ብሄረ ሰው!

አንድ የሃይማኖት ሰባኪ ምዕመናኑን ሲያሰናብት “በሚቀጥለው እሁድ ውሸት ኃጢአት መሆኑን የሚያብራራ ትምህርት እሰጣችኋለሁ። ለትምህርቴ እንዲረዳችሁ እባካችሁ የማርቆስ ወንጌልን ምዕራፍ 17ን አንብባችሁ ኑ” ይላቸዋል።

በሳምንቱ መልካም ምእመናን እንግዲህ ትምህራትችንን ከመጀመራችን በፊት “ስንቶቻችሁ ናችሁ ምዕራፍ17ን ያነበባችሁ?” ብሎ ሲጠይቅ ከጥቂቶች በስተቀር ሁሉም አንብበናል ለማለት እጃቸውን አወጡ።

ሰባኪውም “የማርቆስ ወንጌል ከ16 በላይ ምዕራፍ የለውም። ውድ ምዕመናን፣ ውሸት ኃጢአት መሆኑን የሚያብራራውን የዛሬ ትምህርታችንን እንግዲህ ከእዚህ ተነስተን እንጀምራለን “አላቸውና ማስተማሩን ቀጠለ ይባባል። ኢትዮጵያ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ተጽፎ የነበረ ቀልድ ነው።

ቀልዱን ኮስተር ብናደርገው ምእመናኑ የሌለ ምእራፍ አንብበናል ብለው እጃቸውን በደመነፍስ ያወጡት ለመዋሸት ፈልገው ብቻ ላይሆን ይችላል። መምህሩን ላለማስቀየምም እንዴት የቤት ሥራ ሰጥቶን ሳንሰራ መጣን እንላለን ብለው ሊሆንም ይችላል። የሆነ ሆኖ ግን ትምህርቱ ስለውሸት መሆኑን እንኳ ያላስተዋሉት ምእመናን ዋሽተዋል። ለነገሩ አብዛኞቹ (ሰፊው ህዝብ) ስለነበሩ ዋሽተዋል ማለት ይከብዳል፤ ተሳስተዋል ማለት ይሻላል። ውሸት ለሰፊው ህዝብ የሚመች ቃል አይደለም። ህዝብ ይሳሳታል እንጂ አይዋሽም። “ሕዝብ ይዋሻል” ብሎ ማሰብ በራሱ ሐጢአት ስለሆነ፣ ቶሎ ብሎ እግዜር ይቅር ይበለኝ የሚያስብል ነገር ነው። እንደዚያ ብሎ ለመናገር ቀርቶ ለማሰብ የሚያስችል የህሊና ነጻነት ስለሌለ ብቻ ሳይሆን፣ ትክክል አለመሆኑን በደመነፍስ የሚነግር አንዳች ስሜት አለ። ህዝብ ልክና ትክክል ነው። ግን ሁል ጊዜ እንደዚያ ነው?

ህዝብ ሁሌም ትክክል ነው የሚለው የዋህነት፣ ለህዝብ ከማሰብ ብቻ የሚመጣ ሳይሆን፣ ህዝብ የሚባለውን ውስብስብ ጉድ በሚገባ ካለማጤንም የሚመጣ ሊሆን ይችላል። አሁን ኢትዮጵያ ላለችበት ችግር የመንግሥት ድርሻ 99 ከመቶ ቢሆን የህዝብ ደግሞ 1 ከመቶ እንኳ ሊሆን ይችላል ብሎ ማመን ላወቀበት ሰው፣ ምናልባት የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ ሊሆን ይችላል። ቀበጥ ልጅ በቅጥብቱ የሚደርስበት ችግር ይኖራል። የገዛ ልጅን ቆንጥጦና ገርቶ ማሳደግ ደግሞ የቤተሰብ ኃላፊነት ነው። በገዛ ኃላፊነቱ ጭምር ችግር የደረሰበትን የገዛ ህዝብንም እንዲሁ ማድረግ “ይህ የኔ ህዝብ ነው” የሚል ወገን ሁሉ ኃላፊነት ነው።

