማለት ያኔ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ዴሞክራሲም ግልጽነትም ሰፍኖባታል በሚባልባት አሜሪካም የተለመደ የፖለቲካ ጥበብ ሆኗል። በፖለቲካው ዓለም ሁሉም የየራሱ እውነት አለው። ያቺን እውነቱን ወይም ውስጣዊ ፍላጉቱን ከግብ ለማድረስም ብዙ አግባቢ ቅጥፈቶችን መጠቀም የፖለቲካ ሰዎች ጨዋታ ነው። ማናኛቸው እውነት እንደያዙ ማወቅ ተስኖን ግራ የተጋባንባቸው የኛዎቹ ፖለቲከኞችም የየራሳቸውን እውነት እየነገሩን ነው። ተከፋፍለው በተከፋፈለ መድረክ የቆሙት የቅንጅት ሰዎች፣ ቅንጅት አንድ ነው፣ አልተከፋፍለም፣ ሊከፋፈልም አይችልም እያሉን ነው። ከድርጊታቸው ይልቅ አንደበታቸውን እንድናምን እየነገሩን ነው። ምክንያቱም አንዳንዴ በፖለቲካ ጨዋታ የሚደረገውን ሳይሆን የሚነገረውን ማመን የግድ ነው። የሆነውን ሳይሆን እንዲሆን ወይም እንዳይሆን የምንፈልገውን ብቻ ማመንም ያለ ነገር ነው። በዚያ ላይ ቅንጅት መንፈስ ነው፣ ቅንጅት ተስፋ ነው፣ ቅንጅት ፍቅር ነው…እየተባልን ነው።

ፍቅራችን ከስሙ ነው ወይስ ከሰዎቹ ነው ፣ወይስ ከድርጅቱ? ወይስ ከፍልስፍናው? ፍቅራችን ከዛሬው ቅንጅት ነው ወይስ ከትላንቱ ነው? ፍቅራችን ከትናንቱ ቅንጅት ነው ወይንስ ከወደፊቱ ቅንጅት ነው? ባለፈው ቅንጅት ፍቅር የተለከፉ የወደፊቱንም ይፈልጋሉ? የወደፊቱ ቅንጅት እንደትላንትናው መሆኑ ያጠራጠራቸው ደግሞ ፖለቲካ በቃኝ ይላሉ።

የቅንጅትን ነገር ተወኝ የሚሉ ተነስተዋል። ከእንግዲህ ፖለቲካ በቅቶኛል ያሉም ተሰምተዋል። ነጻ መውጣትን ከሌሎች ትግል የሚጠብቁ ተስፈኞች ሁሌም ትግልና ዳገት እያረፉ ነው ማለታቸው የተመለደ ነው። አዎ ሌሎቹ ነጻ እንዲያወጧቸው የሚመኙ ባሮች ትግል በቃኝ ይላሉ። እንዲህስ ከሆነ ፖለቲካን አታንሱብኝ ይላሉ? ነጻነትን እንዲህ በቀላሉ ሊጎናጸፉ ዴሞክራሲን እንዲህ በቀላሉ ሊያገኟት አስበው ነበር ማለት ነው? ወይስ ቅንጅት የሚባል ድርጅት ይመጣል ብለው ያሰቡ ይመስል እኔ ስለአገሬ ፖለቲካ የማስበው ቅንጅት የሚባል ፖለቲካ ድርጅት እስኪፈጠር ነው? እንደዚያ ካልሆነ ግን ፖለቲካ በቃኝ ማለት ምን ማለት ነው?

