አባማቶጵያ!

ኦባማ ከምንም ነገር በፊት አንደበታቸው ይጣፍጣል። ስለሆነም በወጣቱ ብቻ ሳይሆን በሁሉ ሰው ጆሮ ፖለቲካን በቀላሉ ሊያንቆረቁሩ ችለዋል። ንግግራቸው እንደኛ አገር የቸከ የመነቸከ ከዓመት ዓመት የማይለወጥ አይደለም። የኛ ንግግር አብዮት- ጎሳ -ብሄር ብሄረሰብ- ነፍጠኞች- ፀረ ህዝቦች… በሚሉት ገፍታሪ ቃላት የተሞላ ይመስላል። እውነት ነው አሜሪካና ኢትዮጵያ ይለያያሉ። አሜሪካውያን ያን ያህል የሰነበተ ሥር የሰደደ ችግር የላቸውም። ከተቸገሩበት የታደሉት ነገር ይበልጣል። እንደዚያ ባለ አገር የጣፈጠ ነገር ቢወራም ለጆሮ ይጥማል።

ይህም ሆኖ ግን በአሜሪካ መንገዱ ሁሉ አልጋ ባልጋ ነው ማለት አይደለም። እንደ ጆን መኬይን ደጋፊ ዓይነቶቹ ወግ አጥባቂዎች አሁንም አሉ። መኬይን ሁሉን ነገር እንፋለም( fight) ማለታቸው መንገዳቸውን ሁሉ የትግል አድርገው በመውሰዳቸው ነው። ይህ ከኛ ሰዎች ጋር ሳያመሳስላቸው አይቀርም። ይሁን እንጂ መኬይንና ደጋፊዎቻቸው ሁሉንም ነገር እንደትግል ቢወስዱም ሁሉንም ነገር እንደጠላት አልተመለከቱም። ኦባማ ከጠላቶቻችን ጋር የሚውል ሰው ነው፣ ይህ ሰው አሜሪካን ይወዳል ወይስ አይወድም ? መሳይ ጥያቄ ተነስቷል። አረብ ነው፣ እስላም ነው ሁሉ ተብሏል። “ይህ ሰው ኢትዮጵያዊ ነው ወይስ አይደለም?” ዓይነት መሆኑ ነው። ግን ምርጫው ሲያልፍ ያለፈ አባባል ሆኗል። በመጨረሻው ላይ መኬይንም ሳራ ፔለንም ኦባማ ፕሬዚዳንታችን ነው ብለዋል። የኛ አገር የጠላትነት ጨዋታ ግን ማለቂያ የለውም። አሜሪካ አንድ ነገር አመኑበትም አላመኑበትም ደገፉትም አልደገፉትም ብዙ ነገር ማለቂያ አለው። ይሄድ ይሄድና አንድ ቦታ ይቋጫል። አንዱ የጨዋታ ዓይነት አልቆ ሌላኛው ይቀጥላል። መራመድ መሄድ መንቀሳቅስ ይታያል። እኛ አገር ግን ሁሌም የምናየው አንድ የተቸከለ ነገር ነው።

