ዳኛ፡- ታገል ጌታሁን
ከሣሽ፡- ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሣ – ጠ/ተስፋዬ ደረሰ
ተከሣሽ፡- የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሱፐር ኢንቴንደንት እቴነሽ መኮንን
መዝገቡ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው ተከሣሽ በ24/7/2001 ፅፎ ባቀረበው መልስ ላይ ያነሳቸው መቃወሚያዎች ላይ ብይን ለመስጠት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ግራ ቀኙ ያቀረቡትን ክርክር መርምረን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 245 መሠረት የሚከተለውን ብይን ፍርድ ቤቱ ሰጥቷል፡፡
ብይን
1/ ክሱ
ከሣሽ በጠበቃቸው አቶ ተስፋዬ ደረሰ በኩል በ2/7/2001 ፅፈው ባቀረቡት የተሻሻለ ክስ ተከሣሽ በከሣሽ ላይ የተሰጠን የእስራት ቅጣት ለማስፈፀም በሚል ከሣሽ በተከሣሽ ጥበቃ ስር እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ተከሣሽ ከሣሽን ለብቻቸው በማሰር የሠብአዊ ክብራቸው እንዲነካ አድርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከሣሽ ከእናታቸውና ልጃቸው በቀር በሌላ ዘመድ፣ ወዳጅና የህግ ባለሙያ እንዳይጐበኙ ተከሣሽ የክልከላ ድርጊት ፈፅሟል፡፡ ይህ ክልከላ እንዲነሣ ፍርድ ቤቱ ውሣኔ ይስጥልኝ በማለት አመልክተዋል፡፡
2/ መልሱ
ክሱ ለተከሣሽ እንዲደርስና መልስ እንዲያቀርብ ታዞ ተከሣሹ በ24/7/2001 ዓ.ም. ፅፎ በሱፐር ኢንቴንደንት እቴነሽ መኮንን በኩል ባቀረበው መልስ የሚከተሉትን መቃወሚያዎች አቅርቧል፡፡
ሀ/ አቶ ተስፋዬ ደረሰ ከከሣሽ የተሰጠው ውክልና ስለሌለ እንደ ከሣሽ ጠበቃ ሆኖ ክስ ማቅረብ አይችልም፡፡
ለ/ የእስረኞችን አያያዝ በተመለከተ ውሣኔ የሚሰጠው ተከሣሽ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች በዚህ የተከሣሽ ስልጣን ውስጥ ጣልቃ ገብተው ከሣሽ ያቀረቡትን ክስ ለማስተናገድ የሚችሉበት ሥልጣን የላቸውም፡፡
ሐ/ ከሣሽ አለኝ የሚሉትን ቅሬታ መጀመሪያ ማቅረብ የነበረባቸው ለታሰሩበት ክፍል ኃላፊ ነበር፡፡ ከዚህ በመቀጠል ደግሞ ከሣሽ ለሚገኙበት የማረሚያ ቤት ኃላፊ ነው፡፡ ከዚህም ውጤት ካላገኙ ነው የመጨረሻ ውሣኔ ለማግኘት ለተከሣሽ ማቅረብ የነበረባቸው፣ ከሣሽ ይህንን የአስተዳደራዊ መዋቅር ሰንሰለት ሳይከተሉ እና ተከሣሽ የመጨረሻ ውሣኔ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ሳያቀርቡ ነው ተከሣሽን በፍርድ ቤት የከሰሱት፡፡ ከሣሽ ከፍርድ ቤቱ ውጪ ያሉትን ቅሬታ ማቅረቢያ እድሎች ሳይጠቀሙ ያቀረቡት ክስ ውድቅ ሊደረግ ይገባል፡፡
መ/ ክሱ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 314 ላይ በተቀመጠው የተፋጠነ ስነስርዓት መታየት የሚችል አይደለም፡፡
