የአይቲንክ- አይቲንክ ጨዋታ

ኢትዮጵያዊያን ዳር ሆነነ ምራቃችንን በምንውጥለት የሰው አገር ዴሞክራሲ አንዳንዴ ተሳታፊ መሆን ሲያምረን፣ ጥልቅ እንልበትና “የአይቲንክ- አይቲንክ” ጨዋታ እንጫወታለን። “ አይቲንክ አሜሪካ ለጥቁር ፕሬዚዳንት ሬዲ አይደለችም… ። አይሚን ነጮቹ ዘረኞች ስለሆኑ ኦባማን አይመርጡም ። እኔ ግን አይዶንቲክ የአሜሪካ ህዝብ እንደሱ የሚያስብ አይመስለኝም። ምክንያቱም ለውጥ ይፈልጋል። አሁን ግን ይሄ የጥቁርና ነጭ ጨዋታ እየቀረ የመጣ ይመሰለኛል። ዌል፣ አይቲንክ እኔ ይህን ነገር ሳየው….

አቤት ይቺ “አይቲንክ- አይቲንክ” ጨዋታ እኛ አገር ብትመጣ ጥሩ ነበር። አይዶንቲንክ ኢትዮጵያ ከሸኮቾ ከዳውሮ ከመዥንገር ለሚመጣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዝግጁ አይደለችም….!?

እንኳን ሌላው የመለስ ትግሬነት የሚያንገበግበው ብዙ ነው። እነሱም አማራው ገዛን ብለው አምጸው ነው ጫካ የገቡት። አሁንም ሌላ ሌላውን ይቀባጥሩ እንጂ መንግሥትም ይሁን ደጋፊዎቹ ይህ መንግሥት ከሥልጣን እንዳይወርድ የሚፈልጉት አማራው መልሶ ሥልጣኑን እንዳይዘው ነው። ከሥልጣን ስኳር ትንሽ ትንሽ የቀመሱት አንዳንድ የትናንሽ ብሔረስብ ሰዎችም አይዶንቲክ ቁጥሩ ብዙ ለሆነው ሌላ ብሔረሰብ ከእንግዲህ ሥልጣን ለመልቀቅ ዝግጁ አይደሉም። እኔም ተራ ይድረሰኝ የሚለው ኦነግም ነገ ሥልጣን ቢሰጡት እሱም ተገልብጦ እንደ ወያኔ የባንዲራ ቀን ያከብር ይሆናል። ሥልጣን ከተገኘ እንኳን ኢትዮጵያዊነት የባንግላዴሽ ዜጋ መሆንም ይመቻል። በፍቅር የዘረሩን ኦባማ እንኳ አይሁድ ነኝ ለማለት ትንሽ ሲቀራቸው ሰምተናል።

ለማንኛውም ግን ጥቁሩ ኦባማ ሥልጣን ቢይዙ ጥቁሮች ደስ ይላቸዋል። ከዚያ በኋላ ግን ከቤተመንግሥቱ አንስቶ እስከ ካውንቲው ድረስ ሁሉን ነገር ጥቁሮች በሞኖፖል ይይዙታል ብለው አይጠብቁም። የጥቁር ፕሬዚዳንት ምሳሌያዊነቱ ግለሰባዊ ነው እንጂ ጥቁሮች ሁሉ ወደ ኋይት ሓውስ ይንጋጋሉ ማለት አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይህ አይታሰብም። ጦሩም ደህንነቱም ፖሊሱም ጳጳሱም ባንኩም ፍራንኩም ሁሉም ቁልፍ ነገር በአንድ አካባቢ ሰዎች መጥለቅለቅ አለበት። የአገራችን ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ኮተቱና ጓዙ ብዙ ነው። ኦባማ ግን ምክትላቸውን እንኳ ለመምረጥ ስንት መከራ አይተው ነው። ባለቤታቸው ሚሼል ኦባማንኳ አሁን ገና በአሜሪካዊነቴ ኮራሁ በማለታቸው ተተችተዋል። እኛም ዘንድ ይህ ትችት ቢመጣ ኢትዮጵያዊ ነኝ በማለትና በኢትዮጵያዊነት በመርካት መካከል ብዙ ልዩነት መኖሩ ያሳስባል።

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ያረካንና ያለረካን ብዙ ነን። ረክተናል የሚሉት “የጀመርነውን ፈጣንና ዴሞክራሲያዊ የልማት ጎዳና” እንዳይደናቀፍብን ብለው ይሰጋሉ። አገሪቷ አድጋለች እያሉ ፍቆ እየቆጠሩ፣ መንገድ እየመተሩ፣ ስለ ኢኮኖሚው ፈጣንና አስተማማኝ እድገት እያብራሩ ዛሬን ከትላንት እያነጻጸሩ ይከራከራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ለረሀብ የተጋለጡ ህጻናትን እየቆጠሩ፣ የኑሮን ውድነት በኪሎም ይሁን በጣሳ እየሰፈሩ፣ ከወለል በታች እንኳ እንዳይባል ከሥር ወለል የጠፋለትን ድህነት እያስተነተኑ፣ ሥራ አጡን፣ ታማሚውን፣ ቤት አልባውን፣ እስረኛውን፣ ወላጅ ያጣውን እየዘረዘሩ ዛሬን ከትናላንት እያነጻጸሩ በቁጭት የሚከራከሩም ብዙ ናቸው።

ነገሩን ወግ አስይዞ ለመናገር ክርክር አልነው እንጂ የሚበዛውስ ንትርክ እንጂ ክርክር አይደለም። ከሚነገረው ሀሳብ ይልቅ ተናገሪው ሰው በአቋሙ ደጋፊ ወይም ተቃዋሚ ነው ተብሎ አስቀድሞ ስለሚገመት ሁሉ ነገር የሚታየው በዚያው አንጻር ነው። ጆሮም አይንም አንደበትም ማስተናገድ የሚፈልጉት ለዚያ አቋም ተስማሚ የሆነው ነገር ብቻ ነው። አዲስ አበባ ፎቆችና መንገዶች እየተሰሩ ነው ማለት ለስሜት ደስ አለማለቱ ብቻ ሳይሆን ልክ ጸያፍ እንደመናገር ሊዘገንን ይችላል። የሶማሊያን ጦርነትና ከበስተጀርባው ያለውን ደባ ወይም የኦጋዴንን ነጻ አውጪ ግንባርን አስጊነት ጦርነትና የነገ ጦስ ጠቅሶ መቃወም፣ ይሄ ሰውዬ የወያኔ ደጋፊ ብቻ ሳይሆን አባቱም የታወቁ የጣልያን ባንዳ ሳይሆኑ አይቀርም ሁሉ ሊያስብል ይችላል። በዚህ በዚህ እንኳ መንግሥት ልክ ነው ማለትማ በኢትዮጵያ ታይቶ የማይታወቅ ክህደት ነው። 99 መጥፎ ነገር አውርቶ አንዲት መልካም ነገር መናገር ዜግነት ሊያስገፍፍ ይችላል።

ደግሞ በዚህም ጫፍ ችግር አለ። ኢትዮጵያ ግን አሁንም ስሟ በረሀብና በድርቅ እየተጠራ ኢኮሚኖሚዋ በፍጥነት ማደጉ እንዴት ነው? የሚለው ጥያቄ እንዴት ተለጥጦ በየትኛውም ዴሲማል ተጣፍቶ ከፀረ ትግራይነት ጋር እንደሚገናኝ አይታወቅም። ይህ መንግሥት አምባገነን መሆኑን ያለፍርድ ሰው ገድሎ ያሳየ፣ ያለ ህግ አስሮም ህግ መቀየር የሚችል መሆኑን በራሱ ሰዎች ሳይቀር ያሳየ፣ በምርጫ ሳይሆን በኃይል ሥልጣን ላይ የተቀመጠ መንግሥት ነውና ከሥልጣን ይነሳ ማለት- ለምን ወዲያው ሄዶ የትግራይ ህዝብ ጎሰኛ ነው ተባለ፣ ጸረ ኢትያጵያዊ ነው ተባለ እንደሚባል አይታወቅም። መንግሥት ህዝቡ ላይ ከሚያደርሰው አፈና በላይ ፣ ወያኔ እያልን የምንሰጠው አስተያየት፣ የትግራይ ወንድሞቻችንን እንዳያስቀይምብን ብሎ መሳቀቅና በቁጭት መታፈን የቱን ያህል እንደሚያሰቃይ ያልገባቸው ቢገባቸውም ለዚህ መጨነቅ የማይፈልጉ ደጋፊዎች አሉ። ስዬና መለስ አሁንም አንድናቸው በሚስጥር ተመካክረው ሴራ እየሸረቡ ነው እኔ ትግሬዎችን አላምንም የሚሉ የአማራም ይሁን የኦሮሞ ወይም የሌላው ጎሳ ጎሰኞች መኖራቸው እውነት የሆነውን ያህል ገደለም ቀጠፈም መለስ ዜናዊ ትግሬ ነውና ዘለዓለማዊ ሥልጣን ይገባዋል የሚሉ ጎሰኞች መኖራቸው ሐሰት አይደለም።

መንግሥታዊ በደልና ግፍን ሁሉ የተቃወመን ሁሉ ሆን ብለው ወደ አማራነት የሚያሳንሱና ነገሩን የብሄረሰብ ጨዋታ የሚያደርጉ የፖለቲካውን ትግልና ውይይት ማካባዳቸው አልቀረም። እውነት ነው የአማራ ወኪል ነኝ ብሎ በኢትዮጵያዊነቱ ላይ ጥያቄ አንስቶ የወጣ ድርጅት አለመኖሩ ማንንም ያስቀይማል ብለው የሚክዱት ነገር አይደለም። የዚያኑ ያክልም ቋንቋው አጋልጦ ስለማይሰጣቸው ነው እንጂ አማርኛ ሥር የተደበቁ የዚህ ክፍለሀገር ልጅ ነኝ የዚህ አካባቢ ነኝ እያሉ ወንዝ ለወንዝ የሚጠራሩም ጎጠኞች መኖራቸው ሐስት አይደለም።