የኔ ህዝብ የኔ ብሔረሰብ የኔ ክፍለሀገር ብቻ ማለት አይበቃም። እንደዚያ ማለቱ የግድ የሚያስፈልግ ከሆነ፣ ለመሆኑ የኔ ህዝብ ወይም የኔ ጎሳ ምን እያደረገ ነው? አስተሳሰቡ እንዴት ነው? ተሳትፎውስ ምን ይመስላል? እያሉ መጠየቅ ለዚያ ህዝብ ከሚሰጡ ገጸ በረከቶች ሁሉ የመጀመሪያው ይሆናል። መጀመሪያ ራስን ማየት፣ ከዚያም ይህ ሕዝቤና ወገኔ የሚባልን ነገር ወጣ ብሎ ማየት ይገባል። ይህን ደግሞ “እኔኮ ለህዝቤ ነው!” የሚሉ የፖለቲካ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ሰው ሊያደርገው የሚገባ መልካም ነገር ነው። ካለበለዚያ ለውጥ አይመጣም። ከመንጋው ጋር በጅምላ መነዳትና መንጋጋት፣ የመንጋው መንጋጋ በተመታ ቁጥር የገዛ ድድም መድማቱ አይቀርም።

ከዚህ ኃላፊነት የሚያስቀረን አንዱ ፍርሃት ነው። እንዲህ ብል እንዲህ ይለኛል፣ ህዝቡ ይበላኛል፣ ህዝቡ ያድምብኛል፣ ወገኔ ከማህበር ያወጣኛል… ማለት አይቀርም። ይህ መንግሥትን ከመፍራት የበለጠ ትልቅ ፍርሃት ያሳደረ አንዱ የፖለቲካ ባህላችን ካንሰር ነው። ከማህበር ውጭ ብቻውን መቆም የማይችል ጯኺ ሁሉ ተሸቀዳድሞ፣ በሉት! ውገሩት! ቤተክርስቲያን የገባች ውሻ አድርጉት! ዜግነቱን ግፈፉት! እያለ አዋጅ የሚያስነግረው፣ ከበሮ የሚያስደልቀው ይህ ማስፈራሪያ በመኖሩ ነው። መስዋእትነት የመንግሥት እሰር ቤትና ጥይት ብቻ አይደለም። ይህን የጅምላ ጅራፍም መጋፈጥ ይገባል። ከዚህ ጅራፍ ነጻ ለመሆን የግል ነጻነትን መጎናጸፍ ያስፈልጋል። ሊቀመንበር ልሁን፣ ተከታይ ይኑረኝ፣ ህዝብ ግብር ይጣልልኝ፣ መንግሥትም መደለያ ይስጠኝ፣ አጨብጫቢዬ ይብዛልኝ፣ ዝናዬ ከፍ ከፍ ይበልልኝ የማይል እሱ ነጻ ሰው ነው። ማንንም ደገፍኩ ማንንም ተቃወምኩ ይህ የኔ የማይገሰስ የግል መብቴ ነው፤ ቢፈልግ አንድ ሚሊዮን አይደለም አንድ ቢሊዮን ሰው (ህዝብ) ይቃወመኝ፣ እኔ ግን ባመንኩበት ጸንቼ እቆማለሁ ማለት የጽናት ሁሉ መጀመሪያ ነው። ለዚህ ደግሞ ህዝብ ማነው? እኔ ያለሁበትስ የቱ ጋ ነው? እኔስ ከሱ የምፈልገው ነገር ምንድነው? ብሎ በቅድሚያ ማሰብን ይጠይቃል።