ሠ/ ከሣሽ በተፋጠነ ስነስርዓት እንዲታይ ክሱን ማቅረብ አይችሉም እንጂ ይችላሉ የሚባል፣ ቢሆን እንኳን ተፈፀመብኝ የሚሉት ክልከላ ተደርጓል ከተባለበት ጊዜ አንስቶ ይህ ክስ እስከቀረበበት ጊዜ ድረስ ያለው ጊዜ ሲታሰብ 15 ቀን ስላለፈው ክሱን ማቅረብ አይችሉም ብሎ ተቃውሟል፡፡
3/ ትንታኔ
3.1. መቃወሚያ ቁጥር /ሀ/ ላይ
ከሣሽ ወ/ት እየሩሣለም ይልማ ገ/እግዚአብሔር ለተባሉ ግለሰብ በ18/1/98 በቁጥር 3150/1/98 የተፃፈ ውክልና ሰጥተዋል፡፡ በዚህ መሠረት የከሣሽ ወኪል የሆኑት ወ/ት እየሩሣሌም ይልማ ገ/እግዚአብሔር የውክልና ሥልጣናቸውን ተጠቅመው በ2/6/01 የተፃፈ የጥብቅና ውክልና ለአቶ ተስፋዬ ደማረሰ ዘውዴ ሰጥተዋል፡፡ በዚህ የውክልና ሠነድ ላይ አቶ ተስፋዬ ደረሠ ዘውዴ ከሣሽን ወክለው ክስ ማቅረብ እንዲችሉ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ይህ ለጠበቃው የተሰጠው የውክልና ሠነድ በሠነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 467/97 መሠረት በፅሁፍ ተደርጎ በሠነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ፅህፈት ቤት ማህተም የተረጋገጠ ነው፡፡ እንዲሁም የከሣሽ ጠበቃ በ24/06/00 የተደረገ የጥብቅና አገልግሎት ውል የከሣሽ ወኪል ከሆኑት ወ/ት እየሩሣለም ይልማ ጋር ሁለት ምስክሮች በተገኙበት ውል ፈፅመው የውሉን ኮፒ በማስረጃነት ከዚህ መዝገብ ጋር ተያይዞ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ከሣሽ በወኪላቸው አማካኝነት አቶ ተስፋዬ ደረሰን በጠበቃነት የወከሉ መሆኑን የውክልና ሠነዱና የጥብቅና ውሉ ስለሚያስረዳ አቶ ተስፋዬ ደረሠ ከሣሽን ወክለው ክስ ለማስቅረብ የሚያስችላቸውን ሙሉ ቅድመ ሁኔታ ያሟሉ በመሆኑ አቶ ተስፋዬ ደረሠ ከሣሽን ወክለው ክስ ለማቅረብ የሚችሉበት ውክልና የላቸውም ብሎ ተከሣሽ ያቀረበውን መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡
3.2. መቃወሚያ ቁጥር /ለ/ ላይ
ተከሣሽ ያቀረበው ሁለተኛው መቃወሚያ የእሥረኞችን አያያዝ አስመልክቶ የመጨረሻ ውሣኔ የሚሰጠው ተከሣሽ ነው፡፡ የእሥረኞችን አያያዝ አስመልክቶ ተከሣሽ በፍርድ ቤት አይከሰስም፣ ፍርድ ቤቶችም ጉዳዩን ካዩት ለተከሳሽ በህግ የተሰጠ ስልጣን ውስጥ ጣልቃ እንዲገቡ ይታያል፡፡ ስለሆነም ክሱ ውድቅ ሊደረግ ይገባል የሚል ነው፡፡
የከሣሽ ጠበቃ በዚህ የተከሳሽ መቃወሚያ ላይ በቃል ለችሎቱ በሰጡት አስተያየት መቃወሚያው በመንግሥት አካላት መሀል ያለውን የስልጣን ክፍፍል ፅንሰ ሀሳብ የሚጥስ ስለሆነ ውድቅ ይደረግልኝ ብለዋል፡፡
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግሥት የፌዴራል መንግሥቱ ሲቋቋም በሦስት ቅርንጫፎች ተከፋፍሏል፡፡ እነዚህም ህግ አውጪ፣ ህግ አስፈፃሚ እና ህግ ተርጓማ ናቸው፡፡ የመንግሥት አካላት በዚህ መልክ የተከፋፈሉት ህግን ማውጣት መፈፀምና መተርጎም በአንድ አካል ብቻ ቢሰራ ቡህተ. ሥልጣን ስለሚፈጠር ይህ አካል ህገ መንግሥቱን አክብሮ በህዝብ የተሰጠውን አደራ መወጣቱን ለመቆጣጠር ስለማያመች ነው፡፡