ይልቅ ነገረ ዓለሙን ስተን ባንቀልድ ጥሩ ነው። ነጻ የምንወጣው እኛ እስከሆን ድረስ የትም ገብተን የትም ብለን የሚስማማንን ድርጅትም ሆነ የትግል ስልትና መንገድ መፍጠር የኛ ጊዜን ይቆጥባል። የአርባ ቀን እድላችን ለብርሃኑ ወይም ለኃይሉ ወይም ለመለስ ዜናዊ የተሰጠ ይመስል እዬዬው ምንድነው? ካልሆነላቸው ካልሆኑልን ለምን ገደል አይገቡም? እኛ ጥሩ ህዝብ እስከሆን ድረስ ጥሩ መሪ አናጣም? እኛ መሪዎቹ በወጡ በወረዱ ቁጥር የምናኮርፍ ከሆነ እንደ ከብት የሚነዳንን የምንጠባበቅ ከሆነ እውነትም ከብቶች ነን ማለት ነው። ሲሆን ሲሆን መሪዎቻችንን መፍጠርም ሆነ ማባረር የምንችለው እኛ መሆን ነበረብን። ለነገሩማ እኛ ጠንካራ የድርጅት አባል መሆን ብንችል ለሥልጣን የሚያበቃን ጠንካራ ድርጅት መፍጠር እንችል ነበር። ግን አይደለንም። ሰዎችን እንጂ ድርጅት አንከተልም። አንድ ግለሰብ የሚነዳን ወይም አደራጅቶ የሚያሳድረን እስክንመስል ድረስ የመጣ የሄደውን ሁሉ ስንከተል ኖረናል። ነገም ያንኑ ባለጥሩ ምላስ ሰው እንጠባበቃለን። ጥሩ ንግግር ያደረገን ሰው ከጥሩ ድርጅት የምናስበልጥ ሰዎች ነን። አገር በጠንካራ ድርጅት እንጂ ባመረ ንግግር ነጻ አትወጣም። ቀጣፊ ሁሉ ኦባማን አይደለም። ቦራክ ኦባምም ቢሆን ያለ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ብቻውን በምድረበዳ እንደሚጮህ በሆነ ነበር!

ቅንጅት መንፈስ ነው ወይስ ድርጅት ነው? የምርጫ መንፈስ ማምጣቱ የለውጥ መንፈስ ማነሳሳቱ ማንቃት ማነቃቃቱ እንደውቅያኖስ የረጋውን ህዝብን ከዳር እስከዳር ማእበል ሆኖ ማገላበጡ ቅንጅትን መንፈስ ሊያስመስለው ይችላል። እውነትም ቅንጅት መንፈስን ሊሰብክ ህዝብን በምርጫ አጥምቆ እንደ ክርስትና ዴሞክራሲ ሊያስነሳ ያሰበ፣ ህዝብን የሥልጣን ባለቤት ሊያደርግ የተነሳ ድርጅት ሆኖ ታይቷል። አንዴ የተዘራን የለወጥ መንፈስ ወደኋላ መመለስና ከሰው ጭንቅላትና ልብ ውስጥ ማውጣት የማይቻል በመሆኑ ከዚያ አንጻር የቅንጅት መንፈስነት ትልቅ ድል አስመዝግቧል። ምንም እንኳ የገዢዎችን እድሜ ሊያሳጥር የሚያስችል ውጤት ማምጣት ባይችልም በቀደመው አካሄዳቸው መሄድ እንደማይችሉ አስተምሯቸዋል። ምንም እንኳ የልባቸውን ማወቅ ባይቻልም ባንደበታቸው ትንናት ለማለት ይጠየፉት የነበረውን ሁሉ እንዲሉ የኢትዮጵያን ገናናነት ቀደምትነትና ታሪካዊነት እንዲመሰከሩ አስችሏቸዋል። የናቁትን ህዝብ ወርደው ማነጋራቸው ወጣቱን ገበሬውን ሴት ወንዱን በየቡድኑ ማማከራቸው ቅንጅት መጥቶ ከሄደ በኋላ በገዢዎቹ ዘንድ አድሮ ያየነው ትልቅ የለውጥ መንፈስ ነው። ከዚህ አንጻር ቅንጅት መንፈስ ነው ብለን ልናይ የምንችልበት አግባብ ይኖረናል። ቅንጅት ድርጅት ስለመሆኑ ግን በ እርግጠኝነት ለመናገር አልቻልንም። ምክንያቱም ቅንጅት መንፈስን ለመስበክ እንጂ የፖለቲካ ድርጅት ፈጥሮ ሥልጣን ለመጋራትም ሆነ ለመቀበል የተጠራ ድርጅት መሆኑን ማየት አልቻልንም። እንዲያውም መሪዎቹ ከመንፈስነት በመውጣት ለሥልጣን የሚታገሉ ናቸው እየተባለ ይነገር ጀመር። ግን ቅንጅት የተጠራው ለለውጥ መንፈስ ሰባኪነት ነው ወይስ ለፖለቲካ ሥልጣን ነው?

