አገር በቃላት እየተጫወተ ይመስላል!አገር በቃላት እየተጫወተ ይመስላል። ለፍትህ ለነጻት ለዴሞክራሲ ለአንድነት ለሰላም ለብልጽግና ለፍቅር….ሁሉም ከእነዚህ ቃላት ጋር ይተኛል። ቃላቱም ከአንዱም ሰው ጋር አይጸኑምና ከሁሉም ጋር ይጎለምታሉ። መጽሐፉ እንደሚል ደግሞ ከጋለሞታ አፍ ማር ይንጠባጠባል። አቤት ሰዎቻችን ሲናገሩ ፖለቲከኞቻችን ሲደስኩሩ መምህራን ሲያስተምሩ እንዴት ደስ ይላሉ። የእግዚሐብሔርን ቃልና ፍቅርን የታደሉት ካህናትማ ስብከትን ሲሰብኩ መስማት ነው። እግዜር ግን ቃል ያጣ ይመስል ስብከትን ስብከት ማሰኘቱ ይገርማል። ወይንስ አውቆ ነው? የሰው ልጅ ገና ከታናሽነቱ ጀምሮ….

አባቶቻችን ግን ጎበዞች ናቸው ይኽ ሰው ሰባኪ ነው ይሉ ነበር አሉ። ስብከት ውሸት ማለትም ነበር። ዛሬ የስብከት ትምህርት ይባላል። ድሮ ትምህርት ትምህርት ነው ሌላ ቅጽል አይፈልግም። ዛሬ ግን አንድ ቃል ብቻውን መቆም የፈራ ይመስል ሌላ ቃል ይደረብበታል። ስለዚህ ተለያይተው በለያዩ ፣ ተከፋፍለው በተከፈፋሉ የእምነት ስፍራዎች ሁሉ የ”ስብከት” ትምህርት አለ። ሁሉም ፍቅርን እየሰበኩ ያስተምራሉ። የተፋቀረ ሰው ግን አላየንም። አስተማሪዎቻችንም አልተፋቀሩም። “አይዩዪዪዪዪዪዪ! ትንሽ ቀደም ብለህ ብትመጣ ጌታ አሁን እዚህ ከኔጋ ነበር” ከሚሉት አንስተው፣” እኛ ጌታን የተቀበልነው የዛሬ ስንት ሺ ዓመት ነው” እስከምንለው ድረስ የፍቅር መምህራን ሞልተውናል።

ውሸት ውሸት ውሸት በዛ። ምርጫ ተብሎ በኢትዮጵያ ሲዋሽ አየን። በህይወት የሌለ ሰው ተወዳድሮ አሸነፈ የተባለበትን፣ ከቁም- ሙት የተሻለበትን ምርጫ አየን። 99.9 ከመቶ ኢህአዴግ አሸነፈ። ሂደቱም ፍጹም ዴሞክራሲያዊ ነበር ተባለ። ለምርጫው ገንዘብ (100 ሚሊዮን ብር?) ወጥቷል። የአገር ሀብት ባንኳል። ጊዜ ተቃጥሏል። በዚህ ፌዝ የተቃጠለ ወይም የሚቃጠል አንጀት ግን እየጠፋ ይመስላል። ምክንያቱም ኖርማል ነው (ተለምዷል)። አዲስ ነገር አይደለም። ውሽቱ አስቀድሞ ታውቋል። መንግሥት እንደሚያሸንፍ ሳይሆን እንዳሸነፈ ህዝቡ ያውቃል። ህዝቡ እንደሚያውቅም መንግሥትም ያውቃል። ግን ይህ ታላቅ የውሸት ሥነሥርዓት ህግና ደንብ ነውና መፈጸም አለበት። “ዴሞክራሲ በሂደት የሚመጣ ስለሆነ..” እዚያ ዴሞክራሲ ላይ እስኪደረስ ድረስ ከዚህ ውሸት መጀመር አለበት ይባላል ። ግን መነሻው ውሸት የሆነ መንግሥትና ህዝብ መድረሻቸው የት ነው?

