የኢህአዴግ መንግሥት አምነስቲ ላይ መግለጫ አወጣ

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ነው።

የኢፌዲሪ መንግስት በሰብአዊ መብት ሽፋን በአገራችን ላይ የሚቀርቡ መሰረተ ቢስ ውንጀላዎችን በመከታተልና በማጣራት በተመረጠ አኳኋን ምላሽ እየሰጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ መሰረት የአሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰብአዊ መብት ቢሮ ላወጣው ሪፖርት ምላሽ የሰጠ መሆኑ ይታወሳል፡፡

በትላንትናው እለት ደግሞ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው ድርጅት በሽብር ሴራ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሰዎች ጋር የተያያዘ መግለጫ አውጥቷል፡፡

ድርጅቱ በዚህ መግለጫው ግለሰቦቹ የተያዙት በፖለቲካ ጉዳይና ባላቸው የዝምድና ትስስር እንደሆነና የአያያዛቸው ሁኔታም ለድብደባና ለስቃይ ሊያጋልጣቸው ይችላል የሚል ስጋት እንዳለው አስታውቋል፡፡

እንደሚታወቀው የኢፌዲሪ መንግስት በግለሰቦች ላይ ተከታታይ ግድያ ለመፈጸምና የሕዝብ መገልገያ ተቋማትን ለማውደም ዝግጅት ሲያደርጉ የቆዩ ተጠርጣሪዎች ላይ አስፈላጊውን ማስረጃ ሲያሰባስብ ከቆየ በኋላ በፍርድ ቤት የማሰሪያ ትዕዛዝ በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል፡፡

ሁሉም ታሳሪዎች ሰብአዊ መብቶቻቸው በተከበሩበት አኳኋን በህግ ከለላ ስር የሚገኙ ሲሆን ምርመራው እንደተጠናቀቀም በገለልተኛ ፍርድ ቤት ክስ ይመሰረትባቸዋል፡፡

መንግስት ይህን አለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያገኘ አሰራር በመከተል ጉዳዩ በነጻና ገለልተኛ ፍርድ ቤት እንዲታይ ለማድረግ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ በሚገኝበት ሁኔታ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በህግ ስልጣን ከተሰጠው ፍርድ ቤት አስቀድሞ ግለሰቦቹ የታሰሩት በፖለቲካና በዝምድና ምክንያት ነው ብሎ መግለጫ መስጠቱ የፍትህ ሂደቱን የሚፃረር ተግባር ነው፡፡

ይህ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ነኝ ባይ ድርጅት በጉዳዩ ላይ ከተጨባጭ ሁኔታው የራቀ አቋም ከመያዙና ከማራመዱ በፊት ቢያንስ ቢያንስ መንግስት ማስረጃ እንዳለውና ሁሉም ግለሰቦች በተሟላ ህጋዊ ስርአት መያዛቸውን የመግለጫው መነሻ ማድረግ ነበረበት፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት መሰረት የተቋቋሙት ፍርድ ቤቶች ማስረጃዎችን መርምረው በህጉ መሰረት ውሳኔ ሊሰጡ እንደሚችሉ ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ነበረበት፡፡

ነገር ግን በሰብአዊ መብቶች አከባበር ቁጥጥር ሽፋን የሀገሪቱን ስም በማጉደፍ ላይ ከተሰማሩት ድርጅቶች አንዱ የሆነው አምነስቲ ለፍትህና ለሕጋዊነት ዕሴቶች ቦታ ከመስጠት ይልቅ ሕግ በመተላለፍ የተያዙትን ሰዎች የሰብአዊ መብት ጥሰትና የፖለቲካ ዘመቻ ሰለባዎች አስመስሎ ማቅረብን መርጧል ፡፡

በአገራችንም ሆነ በአለም አቀፍ ህግጋት ገና ውሳኔ ባልተሰጠበት ጉዳይ ላይ ጫና ለመፍጠር የሚደረጉ ማንኛቸውም የተዛቡና ወገናዊ የይፋ መግለጫዎችና አስተያየቶች ፈጽሞ ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው፡፡

ሆኖም አምነስቲ እነዚህን የዳኝነት ነጻነትና ገለልተኝነት መርሆዎች በመጣስ በፍርድ ምርመራ ሒደቱ ላይ ተገቢ ያልሆነ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ መግለጫ እስከማውጣት ደርሷል፡፡

አምነስቲ እየፈጸመ ባለው ጣልቃ ገብነት አለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያላቸውን የዳኝነት ነጻነትና ገለልተኝነት መርሆዎች እንደሚጥስ መረዳት ተስኖት ሳይሆን ድርጊቱ በሃገራችን ላይ የሚደረገውን የቅጥፈትና የማጥላላት ዘመቻ ያጠናክራል ብሎ ስላመነ ብቻ ነው፡፡

በዚህ አጋጣሚ የኢፊዲሪ መንግሥት እንደተለመደው ዜጎች ሕገመንግሥታዊ መብታቸውን በመጠቀም የሚያደርጉትን ጥረት ከማጎልበት በተጨማሪ ማንም ሰው ሕግን ተላልፎ በተገኘ ጊዜ ሰብአዊ መብቱ በተጠበቀበት አኳኋን ጉዳዩ ሕጋዊ እልባት እንዲያገኝ ማድረጉን የሚቀጥል መሆኑን መግለፅ ይሻል።

ሚያዝያ 29 ቀን 2001 ዓ.ም