ሥልጣን በአንድ አካል ላይ ቢከማች ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ ለማስቀረት ሲባል የመንግሥት ስልጣን በሦስት እንዲከፈል ተደርጓል፡፡ እነዚህ ሦስት የመንግሥት አካላት የየራሳቸው የሥራ ድርሻ ያላቸው ቢሆንም እያንዳንዱ አካል የተሰጠውን ሥራ ለመሥራቱ አካላቱ እርስ በርሳቸው ይፈታተሻሉ ለምሳሌ የህግ አወጪው አካል ያወጣቸው ህጎች በትክክል ስለመፈፀማቸው ለማረጋገጥ የአስፈፃሚው አካል ኃላፊዎች በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 55/17 እና 18 መሠረት እየቀረቡ ሪፖርት እንዲያደርጉና አስፈላጊ የመሰለው ትዕዛዝ ለመስጠት የህግ አውጪው አካል ስልጣን ተሰቶታል፡፡ እንዲሁም ይህ የህግ አውጪ አካል የህግ ተርጓሚ የሆኑትን ዳኞች የስነ ምግባር ችግር ሲያገኝባቸው ከሹመታቸው እስከማንሳት ድረስ ውሳኔ ማሳለፍ ይችላል፡፡ የህግ አውጪው አካል የህግ አስፈፃሚውንና ተርጓሚውን አካል ከላይ በተባለው መልክ የሚቆጣጠር ሲሆን የህግ ተርጓሚው አካል ደግሞ የህገ መንግሥቱ አንቀፅ 37 በሚፈቅድለት መሠረት በፍርድ ቤት መታየት የሚችሉ ጉዳዮችን ለማዳኘት ይችላል፡፡ በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 78/1/ ላይ የዳኝነት አካል ነፃ እንደሆኑ ተደንግጓል፡፡ እንዲሁም በአንቀፅ 79/1/ ላይ ክርክሮች ላይ ዳኝነት የመስጠት ኃላፊነት የፍርድ ቤቶች መሆኑ ተደንግጓል፡፡ ተከሳሽ አንድ የመንግስት አካል እንደመሆኑ ህገ መንግስቱ ማክበር ማስከበር አለበት፡፡ ተከሳሽ ህገ መንግስቱን አክብሯል ሊባል የሚችለው ህገ መንግስቱን መሰረት አድርገው የወጡ ህጎችንም አክብሮ ሲሰራ ነው፡፡ ከሳሽ ያቀረቡት ክስ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 21 እና የሚኒስትርች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 138/99 ላይ የተቀመጡ መብቶችን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ተከሳሽ እነዚህን የእስረኞች መብቶች እንዲያስከብር በአዋጅ ቁጥር 365/95 ላይ ሀላፊነት ይሰጥበታል፡፡ ተከሳሽ እንደማንኛውም የመንግስት አካል ስራውን ግልጽነትና ተጠያቂነት በተመላበት መልክ ሊሰራ እንደሚገባ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 12 ይደነግጋል፡፡ በእርግጥ የእስረኞችን መብት የማስከበር ስራ የተከሳሽ ቢሆንም ተከሳሽ ይህንን ስራውን በአግባቡ ከውኗል ወይ? የሚለውን ግን በህግ አውጪና ተርጓሚው መፈተሸ ይችላል፡፡ በአጠቃለይ ስላለው የእስረኞች አያያዝ ለሀገሪቱ ህግ አውጪ የተከሳሽ ሀላፊዎች ሪፖርት ማቅረብ አለባቸው አንድ ታሳሪ ደግሞ በተናጠል መብቴ ይከበርልኝ የሚል ተከሳሽን የህግ ተርጓሚ ለሆነው ፍ/ቤት መክሰስ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ተከሳሽ ተጠያቂነትም ስላለበት ነው፡፡ ነፃ የሆነ ፍ/ቤት የተቋቋመበት አላማ ሁለት ነው፡፡ አንደኛው ግለሰቦች በመንግስት የህግ አስፈፃሚ አካል የእለት ተለት ስራ ውስጥ ጣልቃ እየገቡ ስራ አላሰራም እንዳይሉ ለመከላከል ግን፣ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በህገ መንግስቱ ላይ የተረጋገጡ የዜጎች መብቶች በማንም /ተከሳሽን ጨምሮ/ እንዳይጣሱና ከተጣሱ እንዲከበሩ ለማድረግ ነው፡፡ በአገራችን ህገ መንግስት አንቀጽ 8 ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የሉአላዊ ስልጣን ባለቤት የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች መሆናው ተረጋግጧል፡፡
ይህ ማለት ትልቁ የሥልጣን ባለቤት ተከሣሽ ሣይሆን ህዝቡ ነው ማለት ነው፡፡ የህዝቡ ሉአላዊነት የሚገለፀው ደግሞ በሕገ መንግስቱ ነው፡፡ በሃገሪቱ ሕጎች ላይ የተቀመጡ መብቶች ስለመከበራቸው ፍ/ቤቱ ዘብ ስለሆነ ቅሬታዎችን ማስተናገድ አለበት፡፡ ተከሣሽ የነበረው በአገሪቱ ያለው ሉአላዊ ስልጣን ባለቤት ሕዝቡ እንጂ ተከሣሹ ባለመሆኑ ተከሣሽ ሌሎቹ የመንግስት አካላት እንደሚከሰሱት ሁሉ እርሱም በፍ/ቤት ሊከሰሥ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ሕገ መንግስቱ በከሣሽ ላይ የጣለው የተጠያቂነት መርህ መገለጫ ነው፡፡ ሕዝብ ለተከሣሽ የሰጠውን ሃላፊነት የዳኝነት አካል የሆነው ፍ/ቤት የመቆጣጠር ሥልጣን አለው፡፡ ተከሣሽ እንዳለው በፍ/ቤት የማይከሰስ ቢሆን ኖሮ የህግ የበላይነት መከበርና የሥልጣን ክፍፍል አላማ ጥያቄ ውስጥ ይወድቁ ነበር፡፡ ይህ ፍ/ቤት ሕዝብ የጣለበትን ሀቅን፤ ምክንያትንና ፍትህን የማስፈን አደራውን መወጣት የሚችለው መብቴ ተጣሰ የሚል ግለሰብን ቅሬታ አዳምጦ ለፍትህ ጥያቄው ምላሽ ሲሰጥ ነው፡፡ ስለሆነም በሕገ መንግስቱ፤ በአዋጆችና በደንቦች ላይ የሰፈሩ መብቶችን መከበር የተመለከቱ ክሶች በተከሣሹ ላይ ሲቀርቡ ሀገሪቱ የሕገ መንግስታዊ ሥርአት ባለቤት እንደመሆኗ መጠን አንዱ የሕገ መንንግስታዊ ሥርአት መገለጫ ተከሣሽ በፍ/ቤት መከሰስ መቻሉ በመሆኑ ፍ/ቤቱ የቀረበውን ክስ ማየት መቻል አለበት፡፡
በልዩ ህጎች ሥልጣኑ የፍ/ቤቶች አይደለም፡፡ ተብሎ ለሌላ የዳኝነት አካል እስካልተሰጠ ድረስ እንደተከሣሽ ያሉት የሕግ አስፈፃሚ አካላት ሲከሰሱ ጉዳዩ በፍ/ቤት መታየት ይችላል፡፡ ይህ ፍ/ቤት የንብረት መብቶችን ለማስከበር በመንግስት አካላት ላይ ክስ ሲቀርብ እንደሚመለከተው ሁሉ ከሣሽ ያቀረቡትን ከንብረት መብት የተሸለ ዋጋ ያለውን ሰብአዊ መብት ለማስከበር የሚቀርብ ክስን ማየት መቻል ይኖርበታል፡፡