ህዝብ ሁሉን ነገር ያውቃል ይባላል። የት አለ ዕውቀቱ! መንግሥት ፖለቲከኞችና የፍቅር መምህራን እየተነሱ እንደ ህጻን ልጅ ለምን ይቀልዱበታል? የእነዚህ ሁሉ ምንጭ ህዝብ ነው። ህዝብ ተቃውሞ ስላለው ብቻ ለምን በተቃዋሚነት ብቻ ይታሰባል? የህዝብ ድጋፍ ለምን አይታይም። የሚደግፈውን እየለየ ገንዘብ እያዋጣ ይሰጣል። ውጣ ሲሉት ይወጣል። ተነሳ! ቁጭ በል! ሲሉት ይታዘዛል። ተናገር! ዝምበል! ሲሉት ይፈጽማል። ግን ታላቅ ነው ክቡር ነው ተብሎ እንደታቦት ይመለካል። በድህነት በፍርሃት በውንዥብር ታስሮ መኖሩ ደግሞ ግራ ያጋባል። ሁሉን አዋቂ ነው የተባለው ህዝብ እርስ በርሱ እንዳይተላለቅ ይፈራለታል። ወይ ስጋቱ ልክ አይደለም ወይም ህዝብ የሚባለው ነገር እንደሱ አይደለም። ከሁለት አንዳቸው ውሸት ናቸው። ወይም በዚህም በዚያም ተብሎ ህዝብ ጀግና መባል አለበት። ጥቂቶች ግን ሊያታልሉት ሊበጠብጡት እርስ በርስ ሊያጫርሱት ይችላሉ የሚል ፍርሃት አለ። ለምንድነው ሁሉን አዋቂ የሆነውን ሰፊው ህዝብ ጥቂቶች የሚያታልሉት? በዚህም በዚያም ይነዱታል ያፋጁታል ተብሎ የሚገመተው ለምንድነው? የት አለ እውቀቱ? ታላቁ ህዝብ እንደ ህጻን ልጅ ሞግዚት የሚያስፈልገው ለምንድነው? እኛ የቆምነው ለህዝብ ነው ህዝቡን ከአደጋ ለማዳን ነው እያሉ ራሳቸውን በራሳቸው እየሾሙ ወደድክም ጠላህም የቆምነው ላንተ ነው የሚሉት መብዛታቸው ታዲያ ለምንድነው?

ሁሉም እየተነሳ ህዝቡ በዚህ ገብቶ ህዝቡ በዚህ ወጥቶ ይላል። ስለራሱ ሳይሆን ስለሌላ ህዝብ የሚያወራ ነው የሚመስለው። ራሱ የሌለበትን ህዝብ ማማት ማምለክ ማንሳት መጣል ተለምዷል። “እኔኮ ይህ ህዝብ ያሳነዛኛል እንደ ኢትዮጵያ ህዝብ የሚያሳዝነኝ የለም” የሚል ሊቅ ብዙ ነው። ህዝቡ እንዲህ ማድረግ አለበት መነሳት አለበት ማወቅ አለበት የሚለው ብዙ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ራሱን ጨምሮ እሱነቱን ከህዝብ ደምሮ እኛ እንዲህ ብናደርግ እኛ ይህን ብንከተል ብነሳ መስዋዕትነት ብንከፍል የሚል አለ። ግን እውነቱን ነው ብሎ ማመን ይችግራል። ምክንያቱም ሁለት ሰዓት ተኩል ላይ ለተጠራ ቀጠሮና ፕሮግራም ስድስት ተኩል ላይ መጥቶ እኛ ኢትዮጵያውያንኮ ሰዓት አናከብርም ብሎ ራሱን በድፍረት ሲወቅስ እንደሚኖር ህዝብ ይሆንብናል። ይህን ሰው እንዳይወቁስት ራሱን አስቀድሞ ወቅሷልና ነጻ ነው። አንዳንድ ጊዜ ራሱን በእንዲህ ያለ ነጻነት የሞላ ኢትዮጵያዊ ህዝብ መኖሩ ውሸት ይሆን ወይንስ እውነት ብሎ ማሰብ ጊዜ ይወስዳል። ሀበሻ ሰዓት አያከብርም ይባላል ውሸት ነው – ሀበሻ የማያከብረው ሀበሻን ነው። ባይሆንማ ይህ ሁሉ ሀበሻ ስርቶ አያድርም ነበር ። ሥራ አክባሪ ታታሪ ነው እየተባለ የተመስከረለት ሰው ሰዓት አያከብርም አይባልም። ወይም ከሁለት አንዱ ውሸት ነው።

የፖለቲካው ውሸትማ እልፍ ነው። አምስት ቅንጅቶች- ቅንጅት አንድ ነው ይላሉ። እነብርቱካን ሊቀመንበራችን ኃይሉ ሻውል ናቸው ይላሉ። እነ ኃይሉ ሻውል እነብርቱካን ወያኔ ናቸው ማለት ይዳዳቸዋል። ዶ/ር ብርሃኑ ወያኔ ናቸው ብለው ምለው የነገሩንም ነበሩ። ዛሬ ደግሞ ክተት አውጀዋልና የብርሃኑ ፀረ ወያኔነት መጠን አልፏል እየተባልን ነው። አንዳቸው ወይም ሁላቸውም ዋሽተዋል። ግን ምንም አይደለም የኛ ናቸውና ቢዋሹ መልካም ነው። ልክ ዳቦ ቢወደድም መብራትና ውሃ ቢጠፉም ጤፍ ብርቅ ቢሆንም ሥጋ እያማረ ቢቀርም ምንም አይደለም ኢኮኖሚው አድጓል እንደሚሉት መሆኑ ነው። የሚደግፉትም የሚቃወሙትም ሰው ሁሉ ውሸት ከሆነ ግን መፍትሄው ምንድነው? ያለው ምርጫ የገዛ ሀሳብና አቋምን መመርመር ነው። ምንድነው? ሰው ሊከዳ ይችላል መርምረው የያዙት ሀሳብ ግን አይከዳም። ራስን ሳይዋሹ፣ ጥያቄ ሳይሸሹ፣ ከመንጋ ሳጥን ወጥተው ያለውን ሁሉ ቢያዩት ብዙ ነገር ውሸት ነው። እውነት ስምምነት አይደለም።