ልደቱም ለሥልጣን ኃይሉም ለሥልጣን ብርሃኑም ለሥልጣን የሚል ነገር ሰማን? ታዲያማ ለሥልጣን ካልሆነ ምን እንዲያደርጉልን ነው የምንፈልገው? ህዝቡም የመረጣቸው ያልወደዳቸውን ባለሥልጣኖች አስወግደው የሱ ምትክ ባለሥልጣኖች እንዲሆኑለት ነው እንጂ ኳስ እንዲጫወቱለት አይደለም። ችግሩኮ ሥልጣኑን ማግኘት አለመቻላቸው ነው እንጂ መመኘታቸው አይደለም። ችግሩ ገና ከወዲሁ ለሥልጣን መጣላታቸው ነው እንጂ ሥልጣኑን መፈለጋቸው አይደለም። ጥያቄው የሥልጣን ጥመኝነታቸው ሳይሆን ለዚያ የሚያበቃቸውን ጠንካራ ድርጅት አስቀድመው መስራት አለመቻላቸው ነው። ይህ በቅንጅት መሪዎች ዘንድ የታየ ድክመት ነው። ቅንጅትን የፈጠሩ ሰዎች መሪዎቹ ለሥልጣን እንዲበቁ አሰበው ነው። አንዳንዶች እንደሚሉት እርስ በርስ የሥልጣን ሹክቻ ማድረግም ቢሆን ነውርነት ያለው ነገር አይደለም። በአሜሪካ የፓርቲ መሪዎችም ሆኑ እንደ ኦባማ ክሊንተንና ኤድዋርድ ጆ ባይደን ያሉ ፕሬዘዳንታዊ እጩዎች የአንድ ፓርቲ ሰዎች ናቸው። ፓርቲን እንደ እንደ ቅርጫ መከፋፈል የለመዱት የኛዎቹ ፖለቲከኞች ከዚህ የሚማሩ አይደሉም።

ለማንኛውም ግን ሥልጣን ላይ ያለውን ፓርቲና መንግሥት ማስወገድ የሚችለው የእድር ኮሚቴ የእቁብ ወይም የቤተከርስቲያን ሰበካ ጉባዔ አይደለም። ሥልጣን መረከብ የሚችለው ፣ሥልጣንን እንዴት አድርጉ በፍጥነት መንጠቅ የሚችል ጠንክራ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ለዚህ ደግሞ እወረደ እየወጣ እየተገለባበጠም ቢሆን የፖለቲካ ጨዋታ በሚፈቅደው መንገድ ሁሉ እየሄደ ጎል የሚያስቆጥር ጥሩ የፖለቲካ ቡድንና ግለሰብ ያስፈልገናል። አሜሪካውያንን እንደ አገርም ቢሆን ለዚህ ያደረሳቸው ዴሞክራሲያቸው ብቻ አይደለም። ለአገራቸው ለጥቅማቸው ሲሉ የሚያደርጉት የቅጥፈት ጨዋታቸውም ጭምር ነው። እነ ክሊንተንን ያየ ይከራከር። ለነገሩማ የኛዎቹም የፖለቲካ መሪዎችም ባንላቸውም መዋሸታቸው መቅጠፋቸው አልቀረም። ወጣቶቹ ሲሸመጥጡ አዛውንቶቹ ሳይቀሩ ሲቀጥፉ ግጥም አድርገው ሲዋሹ አስተውለናል። ቅጥፈታቸውን እያየን ዝም ያልነው ፖለቲካው ስለሚፈቅድ ለትግሉም ስለሚረዳ እያልን ነው እንጂ ህጻናትና ገልቱዎች ሆነን አይደለም። ግን ችግራችን ለምን እንደዚያ አደረጉ ሳይሆን እንደዚያ አድርገው ምን ውጤት አስገኙ ነው? ወደ ተራ አሉባልታ የወረደ ቅጥፈታቸው ራሳቸውን ትዝብት ላይ ከመጣል ተርፎ ትግላቸውን ወደፊት አላራመደላቸውም።

