አበባ እና ኢትዮጵያ!
በኢትዮጵያ በተለይም አዲስ አበባ ኑሮ ተወዷል። ሁሉ ነገር ጨምሯል። ፍቅርም ሳይቀር ጨመረ መሰል የ700 ብር እቅፍ አበባ ይዞ ወደ ፍቅረኞች መሄድ እየተለመደ መሆኑ ተዘግቧል። በተለይ ባለፈው ዓመት የቫለንታይንስ ቀን የአበቦች ዋጋ ሰማይ ነኩና እስከ 700 ብር ድረስ ለመሸጥ በቁ። አባዛኛውን ተራ ህዝብ ያስተናግዳል በሚባለው ገበያ ደግሞ የደከመችና የጠወለገች አንዲት ዘለላ ጽጌሬዳ 10 ብር ማውጣቷም ተነግሯል። ዋናው ሀሳቡ ነውና ፍቅርና ትርጉሙ ለገባው ሁለቱም እኩል ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ። ግን አለ አይደል.. የ700 ብር እቅፍ አበባ የታቀፈች ጉብል ለፍቅር ቀን ያላት ትርጉም የተለየ ሊሆን ይችላል። ያለው ማማሩ ያጣ ሲያስጠላ ነው እንዲሉ የ10 ብሪቱን አንዷን እንጨት ጽጌረዳ እንኳ መግዛት ላቃተው ለዚያ ፍቅረኛ ግን ወዮለት!
በዚያ ላይ አዲስ አበባ እንደተሰማው ከሆነ ሁነኛ ሬስቶራንት ገብቶ ራት በልቶ ለመውጣት ቢያንስ ጥቂት የባለ መቶ ብር ኖቶች ኪስ ውስጥ መኖራቸውን ማረጋገጥ ግዴታ ነው ይባላል። በተለይ የቫለንታይንስ ቀን ሲሆን ደግሞ እንደውጭ አገር አስቀድሞ ተደውሎ ቦታ ተይዞ የሚኬድባቸው ሬስቶራንቶች መኖራቸው ተነግሯል።በዘንድሮው የቫለንታይንስ ቀን ደግሞ ባለሶስትና ባለአራት ኮከብ ሆቴሎች ለፍቅረኛሞች ከ250 እስከ 2000 ብር የሚከፈልበት ልዩ የፍቅረኛሞች የእራት ምሽት ማዘጋጀታቸውን አዲስ አድማስ ጋዜጣ ዘግቧል።
ባለፈው ተመሣሳይ መልክ የነበረው መሆኑን የአገር ውስጥ ጋዜጦችን ጠቅሶ ዘኢትዮጵያ ጋዜጣ መዘገቡ አይዘነጋም ። ለምሳሌ ባለፈው ዓመት ናዝሬት ስኩል አካባቢ የሚገኝ “ስሬኔድ” የተባለ አንድ ሬስቶራንት ለቫለንታይንስ ቀን የመጠጥ ዋጋን ሳይጨምር በሰው ሁለት መቶ ብር ማስከፈሉ ተዘግቧል። መቸም ለብቻ አይኬድምና ሁለት ሆነው ከሄዱ አራት መቶ ብር ብቻ ለምግብ መክፈል የግድ ነው ማለት ነው። አዲስ አበባን ከሒልተን ጋር ብቻ የሚያውቃት ሰው ታዲያ ለዚህ ለዚህ ሒልተን ለምን አይኬድም የሚል ሀሳብ ሊኖረው ይችላል። ሒልተን ራሱ በዚያን ቀን በሰው ለአንድ ራት ያስከፍል የነበረው 395 ብር ነበር። 400 ብር ማለት ነው። ሁለት ሲሆኑ 800 ብር ይሆናል። ለማንኛውም እንግዲህ እስከነምናምኑ አንድ ሺ ብር መያዝ አስፈላጊ ነው ማለት ነው። የአበባው ዋጋ ሳይገባ መሆኑ ነው። አበባውም ቢሆን የሰሞኑ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ከአምናው ጭማሪ አሳይቷል። የአንድ ቀንበጥ ጽጌረዳ 2ብር እየተሸጠ ሲሆን እስከነ መጠቅለያው 3ብር ከ50 ያወጣ ነበር። አሁን ግን 5 ብር ገብቷል። በቫለንታይንስ ቀን ደግሞ እስከ 10 ብር ሊደርስ መቻሉ ተዘግቧል።እንዲያው ሲያጋንኑ ነው እንጂ ከ4ብር አላለፈም የሚሉ አሉ። እንደፎርቹን ዘገባ የአበባ ዋጋ መጨመሩን ጨምሯል። አንዷ ቀንበጥ ጽጌረዳ 1ብር ከ45 ሳንቲም ነበረች። በአሁኑ ቫለንታይንስ 4ብር ተሸጣለች።
