ጠንካራ አባል መሪ አጥቶ አያውቅም!

ኃይሉ ቅንጅት፣ ብርሃኑ ቅንጅት፣ መስፍን ቅንጅት፣ ልደቱ ቅንጅት፣ ብርቱካን ቅንጅት ይባሉ እንዳልነበሩ ሁሉ ዛሬ ሁሉም የቻሉትን ደጋፊ ይዘው በየአቅጣጫው እየሮጡ ነው። ይሄ ማነው አየለ ጫሚሶ የሚባለው ሰውዬ እንኳ “ቅንጅት ነኝ” ብሎ ከቅንጅት ሊቀመንበር ኃይሉ ሻውል ጋር ለፊርማና ለድርድር አብሮ ተቀምጧል። አቶ ኃይሉ ሻውልም “አንተ ደግሞ የመቸው ቅንጅት ነህ?” ብለው ተገርመው አልጠየቁትም። እንዲያውም ከአቶ መለስ ፓርቲ ጋር ብቻ ሳይሆን ከቅንጅትም ጋር ልንሠራ ፣ ሰላም ፈጠርን ተደራደርን አሉን። ከብርቱካን ይልቅ ጫሚሶን ያስመረጣቸው እግዚአብሄር ይመስገን! ከእነ ኃይሉ ሻውል ይልቅ እነ ስዬ አብርሐን የመረጡ የእነ ብርቱካን ሰዎችም እንዲሁ። ለእነስዬና ለእነገብሩ አስራትም ከአቶ መለስ ይልቅ እነ መረራ ጉዲና ይቀርቧቸዋል። ትምክህተኞችን አንወድም ለሚሉት ለአቶ መለስ ፓርቲም ቢሆን እንደሳቸው “ብሄር ብሄረሰቦች” ከሚሉት ከእነ በየነ ጴጥሮስ ይልቅ፣ “የጎሳ ፖለቲካ አንወድም” የሚሉት እነ ኃይሉ ሻውል ይሻሏቸዋል። ይህ ሁሉ የአተረማማሾች የፖለቲካ ትርምስ ነው።

መቸም ከእነዚህ ሁሉ ሰዎች (መቸም ድርጅት የለም) የአንዳቸው ደጋፊ መሆናችን አይቀርም። እና ምን እያልን ይሆን? የሚሆነው ነገር ገብቶን ይሆን? ለነገሩ ገባን አልገባን ምን ማምጣት እንችላለን- ድርጅት የሚባል መች አለን። ማምለጫችን ይቺ ናት።

መደራጀት ማለት የጠንካራ መሪ ባለቤት መሆን ማለት አይደለም። ድርጅት የጠንካራ አባላት መኖር ነው። ጠንካራ አባል መሪ አጥቶ አያውቅም። ጠንካራ ድርጅት ደካማ መሪዎች የሚያፈርሱት ደካማ ቤት አይደለም። መሪዎቼ “ከዱኝ!” እያለ በየወንዙ የሚያልቅስ ልፍስፍስ መንጋ የሚያቆመውም ተቋምም አይደለም። ይልቁንም መሪዎቹን ጊዜና ደንብ ጠብቆ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መቀያየር የሚችል ነው። ይህ መብትና አስገዳጅ ጉልበት ያለው አባል ድርጅት አለኝ ማለት ይችላል። ካልሆነ ግን ጀሌ ነው። የብርቱካን አምላኪ፣ የኃይሉ ጀሌ፣ የልደቱ አጨብጫቢ የብርሃኑ ተሳቢ ነው። “እኔን ያልክ ተከተለኝ” ብሎ አመራር ቆም ብሎ ማሰብ ለማይችል መንጋ የሚሰጥ ትእዛዝ ነው። ፕሮፌሰር መስፍን በዚያ፣ ኢንጂነር ግዛቸው በወዲያ፣ ኃይሉ አርአያ በወዲህ ያዕቆብ በሌላ መንገድ ሲሮጡ እየተሸራረፈ የሚሮጥ መንጋ፣ አባል ሳይሆን ምንም መሠረት የሌለው ተጎታች ነው።

እውነት ነው ከእነዚህ ጠንካራ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። የተነሱ የወደቁ፣ የተወገዙ የተመረቁ፣ የታሰሩ የተፈቱ፣ ተፈትነው የታዩ፣ የበሉ የተበሉ ይኖራሉ። ምናልባትም ጠንካራ አባልና ተከታይ ቢኖራቸው ጠንካራ ድርጅት የሚወጣቸው ይኖራሉ። ከሌላቸው ወይም ካልነበራቸው ግን አሁን እንደሆኑት ሆነው ይቀራሉ። አሁን የሆኑትን የሆኑት በራሳቸው ድክመት ነው ወይንስ በኛ አጓጉል መንጋነት ጭምር ነው የሚለውን የሚያውቅ የለም። ያሳሰርነውን ማስፈታት ካልቻልን፣ እንዲያውም እሱን ወይም እሷን ረስተን ከአዲስ መጪው ጋር ከዘለልን፣ የወረት ደጋፊዎችና ከንቱ ጯኺዎች ሆነን እንቀራለን። የታሰሩልንም እኛን አምነው እኛን ብለው ከሆነ ይታዘቡናል፣ ያዝኑብናል፣ ያፍሩብናል፣ በልባቸውም ይጠሉናል፣ ብሎም ይንቁናል። እንደ ኃይሉ ሻውል ይተፉብናል።