መንግሥትም ተቃዋሚም የሚያዉቁትና የሚታወቁበት አንድ ነገር አለ። “ዴሞክራሲና ሰላም ለማረጋገጥ፣ ህዝባዊ አንድነትን ለማስፈን፣ ብልጽግናን ለማምጣት” በሚል በጭንቅላታቸው የሚያካሂዱት ቋሚ አብዮት አለ። አብዮታችን ቋሚ ነው። “ታጋይ ቢሞት ትግል አይሞትም!” ይባላል። ትግል ዘለዓለማዊ ሆኖብናል። ባለሥልጣኖቻችን ለዘለዓለም ሥልጣን ላይ መቆየት የሚፈልጉት ሥልጣን ስለወደዱ ብቻ ሳይሆን በነሱ ዕድሜ የሚያልቅ ትግል አለመኖሩ ስለሚሰማቸውም ጭምር ሊሆን ይችላል። ውረዱ እስኪ ደግሞ ለሌላ ሰው ልቀቁ ሲባሉ እንዴ ትግሉን ለማን ትተን? ማን ተክቶን? መባሉ ለዚህ ነው። መለስን ማን ይተካቸዋል? የሚባል ጅልነት አለ። ይህን የጅል እምነት፣ ከፊሉ በቅጥፈት ቢይዘውም ከፊሉ ደግሞ በእምነት መያዙ ሀሰት አይደለም። የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪክ ድርጅቶችም ላይ እንደጉድ ተጎልተው በማይለወጥ የፖለቲካ ባህል ውስጥ የጎለቱን ሞልተዋል። “እኔኮ እንደ ሌሎቹ የራሴን ኑሮ መኖርና ማሳደድ አላቀተኝም” የሚሉ የዋሆች አሉ። አንዳንዴ ምናለበት እነዚህ ሰዎች ፖለቲካውን ትተው የራሳቸውን ኑሮ አርፈው ቢኖሩ ማለትን ያስመኛል። አልቻልኩም እስኪ ደግሞ እኔ ካቀተኝ ሌላው ይሞክረው ብሎ ነገር አይገባቸዋም። “እኔኮ ለኔ ሳይሆን ለሚቀጥለው ትውልድ ነው” ሲሉ ይገርማሉ። አጠገቡና በቅርቡ ላለ ትውልድ መሆን ያልቻለ ለትየኛውም ትውልድ አይሆንም። እንዲያውም ችግርን እንደ ውርስ እያስተላለፉ የሄዱት እንዲህ ዓይነቶቹ አስተሳሰቦች ናቸው። ላሁኑ ትውልድ የሠራ ለሚቀጥለው ትውልድ ይሠራል። አሜሪካውያንን ዛሬ ድረስ የጠቀማቸው የትላንቶቹ ለራሳቸው ሲሉ ትላንት ያወጡት ህግና ሥርዓት ነው። እንጂ የዛሬዎቹ ለዛሬ ብለው ዛሬ ያወጡት ህግ አይደለም። እንዲያውም ከዛሬዎቹ የበፊቱን ሊያፈርሱ እንዲመቻቸው አድርገው ሊቀለብሱ የሚታገሉ ይገኙባቸዋል። የሥልጣን ገደብን ተቀብለው ጊዜያቸው ሲደርስ የወረዱ ሰዎች ባይኖሩ ኖሮ ምርጫ አጭበርብረዋል የሚባሉት እንደቡሽ ዓይነቶች ሁሌም በተኙብን ነበር። ይህም ሆኖ ግን እነሱ እንኳ ከተሰጣቸው የጊዜ ገደብ አላለፉም። አዲስና የተሻለ ነገር ማውጣት ባይችሉ እንኳ የቀደመውን መልካም ነገር አክብረው መኖራቸው ብቻውን ያስከብራቸዋል።

እኛ አገር ግን ዴሞክራሲ በአንድ ጊዜ ሳይሆን በሂደት የሚመጣ ነውና ዝምበሉ ይባላል። የአጭር ጊዜ ሳይሆን የረጅም ጊዜ ሂደት ነው ይባላል። እኔ ሥልጣን ላይ ረጅም ጊዜ መቆየት አለብኝ እንደ ማለት ነው። ቡሽ ሥልጣን እየጣማቸው ሲለቁ፣ መኬይን እየቆጫቸው ሲያበቁ ማየቱ ትልቅ ትምህርት ሊሆነን ይገባል። ስለዚህ ትምህርትነቱ ከኦባማ ብቻ ሳይሆን ከበስተጀርባው ካለ ጠቅላላው ሥርዓትና ሂደቱ ነው። ኦባማ የዚህ የአሜሪካ መልካም ሥርዓት ባህልና ፖለቲካ ውጤት ተጠቃሚ እንጂ ፈጣሪ አይደሉም። የኦባማ ታሪካዊነት የፖለቲካ ሥርዓቱን ገዳቢዎችና አካላካዮች ሞግተው በአሸናፊነት ሥርዓቱን መጠቀማቸው ነው እንጂ የፖለቲካ ሥርዓቱን መፍጠራቸው አይደለም። ይህ ማለት ከኦባማ የምንማረው ነገር የለም ማለት ሳይሆን እንደኦባማ ዓይነቶቹን ሰዎች ሊያወጣ የሚያስችል ሥርዓትና ባህል መኖሩንም ለማሳየት ነው። አሜሪካ እንዲህ ያለች አገር ናት። ከኦባማ የምንማረውማ ሞልቷል!

እንደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆነ የፖለቲካ መሪዎች ሆነን ራሳችንን ብንወስድ የሚከተሉትን መማር እንችላለን። ለምሳሌ ህዝባዊ አደረጃጀትንና ለለውጥ ማነሳሳትን እንማራለን። እኛ ጠንካራ ድርጅት ፈጥሮ ህዝብ ማነሳሳት አልቻልንም። በገዛ ፈቃዱ ተገልብጦ የመጣልንንም ሆነ ራሳችን ያነሳሳነውን ህዝብ መጠቀም ያልቻሉ ድርጅቶችና መሪዎችን ያበቀልን ነን። ሆ ብሎ ብትን የሚል ጤዛ ስብስብ እንጂ ሳያቋርጥ የሚያንኳኳ ስብስብ የለንም። ከላይ ወደታች እንጂ እንደኦባማ ከታች ወደላይ የተዋቀረ ስብስብን የሚፈቅድ አደረጃጀት አልተከተልንም። የገንዘብን አስፍላጊነትና ወሳኝነትን እንደነገሩ እንጂ በሚገባ አልተነገዘብንም። ከኦባማ በስተጀርባ ላለው ገንዘብ መሰረቱ ብዛቱ ሳይሆን ያልተቋረጠ ምንጭ መዘርጋቱ ነው። የገንዘብን አስፈላጊነት መገንዘብ ብቻውን በቂ አለመሆኑን የኦባማና የዴሞክራቶች የምርጫ ዘመቻ አስተምሮናል።

ዴሞክራቶች የተነሱት፣ ኦባማ ያሽነፉት ኢኮኖሚው ስለወደቀ ብቻ አይደለም። ወይም አይ አሁንስ ሪፐብሊካኖች አልቆላቸዋል ብለው በመዝናናትና መዘነጋት እድል (“ነፋስ”) በሰጣቸው ፖለቲካ ተጠቅመው አይደለም። ሪፕብሊካኖች ስለደከሙ ሳይሆን እነሱም ስለጠነከሩ ነው። ህዝቡ ለውጥ ፈልጓል ብለው በመዘናጋት አልተመጻደቁም። መላው ዓለም ከበስተጀርባቸውተሰልፎ እያለ እንኳ እነሱ ግን ምንም እንዳልተፈጠረ ስጋትና ጭንቀት እንደገባቸው ነበሩ። አልጎርና ኬሪ ተዘናግተው ምን እንደሆኑ አይተዋል። እኛም አገር የሆነው እንደዚህ ነው። በህዝብ የተጠላ መንግሥት መኖሩ፣ የተንኮታከተ ኢኮኖሚ መታየቱ፣ ረሀብ መከሰቱ ያጽናናቸው ሁሉ “አሁንማ አልቆለታል” በሚል መዝናናት ንቀት አሳድረው ይታያሉ። የአገር ድህነት አንድ ነገር፣ የመንግስት ወይም የገዢው ፓርቲ ሀብት ደግሞ ሌላ ነገር መሆኑን ቢገነዘቡም አቅማቸውን ከዚያ አንጻር ፈትሽው መንቀሳቀስ አልቻሉም። ከአራትና አስምት ሰዓት ዲስኩር በኋላ በየአዳራሹ ገንዘብ ለመሰብሰብ ይጣጣራሉ። ከዚያች የሰበስቧት ለጽህፈት ቤትና ለስልክ መደወያ፣ ለሆቴልና ትራንስፖርት ከበቃቻቸው፣ የዓለም መጨረሻ የሆነ ይመስላቸዋል። እሷን ቋጥረው ቢሊየነሩን ፓርቲና ቢሊየነሮቹን አጋሮቹን አሸንፈው ሥልጣን ለመያዝ ይሽቀዳደማሉ። ያሸነፉትን ምርጫ በቀላሉ ሊጠነቁ እንደሚችሉ ቢገነዘቡም ከዚያ በኋላ ስላለው ነገር ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ አይዘጋጁም። የሀሳብ አለመግባባት ብቻ ሳይሆን ድህነትና ባዶ ካዝናም ሊበታትን ይችላል። መናናቅ የተፈጠረው ማንም ከማንም ተለይቶ ቢሄድ የሚጎዳበት ነገር አለመኖሩን ከመገንዘብ ጭምር ነው። የፈለገው ሰው የፈለገውን የፖለቲካ ድርጅት ለቆ ቢሄድ ደመወዝ አይቀርበትም። ብዙ ተከታዮችና አባላት ስለሌሉት አያሰጋውም። አቅም ኖሮት ተጽእኖ ሊያመጣ የሚችል የረባ ሚዲያ ስለልተፈጠረ ዝናው ብዙም አይወርድበትም። ምክንያቱም ይህን ሁሉ ተጽእኖ ለማሳደር ገንዘብ ያስፈልጋል። በዚያ ላይ አስር ብር አዋጥቶ 10ሺ ብር በሉኝ የሚል ከሳሽና ወቃሽ በበዛበት ሁኔታ ከገዛ ኪስ እየከፈሉ መታገልም ያደክማል። ይህ ሁሉ ሆኖ ብዙዎችን የሚያጽናናቸው ትግል ውስጥ መቆየትና ከአብዮቱ አለመለየታቸው ነው። ውጤት ማምጣት አለማምጣት ፖለቲከኞቻችንን የሚያስጨንቅ ህመም የሆነ አይመስልም። ኦባማ በአጭር ጊዜ ምን ሊሠራ እንደሚቻል አሳይተዋል።