እንደኔ የሚያስቡ በማህበራቸው ሳይሆን እኔንም በቀላቀለ ማህበራችን የሚያስቡና የሚያሳትፉኝ ከሆነ እኔና እነሱ ህዝብ መሆን እንችላለን። እኔን ያልጨመረ ህዝብ ግን ህዝቤ አይደለም። እኔ የሌለሁበት ጎሳ የኔ አይደለም። የኔ የሚሆነው እኔንም እንደራሱ ጎሳ “የኔ ነው” ሲለኝ ነው። ከኔ የተለየ፣ እኔን ያልጨመረ ኢትዮጵያዊነት አላውቅም። ኢትዮጵያዊነቴን ከኔ የሚቀማ ወይም ሊሰጠኝና ሊነሳኝ የሚገምተኝ ኢትዮጵያዊ አለመኖሩን ግን በሚገባ አውቃለሁ። ምክንያቱም ቀኝ እጄ ለግራ እጄ እውቅና አይሰጠውም… እንዲህ ያለ አስተሳሰብ የሚሰጠን አዲስ መንፈስ ያስፈልገናል።

ጅምለኞች ቀፍድደው ይዘውናል። ጎሰኞች ግራና ቀኝ እጃችንን ከፋፍለው ያሟግቱብናል። እኔ ኦሮሞ ካልሆንኩ አንድ ሰው መጥቶ ኦሮሞነቱን የሚነገረኝ ለምንድነው? አማራ ካልሆንኩ የእሱ አማራነቱ ምን ያደርግልኛል? እሱ ትግሬ ስለሆነ ታዲያ ምን ይጠበስ? እሱ የደቡብ ወይም የሰሜን ልጅ ስለሆነ – ጉራጌ ነኝ- ጎንደሬ ነኝ፣ ጎጃሜ ወይም ወለጌ ነኝ ስላለኝ ታዲያ ምን አባቴ ላድርግለት? በዛ። በጣም በዛ። እንከባበር ብሎ ነገር ምንድነው? አክብሬ ምን ላድርገው? እሽኮኮ ልብለው? አሞላቁኝ፣ አስቡኝ፣ እውቁኝ- እወቁልኝ ማለቱ በዛ። እሺ አንተ ሲዳማ ነህ እንበል፣ እኔ ደግሞ ጉራጌ ልሁን፣ እና አሁን ሁለታችን በጋራ ማን ተብለን እንጠራ? አሜሪካን አገር ሄደን አንድ ፈረንጅ ሲጠይቀን ማን ነን ከየት ነን ብለን እናስረዳው? እኔና አንተ በምን ቋንቋ እናውራ? ሌላ ሰው አንተ ማንትስ ብሎ ብሄረሰብህን ስለሰደበ ታዲያ ምን አባቴ ላድርግህ? ያንተው ጎሳ ያንተኑ ጎሳ ሲገድል ሲያስር ሲያሳድድ አልኖረምን? አሁንስ ይሕንኑ እያየን አይደለምን? በዛ!

ይልቅ እኔንም አንተንም እኩል የሚዳኘን መስፈርት ይኑረን። ብሄረሰብ ምናምንህን እዚያው ለራስህ ከቢጤህ ጋር ቀቅለህ ብላውና እኔና አንተ እኩል የምንናገርበት ፕሬስ፣ እኔና አንተ እኩል የምንታይበት ፍ/ቤት፣ እኔና አንተ እኩል ተወዳድረን ልንቀጠር የምንችልበት የሥራ ቅጥር ሥርዓትና መ/ቤት ይኑረን። የእኔና አንተ ሰውነት ይቅደም። እዚህ አሜሪካን አገር ለሥራም ሆነ ለኃላፊነት እንደምንወዳደረው እስኪ እኔና አንተ አገራችንም ላይ እንደዚሁ እንወዳደር። እዚህ ሰው – እዚያ ብሄረሰብ የምንሆነው ለምንድነው?