የአበባ ነገር ከተነሳ ኢትዮጵያ አበባ አበባ ብላ ልትሞት ነው። ኢትዮጵያ በየወሩ 80 ሚሊዮን የአበባ ዘለላዎችን 40 ወደሚሆኑ አገሮች ትልካለች። ከዚህ ውስጥ 70 ከመቶ የሚሆነውን የምትገዛው ኔዘርላንድ ናት። ጀርመን እንግሊዝና ሩሲያም የኢትዮጵያ አበባ ተሰማምቷቸዋል። ወደ አሜሪካ በመጠኑ ቢላክም ገበያው ገና መሆኑ ይነገራል። ኢትዮጵያ የአበባ እርሻ በመኖሩ ከ50 ሺ በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች የሥራ እድል መፈጠሩን ትናገራለች። በ2007 ከአበባ ብቻ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ማግኘት እንደተቻለም ባለሥልጣናት ይናገራሉ። ገቢው ከቀደመው ዓመት ጋር ሲስተያይ በ 5 እጥፍ መጨመሩም ይነገራል። በዚህ የልብ ልብ የተሰማው መንግሥት የቡናን ገቢ በአበባ ለመተካት አስቦ እንደነበርም ተነግሯል። እንዲያውም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ከአበባ ከምታገውኘው የውጭ ምንዛሪ ይልቅ ከቡና የምታገኘው የምንዛሪ መጠን የበለጠ እንዲሆን ጥረት እንደሚደረግ ማሰቡን አንድ ባለሥልጣን በወቅቱ ተናገረዋል። አሁን ባለው ድርሻ ግን አበባ እያስገኘው ያለው የውጭ ምንዛሪ አገሪቱ የተለያዩ ሸቀጦችን ኤክስፖርት በማድረግ ከምታገኘው ሁለት ከመቶ እጅ ብቻ መሆኑ ተገልጿል።
አስገራሚው ነገር ደግሞ ይህ ሁሉ ከተነገረለትና ከተፎከረለት በኋላ ዘንድሮ በመንግሥት የተሰጠው መግለጫ የተለየ ሆኖ መገኘቱ ነው። ለምሳሌ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ውስጥ 298 ሚሊዮን ዶላር ያስገኛል ተብሎ የተጠበቀው የአበባ ንግድ 177.6ሚሊዮን ዶላር ብቻ ማስገኘቱን አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ለሮይተር መግለጻቸውን ጀርመን ድምጽ ዘግቧል። አበባን ለማልማት በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የተበደሩት ነጋዴዎችም ገንዘቡን መክፈል ስላልቻልን የብድር መክፈያው ጊዜ ይራዘምልን በማለት እየጠየቁ መሆኑም ተዘግቧል። የሆኖ ሆኖ አበባ በውጭ ገበያው ቅናሽ ማሳየቱ እየተነገረ ነው። ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ አንዱን ነጠላ እንጨት አበባ በ $1.28 መሸጥ ይዛ ነበር። አሁን ወደ $0.25 ወይም ስሙኒ (ኳርተር) ወርዷል።
