ሥራ የለም ታክስ የለም- የበጀት ጉድለት ቀውስ አስቸግሯል


ቢሆንም ጠላት ደስ አይበለው!

መንግሥት በዚህ ዓመት የ54 ቢልየን ብር በጀት አውጥቷል። ለዚህ በጀትም 30 ቢልየን የሚሆነውን የማገኘው ከታክስ ከምሰበስበው ገንዘብ ነው ብሎ አቅዷል። ከግማሽ ዓመት በላይ በሆነው ጊዜ ውስጥ እስካሁን የሰበሰበው ግን 12 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው። በቀሪው የበጀት ዓመት መዝጊያ ሁለትና ሶስት ወራት ውስጥ ቀሪውን 18 ቢሊዮን ብር ይሰበስባል ማለት የማይመስል መሆኑ ቢገባውም ነጋዴዎች ሰብስቦ ሰሞኑን ታክስ አምጡ እንጂ እያላቸው ነው። በተለይም ታክስ ባለመክፈል ያስቸገሩ ያላቸውን 55 የሚደርሱ ታላላቅ የቢዝነስ ድርጅቶችን ለይቶ በማውጣት ወጥሮ እያስጨነቃቸው መሆኑ ተሰምቷል። እነዚህ እያንዳንዳቸው ከ4ሚሊዮን እስከ 10 ሚሊዮን ብር የታክስ ውዝፍ ያለባቸው መሆኑንም ገልጿል። ከባለሥልጣናት ጋር እይተሻረኩና የማጭበርበሪያ ዘዴዎችን ሁሉ እየተጠቀሙ መክፈል የሚገባቸውን ያህል የማይከፍሉም ሆኑት ጨርሶውንም እንዲታለፉ የሚደረጉት በርካታ መሆናቸውም ያታወቃል። አሁን ደግሞ “ኢኮኖሚው ወድቆ የውጭ ምንዛሪ ጠፍቶ…” የሚለው ምክንያት ተጨምሯል። እውነትም ጠፍቷልና በአግባቡ መክፈል የሚችሉትም ሳይቀሩ እንግዲህ ከየት አምጣ ትለናለህ እያሉት መሆኑ እየተሰማ ነው። መንግሥት ግን የከፈላችሁትም ያልከፈላችሁትም የእያንዳናችሁን ፋይል እንደገና ማየት አለብኝና የወጪ ገቢ ሰነዶቻችሁን በአስቸኳይ ይዛችሁ ለዚህ ግዳጅ ወዳ ሰማራኻቸው ኦዲተሮቼ ቅረቡ የሚል አዋጅን በመመሪያ አስነግሯል። በሌላ በኩል ደግሞ ይህን የበጀት ጉድለት የውጭ መንግሥታትና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በ እርዳታና በብድር መልክ እንዲደጉሙት ዲፕሎማቶቹን አሰማርቷል። ውስጡ ይህን ሲመስል ውጪው ግን በኢኮኖሚው እድገት አሸብርቋል። ነገሩ ሁሉ ጠላት ደስ አይበለው ይመስላል።