ያ ዘመን አልፎበታልና ይቅር። ይኸው አልሰራም። ታየ! ሁሉንም ሥልጣን ሁሉንም ገንዘብ መፍለጡንም መቁረጡንም ሁሉንም አዩት። ተለቆላቸውም ሆነ አስለቅቀው ሌላው ተቀምጦበታል ብለው የቋመጡለትን አልጋ እንጣጥ ብለውበት አዩት! ድሮ ተናቅን ካሉት በላይ ተናቁበት። ሌላው ብቻ ሳይሆን “የኔ ነህ – ያንተ ነን” ያሉት ወገናቸው ሳይቀር ጠላቸው እንጂ ፍቅርና ሞገስን አላገኙበትም። ይህንን ጎሳ በማውረድ የራሱን ጎሳ ለማንገስ እየገሰገሰ ያለው ሁሉ ያንን ለመድገም እየሮጠ ከሆነ ምን አዲስ ነገር አለ?

በፈለገው መንገድ ቢገላበጥ ችግራችን አሁንም ይኸው ነው። መንግስት ሆኖ ለተቀመጠው ጎሳ – ሰላም ማለት እኔ ሥልጣን ላይ ሆኜ እየገዛሁ ልቀጥል ማለት ነው። በተቃዋሚ በኩል- የኔና ጎሳ ሥልጣን ላይ ካልወጣ ኢትዮጵያ ሌላ መሪ አያምርባትም ማለት ነው። ለሁለቱም ወገኖች ኢትዮጵያዊነት እንደነዚህ ነው። በኢትዮጵያ የብሔረሰቡ (85) እና የፖለቲካ ድርጅቱ (91) ብዛት ተቃራራቢ የሆነውም ለዚህ ይመስላል። የትኛውንም ወገን ብሄረሰብ ቢሉት፣ ክልል ቢያድርጉት፣ ብሄርም ቢሉት ሌላው ጋር ሲደርስ ኢትዮጵያዊ ነው። መጨረሻው ኢትዮጵያዊ መሆኑ የማይቀርን ነገር ደግሞ ከመነሻው ለምን ኢትዮጵያዊ አናደርገውም። ከዚያም አልፎ “ሰው ሁሉ ሰው ነው” ማለት ብንችልማ በምን እድላቸን። ግን በማህበር እንጂ በግሉ ራሱን ችሎ መቆም የማይችል ስንት ሰው ስላለ ኢትዮጵያ መቸም ቢሆን መቸገሯ አይቀርም። ዛሬ ዛሬማ የሥራ መጠየቂያ ሬዙሜያችን (ሲቪያችን) ላይ “ፕሮፌሽን” በሚለው ቦታ ብሄረሰብና ክፍለሀገራችንን ለመሙላት ትንሽ የቀረን እየመሰልን ነው።

“ብሔራዊ እርቅ” የሚባለው ነገር የማይጨበጥ ጉም ሆኖ የቀረው መጀመሪያ ራሳችንን ከዚህ የቡድን ማንነት አንጽተን “ሰው ብቻ” ሆነን የመቆም ቅንነትና ድፍረት ስለሌለን ነው። ሰው ሆነን ካየነው ሁሉም ሰው ሰው ነው። ከዚህ መርህ በኋላ ሰውም አገርም ይስተካከላል። ልማትም ይደላደላል። ሰላምም ይወርዳል። እኔነትም በአጃቢ ሳይሆን በራሱ አደባባይ መውጣት የሚችል ነገር ሆኖ ይከበራል። ክብር ከፈለግን መጀመሪያ እኔ ሰውዬው መታየት አለብኝ የሚል ጠንካራ እምነት ያስፈልገናል። ራሳችንን በተውሶ ሳይሆን በራሳችን ማኩራት አለብን። ላሊበላን አይቶ እኛን እንዲያይ ሳይሆን እኛን አይቶ ላሊበላን እንዲያይ ማድረግ ካልቻልን ላሊበላም የኛ እኛም የላሊበላ አይደለንም። የምንናገረው ሳይሆን የምናሳየው ማንነት ያስፈልገናል። እንዲህ ነኝ፣ እገሌ ነኝ፣ የእነገሌ ነኝ የማለትን ጉራ አብዝቶ፣ ትንኝ አሳክሎ ዝሆን ተራ ያስቆመንም ይህ የማንነት ቀውስ ነው። ማነን? (ዘኢትዮጵያ)