የኢኮኖሚ አዋጭነቱን ብቻ ሳይሆን አደገኝነቱን በመጥቀስ የአበባን ንግድ መስፋፋት የሚቃወሙ ወገኖችም አሉ። እንደነሱ አባባል የአበባ ንግድ ለዓመታት ስትስራው ለኖረችው ኬንያም ሆነ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች አልሆነም። አበባ በተመረጠና በተከለለ ቦታ የማይተከል ከሆነ የእርሻ መሬትንም ሆነ የተፈጥሮ አካባቢን በመበከል የሚያመጣው ጉዳት ከፍተኛ ነው ይላሉ። በኢትዮጵያ በአበባ ሥራ ላይ ከተሰማሩት 80 ከመቶ የሚሆኑት ወጣት ሴቶች እንደሆኑና በርካሽ ጉልበታቸውንም እየተበዘበዙ እንደሆነ በመግልጽ በሌላው የግብርና መስክ፣ በትምህርትና በቤተሰብ አስተዳደርና ላይ የሚያመጣውን ተጽእኖ እየጠቀሱ ይቃወማሉ። በጤፍ አምራችነታቸው የሚታወቁት እንደ አድአ ጤፍ አምራች አከባቢዎችም ጤፉን እየተው አበባ ማሳ ላይ መሰማራታቸው ተወርቶ ነበር።የአበባን እርሻ ሥራዬ ብለው ማምረት የይዙት ግን 74 ድርጅቶች ናቸው። ከሁሉ ከሁሉ ደግሞ በአበባ ሥራ ላይ በድንገት የተሰማሩት በአብዛኛው የውጭ አገር ዜጎች በመሆናቸው ጉዳያቸው ከንግዱ እንጂ በአገር ላይ ከሚያመጣው ዘርፈ ብዙ ችግር አይደለም የሚሉ አሉ።
የውጭ ኢንቨስተሮች ነገር ከተነሳ ኢትዮጵያ ህንዶችና ቻይናውያን የተቀራመቷት አገር እየሆነች ነው ብለው ስጋት የገባቸው ተሰምተዋል። ልክ እንደ ቻይናውያን ሁሉ ህንዳውያንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ እያደረጉ ያሉት ድንገተኛ እንቅስቃሴ ጠቃሚነቱና አሳሳቢነቱ አነጋጋሪ እየሆነ ይመስላል። ባለፈው ሳምንት ይፋ የተደረገው አንድ የመንግሥት መግለጫ እንዳመለከተው በኢትዮጵያ ኢንቨስት እያደረጉ ያሉ ህንዳውያን ቁጥር በአስገራም ቁጥር ጨምሯል። በቅርብ ጊዜ በፊት በኢትዮጵያ 50 ብቻ የነበሩት የህንድ ኩባንያዎች ዛሬ 270 ደርሰዋል። ማለትም በ220 ከፍ ብለዋል ማለት ነው። ህንዳውያኑ በአበባ ሥራ ብቻ ሳይሆን በኮንስትራክሽንና ግብርና ዘርፎች ከፍ ያለ ድርሻ እየያዙ መምጣታቸውም ተነግሯል። በአብዛኛው መልኩ በህንዳውያንና ቻይናውያን እየተገፉ ከገበያ ውጪ እየሆኑ ያሉት ኢትዮጵያውያን የቢዝነስና እና በተለይም የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች አዝማሚያ አሳሳቢ መሆኑም እየተገለጸ መሆኑም ተሰምቷል። የኢትዮጵያ ነገር አንድ ሰሞን ሰማይ ነካን ብለው ወዲያው ዘለው እንደፈረጡት የምስራቅ እስያ “ታይገርስ” ወይም ባዶ ህንጻ ብቻ ታቅፈው እንደቀሩት አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች እንዳይኮን ስጋት ማደሩ አልቀረም። ከጽጌረዳ አበባው ጋር እሾህም መብቀሉ ያለ ነውና ጥቅምና ጉዳቱን ማሰብ እንደሚገባ የሚመክሩ አሉ። (ዘኢትዮጵያ)