የዚያኑ ያክል ደግሞ በቃ አማራ ሆኜ ተፈጠርኩ ታዲያ ምን ይጠበስ? ቋንቋዬ ፊደሌን ወጌን ባህሌን እወደዋለሁ፣ ታሪኬን እኮራበታለሁ። የተሟላች ድንበሬን እጠብቃለሁ። ከወንድሞቼ ነጻ እወጣለሁ ያለ ድርጅት አልበቀለብኝም። ገና ለገና አማራ ነኝና የኢትዮጵያ መሪ መሆን የምችለው እኔ ብቻ ነኝ የሚል ሌላ ገልቱ አማራ ስላለ እኔ ምንላድርግ? አማራው ሁሉ አንድ ሰው የሚመስላችሁ ለምንድነው ብሎ በምድረ በዳ የሚጮህ አለ!

እዚህም ደግሞ ትግራይ እምባ የለም ያላችሁ ማነው ይላችኋል! እና ታዲያ ወያኔ ከትግራይ ተጠራርቶ ተደራጅቶ ስልጣን ስለያዘ እኔ ትግሬ በመሆኔ ምናባቴ ላድርጋችሁ? ያው እስሩም አልቀረልኝ፣ ታዩኛላችሁ እንደናንተ ተሰድጄ፣ ሠርቼ ነው የምኖረው፣ ወይ ከአገሬ አልሆንኩ ወይ የናንተን እምነት አላገኝሁ እውነት ነው ወያኔዎቹ ሁሉ ትግሬ ናቸው ትግሬዎች ሁሉ ግን ወያኔዎች ለምን ይመስሏችኋል? አማራው ሁሉ ብአዴን ነው? ደግሞስ ቢሆንስ ትግሬው በትግሬነቱ እንጂ በምክንያት መንግሥትን መደገፍ አይችልም ያላችሁ ማነው? አማራው አማራ ስለሆነ ኃይሉ ሻውልን መደገፍ አይችልም ማለት ነው? እናንተስ ብትሆኑ አዲስ አበባም ይሁን በየክፍለሀገሩ ስንት ዘመን አብረን ስንኖር ያልተናገራችሁትን ቤተመንግሥት ስንገባ ወደመጡበት እንመልሳችኋላን ያላችሁን ወራሪነታችን የሚሰማችሁ ለምንድነው? ለመሆኑ ከየትኛው ዓለም ነው የመጣንባችሁ!

ኦሮሞው ይቀጥላል በዚያ በኩል አዎ በሉ እስኪ ፖለቲካ ተማሩብኝ፣ አገር ስትዘርፉና ስትገድሉ ኖሯችሁ በኔ ኦሮሞነት ኢትዮጵያዊነትን ሸምቱ፣ኢትዮጵያን ያለማችሁ ይመስል ኢትዮጵያን የሚያጠፋ መጣ እያላችሁ ቀስቅሱ! አዳሜ ተነስቶና ቃዥቶ ኦነግ ነኝ ኦህዴድ ነኝ ስላለ ኦሮምያ ብሎ ስለዘመረ እኔ ምን ላድርጋችሁ? ብደግፍ ኦህዴድ ብቃወም ኦነግ እያላችሁ ቁም ስቅሌን የምታሳዩኝ ምንድነው? ኦሮምያ ትገንጥል የሚል ስንት ኦሮሞ ታውቃላችሁ! ስለ ሰብአዊ መብት አፋችሁን የምትከፍቱ ሁሉ እስር ቤት ያለውን ኦሮሞ ቁጥር ታውቁታላችሁ? ጎንደሬ ነኝ ጎጃሜ ትግራይ ነኝ ጉራጌ ስትሉ በኩራት ነው። ኦሮሞ የሚባል ነገር ፖለቲካ ሆኖ የሚያስደነግጣችሁ ለምንድነው?

እንዲህ እያለ ሁሉም በያለበት ይጮኻል። አብዛኛው መድረክ ግን በየብሔረሰቡና በየድርጅቱ ባሉ አክራሪዎች ጩኸት የተሞላ ይመስላል።ይህ ጩኸት እስካለ ድረስ ስለተሰራው መንገድም ሆነ ሰለተራበው ህጻን ደንታ ያለው ሰው መኖሩ አይታይም። ጩኸት የግድ ከሆነ እንዲህ ተብሎ ቢጮኽ ጥሩ ነው፦ሁላችሁም ከዘፈንና እስክስታ ያልዘለለ ነገር የማይታበት ብሔረሰባችሁን እዚያው ለየራሳችሁ አድርጉት። ይልቅ አክራሪዎች ብሰሉና፣ አገር ሆነን ስለ ህገመንግሥት፣ ስለ ፕሬስ ነጻነት፣ ስለኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ ስለግለሰብ መብትና ግዴታ እንነጋገር። ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻ በቂ ይሁን። የቋንቋና የጎሳ የመንደር ኬላ ይሰበር። አመድ በዱቄት አይሳቅ!

አይቲንክ ይሄ ህዝብ ለእንደዚያ ያለ ሀሳብ ገና ሬዲ አይደለም። (ዘኢትዮጵያ)