ተከሣሽ የሕግ አስፈፃሚው አካል እንደመሆኑ በሕግ የተሰጡትን ሥልጣንና ሃላፊነት ያለማንም ጣልቃገብ ሊሰራ ይገባል፡፡ ተከሣሽ በፍርድ ቤቱ ሥራ ጣልቃ እንደማይገባው ሁሉ ፍ/ቤቱም በተከሣሽ የውስጥ ሥራ ጣልቃ መግባት አይችልም፡፡ ተከሣሽ ባቀረበው መቃወሚያ ላይ ፍ/ቤት በእኔ ሥልጣን ውስጥ ጣልቃ መግባት አይችልም ብሏል፡፡ ጣልቃ መግባት ከቃሉ እንደምረዳው አንድ አካል በሌላ አካል ስራ ወስጥ ገብቶ ሲገኝ የሚሰጥ ሥያሜ ነው፡፡ ፍ/ቤቱ በዚህ መዝገብ ውስጥ እየሰራ ያለው ግን በሕገ መንግስቱ የተሰጠውን የዳኝነት ሥራ ነው፡፡ ፍ/ቤቱ ይህን ተግባን ሲወጣ ለተከሣሽ የተተው በፍ/ቤት መታየት የማይችሉ non justiceable ጉዳዮችን ማየት ይችላል ማለት አይደለም፡፡ ይህንን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ከሣሽ ያቀረቡት ክስ ተከሣሽ በየእለቱ እኔ የምፈልገውን የምግብ አይነት እየሠራ ሊሰጠኝ ይገባል የሚል ቅንጦት አዘል ቢኖረው ኖሮ ለእስረኞች በየእለቱ የሚቀርቡ ምግቦችን ምንነት መወሠን ያለበት ተከሳሹ ስለሆነ ጉዳዩ በፍ/ቤት መታየት የሚችል አይሆንም፡፡ ነገር ግን ክሱ ተከሳሽ በህግ ላይ ምግብ የማቅረብ ግዴታ ተጥሎበት ሳለ ሙሉ በሙሉ ምግብ ከለከለኝ የሚል ቢሆን ተከሳሽ ምግብ ለእስረኞች የማቅረብ ግዴታ በህጉ ላይ ስለተጣበት ጉዳዩ በፍ/ቤት መታየት የሚችል justicabel matter ይሆናል፡፡ ከዚህ አንፃር ከሳሽ በዚህ መዝገብ ያቀረቡትን ክስ ስናየው የሰብአዊ ክብሬ ተጣሰ፣ የመጎብኘት መብቴ ተነካ የሚል ስለሆነና እነዚህ መብቶች ደግሞ በህገ መንግስቱ እና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንቡ ላይ ስለተቀመጡ የከሳሽ ክስ በፍ/ቤት መታየት የሚችል justiceable matter ይሆናል፡፡ በመሆኑም ለፍ/ቤቱ ያቀረበለት ክስ justicable matter በመሆኑ ይህንን ለመመልከት የህገ መንግሥቱ አንቀፅ 37 ስለሚፈቅድለት ፍ/ቤቱ በተከሳሽ ሥራ ውስጥ ጣልቃ ገብቷል ሊባል አይችልም፡፡
በአዋጅ ቁጥር 365/95 እና በደንብ ቁጥር 138/99 ላይ ተከሳሽ እስረኞች አስተዳደር መመሪያ ማውጣት እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ በዚህ መሰረት ተከሳሽ ያወጣቸው መመሪያዎች ካሉት እነዚህን መመሪያዎች አክብሮ ስራውን እየሰራ መሆኑን ፍ/ቤቱ መቆጣጠር ይችላል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ይህ መመሪያ ከእናት አዋጁና ደንቡ ጋር የሚቃረን መሆን አይችልም፡፡ የሚቃረን ከሆነ የበላይነት ያለው አዋጁና ደንቡ ስለሆነ መመሪያውን ፍ/ቤቱ ሥራ ላይ ላያውለው ይችላል፡፡ በመሆኑም ተከሳሽ ፍ/ቤቱ የእስረኞችን አያያዝ የሚመለከት ክስ የማየት ሥልጣን የለውም ብሎ ያቀረበው መቃወሚያ ከላይ ባብራራነው ምክንያት መሠረት ውድቅ ተደርጓል፡፡
3. መቃወሚያ ቁጥር “ሐ” ላይ