ሌላውን ዜጋ ያልጨመረ ግልጽ አድልዎና ስግብግብነት የነገሠባቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የራሳቸውን ኢትዮጵያ ነጥለው የሠሩ ሁሉ ኢትዮጵያ እንደዚህ የተጎማመደች እንደ አካባቢያችሁና አስተሳሰባችሁ የጠበበች አይደለችም ሲባሉ ኢትዮጵያዊ አይደላችሁም ተባልን ብለው ቡራ ከረዩ ሲሉ ማለት የተፈለገው ነገር ወይ ገብቷቸዋል ወይም አልገባቸውም። ወይም ደግሞ ኢትዮጵያዊ የሚባለው ነገር በቃ እንደሱ ነው ፤ ወይ ይገባል ወይ አይገባም። ሁሉም ኢትዮጵያን የሚያያት አካባቢውን ብቻ ካወቀች ነው። ድርጅቱን እምነቱን ቋንቋውን ብቻ ከተከተለች የራሴ የሚለውን ሰው ብቻ ባለሥልጣን ከሾመች ብቻ ይሆን እንዴ ያሰኛል። ይቺን ሁሉም የሚያውቃትን ኢትዮጵያ ለማምጣት እንዴት ይቻላል? ወይስ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ገና በሂደት ላይ ያለች ተገንብታ ያላለቀች ውብ ጅምር ነች። ወይስ ዘመንተኞች እንደሚሏት ኢትዮጵያ መጀመር የሌለባት አስቀያሚ ነገር ነበረች። “በኃይል ሳይሆን በመከባበርና በመፈቃቀር የተገነባች ኢትዮጵያ!” የሚል ነገር ከሰማችሁ “አስቀያሚቷ ኢትዮጵያ” ያስቀየመቻቸው መሆናቸውን አለመዘንጋት ነው። ችግሩ ግን በተራቸው እነሱም በኃይል እንጂ በመከባበርና መፈቃቀር ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን መገንባት አልቻሉም። የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት ያሉት ነገር ተረት መሆኑን ሥልጣን ሲይዙት አይተውታል። ወይም ደግሞ ቀድሞውንም እንደዚያ የሚባል ነገር አለመኖሩና ውሸት መሆኑን አሳምረው ያውቁታል። ለብሄረሰባችንም ሆነ ለአካባቢያችን ከዚህ በላይ ተስማሚ ጊዜ የለም ማለታቸው በግልጽ ማስታወቁ ብቻ ሳይሆን እነሱም በተራቸው አስቀያሚቷን ኢትዮጵያ እየፈጠሩ መሆናቸውን አያስተውሉትም። ኢትዮጵያ ከመቸውም ጊዜ በላይ ሰላማዊትና በእድገት ጎዳና ላይ እየተጓዘች ያለች አገር መሆንዋን ሲሰብኩ ቅጥፈት የሚሆነውም ለዚህ ነው።

እነሱን ከገለበጥን ወይም ከተገለበጡልን በኋላ ሰለምንገነባት ኢትዮጵያ ያለንም ሀሳብ ተመሳሳይ መሆኑን ደግሞ ከወዲሁ ካልመረመርን ኢትዮጵያ ላንዱ አምራ ላንዱ ማስቀየሟን አታቆምም። ኢትዮጵያ ዝምብላ የምትነገር የቃል ተረት ወይም ምቾትና እንግልት የሚተረጉማት መሆን የለባትም። በሌላ አገላለጽ ለአቶ መለስ ዜናዊ ዛሬ ጊዜው ተመችቷልና ባንዲራው ጨርቅ ላይሆን ይችላል። “ባንዲራችንን እንዴት ጨርቅ ይሉታል?” ይል የነበረው ደግሞ በተራው ዛሬ አቶ መለስን መልሶ፣ “ችግሩ ከጨርቁ አይደለም ከጨርቁ በስተጀርባ ያለው ነገር ነው” ቢላቸው አቶ መለስም ሆኑ ደጋፊዎቻቸው ትላንት ያሉትን መዘንጋት የለባቸውም። ለካ ይህም አለ ተብሎ ደግሞ በስተምእራብ ሱዳን መሬት ተቆረሰ እያሉ እየጩኹ ፣ በምስራቅ ኢትዮጵያ ከሚገነጠለው ኦጋዴን ጋር ተሰልፌ ልዋጋ ማለትም አስቂኝ ጨዋታ ነው። አገርም ባንዲራም ኢትዮጵያዊነትም የቃላት ብቻ እንዳይሆኑ ይህን ሁሉ አዟዙሮ መጠየቅና ማመዛዘን ይገባል። (ዘኢትዮጵያ)