የኛ ድርጅቶች ምን እየጠበቁ ተከታዮቻቸው ምን ተስፋ እያደረጉ እንደሆነ የሚታወቅ ነገር የለም። ከዚህ ሁሉ ውድቀትና መነሳት በኋላ ዛሬም የሚዘፈነው ያው ዘፈን ነው። ዛሬም የሚታረሰው በአሮጌ በሬ ነው። በሌላም በኩል ሥርዓቱን ከመለወጥ ሥርዓቱን እስከነ መጥፎ ጠረኑ አቅፎ መተኛት እየተሰበከ ነው። የሰላም ትርጉሙ ባርነት ሆኗል። የትግልም ትርጉሙ ባዶ ቀረርቶ መስሏል። በዚህ መካከል ሆኖ ከኦባማ ምን እንማራለን ማለት ይቸግር ይሆናል።

ቢሆንም ቢሆንም ከዘመን ጋር አብሮ መለወጥን፣ ቴክኖሎጂን መጠቀምን፣ ደጋግሞ ማንኳኳትን፣ ከታች ወደላይ መደራጀትን፣ በጎ ፈቃደኝነትን፣ ህዝባዊ ተሳትፎን ፣ቀናነትን፣ ዲፕሎማሲን፣ መነጋገርን፣ ንትርክን ሳይሆን ክርክርክን፣አፍ መካፈትን ሳይሆን ጆሮ መከፋፈትን፣ ዝልፊያን ሳይሆን መከባበርን፣ ክፍፍልን ሳይሆን ህብረ ሰውነትን፣ አንድ ሁለት ተብሎ የሚቆጠር ፍሬ ነገርን፣ ማውገዝን ሳይሆን አማራጭ ማቅረብን፣ ወጣቱን! ወጣቱን! ወጣቱን! ያለፈውን አሮጌውንና ችክ ምንችክ የሚለውን ሳይሆን የወደፊቱን፣ ለውጥንና አዲስ ነገርን መስበክ ብቻ ሳይሆን አዲስና የተለወጠ ሀሳብና አሰራርን መማር እንችላለን። ኦባማ ያመጡት አዲስ አስተሳሰብ ላይኖር ይችላል። ያሳዩን አዲስ መንገድ ግን አለ። አስደናቂውም ነገር ጥቁር ፕሬዘዳንት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ፕሬዚዳንት ለመሆን የተከሄደበት መንገድ ነው። አሜሪካና ኦባማ የሄዱበትን መንገድና በመንገዳቸውም ያሳዩንን መንገድ በምሳሌነት ወስዶ ከራስ አገርና ፖለቲካ ጋር አዋህዶ መጓዝ ይጠቅማል። አሜሪካ መኖር ብቻውን በቂ አይደለም። ኢትዮጵያና አሜሪካ የሚገናኙበትም ሆነ የሚተላለፉበት መንገድ ስለማይጠፋ አሜሪካ የምትሄድበትንም ሆነ እስካሁን የመጣችበትን መንገድ ማየት ይጠቅማል። ይህን ታሪካዊ ጊዜ እንደ ዓለም ዋንጫ ጨዋታ ኦባንም እንደ ኮከብ ተጨዋጭ ተመልክተን እንዳቀር ያሰጋል። ከራሳችን ህይወትና አገር ጋር ካላላያዝነው ፈንጠዝያውና ዝላዩ ብራዚልኮ አሸነፈ እንደማለት ሆኖ ይቀራል። (ዘኢትዮጵያ)