ተከሳሽ ያቀረበው ሶስተኛ መቃወሚያ ክሱ የአስተዳደር ውሳኔ ክለሳን የሚመለከት እንደመሆኑ ከሳሽ ወደ ፍ/ቤት ክስ ከማቅረባቸው በፊት ከፍ/ቤት ውጪ ያሉትን ቅሬታ ማቅረቢያ መንገዶች ተጠቅመው ጉዳዩን ለተከሳሽ ስላላቀረቡ ይህ እድል ተሟጦ ሳያልቅ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ማየት አይችልም የሚል ነው፡፡ ለዚህ መቃወሚያ የከሣሽ ጠበቃ በችሎት በሰጡት አስተያየት ከሣሽ የሚገኙት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ይህ ማረሚያ ቤት በተከሣሽ ስር የሚተዳደር ተቋም ነው፡፡ ከሣሽ ላይ የእስር ቤቱ የፈፀመባት ክልከላና የመብት ጥሰት በተመለከተ ሀላፊነቱ የእስር ቤቱ የበላይ ተከሣሽ ነው፡፡ ስለሆነም ቃሊቲ ያለው እስር ቤት የራሱ የሕግ ሰውነት ስለሌለው የሚከሰሰው ተከሣሽ ነው በሕግ የተቀመጠ የቅሬታ ማቅረቢያ መድረክ በተከሣሽ መስሪያ ቤት ውስጥ ስለሌለ በቀጥታ ተከሣሽን በፍ/ቤት መክሰስ እንችላለን፡፡ ተከሣሽም ቢሆን በከሣሽ ላይ የሰብዓዊ መብት በደል የተፈጸመ መሆኑን ክሱን ከመጥሪያ ጋር ስንሰጠው አውቋል፡፡ ክሱ ከደረሰው ጊዜ ጀምሮ 14 ቀናት አልፈዋል በመሆኑም በዚህ ጊዜ ውስጥ ተገቢን ማጣራት አድርጎ ስለጉዳዩ ተገቢውን ነገር ማድረግ ይችል ነበር ይህንን አላደረገውም ስለሆነም ክርክሩ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡ የተከሣሽ ወኪል ሱፐር ኢንቴንደንት እቴነሽ መኮንን በዚህ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቀው ስለጉዳዩ የምናውቀው ነገር የለም እያጣራን ነው የአ.አ ማረሚያ ቤትን ጠይቀን ምላሽ አልሰጠንም ብለዋል፡፡
በከሣሽ የቀረበው ክስ የተከሣሽ አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲከለስ የሚጠይቅ ነው፡፡ የአስተዳደራዊ ውሣኔ ክለሣ /administrative review/ ክስ መቅረብ የሚችለው ከፍ/ቤቱ ውጪ ያሉ የቅሬታ ማቅረቢያ እድሎችን ከሣሽ አሟጦ ከተጠቀመ በኋላ ነው በሀገራችን ሕጎች ውስጥ አንድ እስረኛ ተፈፀመብኝ የሚለውን በደል ማቅረብ የሚችልበት ከፍ/ቤት ውጪ ያለ የዳኝነት ሰጪ አካል የለም፡፡ ተከሣሽን ባቋቋመው አ/ቁ 315/95 ላይም እስረኞች ቅሬታ የሚያቀርቡበት ልዩ የዳኝነት አካል የለም፡፡ ይህ ፍ/ቤት የሚቀርብለትን ክሶች በሌላ አካል መታየት ያለባቸው ናቸው ብሎ መመለስ የሚችለው በሕግ ለሌላ የዳኝነት አካል የተሰጠን ጉዳይ ነው፡፡ ከሣሽ ያቀረቡትን ክስ ለማየት የተቋቋመ የዳኝነት አካል የለም፡፡ እንዲሁም የተከሣሽ ወኪል በችሎት ቀርበው ስለጉዳዩ አናውቅም ነበር ቢሉም ክሱ ደርሷቸው መልስ እስኪሰጡ ድረስ 14 ቀናት ጊዜ ነበራቸው፡፡ ይህ ጊዜ ደግሞ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኙትን የከሣሽን የአስተሣሰር ሁኔታ ለማጣራትና የመጨረሻ ውሣኑ ለመስጠት በቂ ጊዜ ነው፡፡ ተከሣሽ ግን እነዚህ 14 ቀናት በዝምታ አልፎታል፡፡ ይህም ማለት በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሣኔ በዝምታ እንደሰጠ ያስቆጥረዋል፡፡ በመሆኑም ከላይ በተብራሩት ምክንያቶች ተከሣሽ ያቀረበውን 3ኛ መቃወሚያ ፍ/ቤቱ ውድቅ አድርጎታል፡፡