ህዝብ ብዙ ዘበኛ የሚያቆመው ፖለቲከኞች ለረጅም ጊዜ ሥልጣን ላይ እንዳይቆዩ የሚከላከለው ቅጥፈታቸውን ስለሚያውቅና ከጥቅሙ በላይ አልፈው እንዳይሄዱ ነው። ፖለቲካ ዝም ተብሎ እናቶቼ አባቶቼ እህቶቼ ወንድሞቼ በሚል የካህን ቃል ብቻ አይካሄድም። ወይም እኔ ቆራጥ ነኝ አንበሳ ነኝ ፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ በሚል አጓጉል ግብዘነትና የዜግነት ንግድ የሚካሄድ አይደለም። ኢትዮጵያዊ ያልሆነ የለም። አብረው ሲሰሩ ኢትዮጵያዊ፣ ሲለያዩ የሌላ አገር ዜጋ ሆኖ የሚያድር ሰው የለም። ውሸት ሲባል ይህና እንዲህም አይደለም። ቡሽ አሜሪካዊ አይደሉም ኦባማ ክሊንተን መኬዬን አሜሪካዊ አይደሉም አልተባለም ወይም አልተባባሉም። ይህ ነገር አሜሪካንን አይጠቅምም ይጎዳል ማለት ያለ ነው። እኛም አገር ይህ መለመድ አለበት። ማነው ኢትዮጵያን የሚወድና የሚጠላ የሚል ተራ ነገር ሳይሆን ለኢትዮጵያ የሚበጃት አስተሳሰብ ፍልስፍናና ፖሊሲ ያለው ማነው የሚለው ነው። ጥሩ አደረጃጀት ያለው የተቀላጠፈና ጊዜና ዘመኑን ማንበብ የሚችል ማነው ማለት አገርን የሚጎዳ ወይም የከዳ አስተሳሰብ አይደለም። በርካታ አባላትና ተከታይ ያሉት፣ ዓለም አቀፍ ተሰሚነት ያለው፣ የፋይናንስ አቅሙ የደረጀ፣ ድርጅታዊ ጥንካሬው ስር የሰደደ፣ ማስገደድም ድርድርም መጠቀም የሚችል፣ ተናግሮ ሊደመጥ ሞግቶ ሊረታ የሚችል፣ ጠንካራ ድርጅት ማነው የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል። ግለሰብ ሳይሆን ድርጅት? ቅንጅትም መንፈስ ነው ፍቅር ነው አንድነት ነው…ተባለ እንጂ ግለሰብ ወይም ግለሰቦች ነው አልተባለም። ሰዎች አላፊ ናቸው። ድርጅት ግን ዘለዓለማዊ ነው። ክሊንተንዬ በጣሙን እወድሻለሁ ግን ከፓርቲዬ ከዲሞክራት አትበልጪም…አዎ እኔም ፕሬዚዳንት ብሆን በወደድኩ ግን ከፓርቲዬ አይበልጥብኝም። ዴሞክራትን ያየ በቅንጅት አይጫወትም።