3.4 መቃወሚያ ቁጥር መ ላይ ተከሣሽ ያቀረበው አራተኛ መቃወሚያ ክሱ በተፋጠነ ሥነ ሥርዓት መታየት አይችልም ከሣሽ በፍ/ብ/ስ/ስህ/ቁ 302 መሠረት ቃለመሀላ አላቀረቡም የሚል ነው፡፡
ከሣሽ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 302 መሠረት ቃለመሀላ አቅርበው በመዝገቡ ውስጥ ይገኛል ስለሆነም ቃለመሀላ አልተደረገም ብሎ ተከሣሽ ያቀረበው መቃወሚያ ታልፏል
በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 314 መሠረት በተፋጠነ ስነስርዓት እንዲታዩ የሚቀርቡት ጉዳዮች የመንግስት አካላት ክልከላ የሚፈጽሙባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ በዚህ አንቀፅ ላይ ከተዘረዘሩት ክልከላዎች ውስጥ ጋብቻ ከማድረግ መከልከል አንዱ ነው፡፡ ይህ አንቀፅ የክልከላ አይነቶችን ዘርዝሮ ጨርሶ አይዘጋም /Open ended/ ነው፡፡ ጋብቻን ከማድረግ አንድን ሰው ሲከላከል የሚነካበት ጋብቻን የመፈጸም የተፈጥሮ መብት አለ፡፡ በመሆኑም በዚህ አንቀጽ መሠረት መብቶች ላይ የሚፈጸሙ ክልከላዎች ይቀርባሉ ማለት ነው፡፡ ከሣሽ ያቀረቡት ክስም ከመብት ጋር በተያያዘ ክልከላ ተፈጸመብኝ የሚል ነው፡፡ መብት ላይ የተደረገ ክልከላ ከሆነ ደግሞ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 314 መሠረት በተፋጠነ ስነስርዓት መቅረብ ስለሚችል የተከሳሽ መቃወሚያ ውድቅ ተደርጓል፡፡
3.5 መቃወሚያ ቁጥር “ሠ” ላይ
ተከሳሽ ያቀረበው የመጨረሻ መቃወሚያ ክሱ ክልከላ ተፈጸመ ከተባለበት እለት 15 ቀን በኋላ ስላቀረበ ክስ ማቅረቢያው ጊዜ አልፏል የሚል ነው፡፡
ከሳሽ በፍ/ቤቱ አሻሽለው እንዲያቀርቡ በታዘዙት መሠረት በ2/7/01 የተጻፈ ክስ አቅርበዋል፡፡ በዚህ ክስ ላይ ክልከላው የካቲት 22 ድረስ እንደተፈጸመ ገልጸዋል፡፡ ከሣሽ ይህንን መዝገብ የከፈቱት ደግሞ በ27/6/01 ነው፡፡ ከዚህ ቀን ወደኋላ 15 ቀናት ሲቆጠሩ ከሳሽ ከ13/06/01 ጀምሮ ተፈጸመብኝ የሚሉትን ክልከላ እስከ 06/7/01 ድረስ ክስ ሊያቀርቡበት ይችላሉ፡፡ ክሡን ደግሞ ከ6/7/01 በፊት ነው ያቀረቡት፡፡ በመሆኑም ከሳሽ ክልከላ ተፈጸመብኝ ካሉት ቀን በኋላ ባሉት 15 ቀናት ውስጥ ክሱን ስላቀረቡ 15 ቀናት አልፈዋል ብሎ ተከሳሽ ያቀረበውን መቃወሚያ ፍ/ቤቱ ውድቅ አድርጎታል፡፡
ፍርድ
ከሳሽ ያቀረቡት ክስ ለብቻዬ እንድታሰር ተደርጌ የሰብአዊ ክብሬ ተነካ እና በቅርብ ወዳጆቼ እና ጠበቃዬ የመጎብኘት መብቴን ተከልክያለሁ እንዲከበሩ ውሳኔ ይሰጥልኝ የሚል ነው፡፡
ተከሳሽ በሰጠው መልስ ላይ ከሳሽ በክሱ ላይ የተዘረዘሩትን ድርጊት አልፈጸምኩም ብሎ አልካደም፡፡ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 234 መሠረት ተከሳሽ መልስ ሲሰጥ በግልጽ ካልካደ በክሱ ላይ የተዘረዘረውን ነገር እንዳመነ ያስቆጥርበታል፡፡ ተከሳሽ በሰጠው መልስ ከሳሽ ከእናቷና ልጇ ውጪ ባሉ ዘመዶቿና ጓደኞቿ ለምን መጎብኘት እንደሌለባት ምክንያቱን አቅርቦም አልተከራከረም፡፡ እስረኞች ምንም እንኳ በፍርድ የተመሰከረላቸው የሕዝቡ ጠላቶች /Judicially certified enemies of the public/ ቢሆኑም የመሠረታዊ መብቶች ባለቤቶች ናቸው፡፡ የህገመንግስቱ አንቀጽ 21 እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 138/99 አንቀጽ 13 እስረኞች በቅርብ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው እንዲሁም ሐኪም፣ የሕግ ባለሙያና የሀይማኖት አባት የመጎብኘት እንዲሁም ከሌሎች እስረኞች ጋር በእኩል የመታየት መብት እንዳላቸው ይደነግጋሉ፡፡ ይህ የሆነው የእስር ቅጣት አላማ እስረኛውን ማረም ማነጽ በመሆኑ ነው፡፡ ከሳሽ በክሳቸው ላይ እንደገለጹት ከእናታቸውና ልጃቸው ውጪ ሌላ ሰው እንዳይጎበኛቸው ክልከላ ተደርጎባቸዋል፡፡ ተከሳሽም ይህንን ክዶ ባለመከራከሩ የክሱ ይዘት እውነት እንደሆነ ፍ/ቤቱ ግንዛቤ ወስዷል፡፡ ተከሳሽ ከከሳሽ በቅርብ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው የማይጎበኙበት ምክንያት መኖሩን ተከሳሽ ስላልተከራከረ እና ከሳሽ በነዚህ ሰዎች የመጎብኘት መብት ስላላቸው ተከሳሽ በከሳሽ የመጎብኘት መብት ላይ የጣለውን ክልከላ ሊያነሳ ይገባል፡፡
በሌላ በኩል ከሳሽ ለብቻዬ መታሰሬ ሰብአዊ ክብሬን ይነካል ከሌሎች እስረኞች ጋር አብሬ እንድታሰር ይደረግልኝ ብለው የጠየቁ ቢሆንም አንድ እስረኛ ከሌሎች እስረኞች ጋር ተቀላቅሎ የመታሰር መብት በሕግ አልተረጋገጠለትም፡፡
ተከሳሽ እስረኞችን ሲያስተዳድር የተጣለበትን አንዱ ግዴታ እስረኞች እንዳያመልጡ መጠበቅ ነው፡፡ ተከሳሽ ከሳሽን ለብቻዋ ማሰሬ ለጥበቃ ያስፈልገኛል ብሎ ካመነ ይህንን ከማድረግ የሚከለክለው ነገር ስለሌለ ከሳሽ ብቻዬን በመታሰሬ ሰብአዊ ክብሬ ተነካ ብለው ያቀረቡትን ጥያቄ ፍ/ቤቱ ውድቅ አድርጎታል፡፡
ውሳኔ
1. ተከሳሽ ከሳሽን ከሌሎች እስረኞች ጋር እንዳይገናኙ አድርጎ ብቻቸውን የማሰር ስልጣን አለው ከሳሽ ብቻዬን በመታሰሬ የሰብአዊ ክብሬ ተነክቷል ብለው ያቀረቡትን ጥያቄ ፍ/ቤቱ ውድቅ አድርጎታል፡፡
2. ከሳሽ በቅርብ ጓደኞቻቸውና ዘመዶቻቸው እንዲሁም በሐኪም የሕግ ባለሙያና በሀይማኖት አባት የመጎብኘት መብት ባለቤት መሆናቸው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገመንግስት አንቀጽ 21 እና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 138/99 አንቀጽ 13 ላይ ስለተረጋገጠ ተከሳሽ ለሌሎች እስረኞች ይህንን በሚያከብርላቸው መልክ የከሳሽንም እነዚህ መብቶችን እንዲያከብር እና በከሳሽ ላይ የጣለው ክልከላ እንዲነሳ ተወስኗል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡
የዳኛ ….. ፊርማ ታገል ጌታሁን