ንቀታቸው በብዙ መንገድ ይገለጻል። ለምሳሌ አይፈሩንም። አርባ ቦታ ተከፋፍለው የቆሙት አርባ ቦታ ተከፋፍሎ የሚቆም ደጋፊ መኖሩን ስለሚያውቁ ሊሆን ይችላል። ማን ምን ሊያደርጋቸው ይችላል? “እኔ ድርጅቴን ከአንተ በላይ እወደዋለሁ፣ ብትፈልግ አንተ ጥርግ በል!” የሚላቸው ማነው? የትኛው ደጋፊ ይጎዳቸዋል? የትኛው ደጋፊ አቅፏቸው እስከመጨረሻው ሊጓዝ ይችላል? የትኛው ደጋፊ መሪዎቼን አሁኑ ካልፈታችሁ ጉድ አፈላለሁ ብሎ ያስጥላቸዋል? 10ሺ ሰዎች ታስረው 10ሺ ሰው እንቅልፍ ተኝቶ ሲያድር ታይቷል። የሚርመጠመጥ፣ ሰንካላ ምክንያት የሚያበዛ፣ ቅራቅምቦ የሚያስጎመዠው የማይኖርበትን ቤት የሚገነባ፣ በገዛ አገሩ ተደብቆ የሚገባ፣ “እኔ ፖለቲካ አልወድም!” ባይ ሥልጡን ጮሌና ሎሌ በየቤቱ ሞልቷል። “መብት” በሚል ምሽግ ሥር የተደበቀ መብት ያለው እየመሰለው መብቱን አሳልፎ የሰጠ፣ በር ዘግቶ የተቀመጠ ብዙ ነው። የራሱ መሆኑን ረስቶ የገዛ አገሩን የሚቀላውጥ እልፍ ነው። “ፖለቲካ አልወድም” ባይ ሁሉ ፖለቲካውን ትቶ አፉን ዘግቶ ቢኖር ጥሩ ነው። ግን አዳሜ በያለበት ከማጉረምረም አልዳነም። “እኔ ፖለቲካ አልወድም!” የሚለው ሰው፣ ከትንሽ ደቂቃ ጭውውት በኋላ፣ ሮሮውን ያቀልጠዋል። “እነዚህ ሰዎችኮ…” እያለ በገዛ ቤቱ የሚንሾኳሾክ ዘመን የዞረበት ዘመናዊ ትውልድ እልፍ ነው። የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችም ይህን ሁሉ ይታዘባሉ። ያወቁበትም ይጠቀሙበታል። ስለዚህ በስሙ ያሻቸውን ያደርጋሉ።

“ምን የሚረባ የፖለቲካ ድርጅት አለ? ሁሉም ዝም ብሎ ሌባ ነው!” እንደዚህ ነው እንደዚያ ነው… ሲባል ይሰማል። ልክ ሊሆን ይችላል። ያልተፈጠረ ከየ ይመጣል? የጠነከረ ድርጅት ሊፈጥር የሚችል ህዝብስ የት አለ? ራሱን በራሱ አነሳስቶና አደራጅቶ ዘራፍ ተነስቻለሁ፣ ራሴን በራሴ አሰተባብራለሁ፣ መሪዎቼን ከራሴ አፈልቃለሁ፣ የሚል ህዝብ የታለ? መዋጮ መወርወር ወይም ምን እንደተባለ እንኳ ሳያቁ ማጨብጨብ አይደለም። ወጥቶ መምረጥ ድምጽ መስጠትም አይደለም። ቁምነገሩ ከሚመርጡት የሰው ዓይነት እንጂ ከምርጫው ተሳትፎ አይደለም። አገር ወጥቶ የመረጣቸው አጁዛዎችንማ አየናቸው። ባህል ሆኖብን አክብሮት ተብሎብን ስንቱን ሽበትና ቅሌት ተሸከምን።

ህዝቡ ከዚህ በላይ ምን ማድረግ ይችላል? የሚሉት ፈሊጥ ይሰማል። ምንድነው ከዚህ በላይ ብሎ ነገር? ሩጫዬን ጨረሻለሁ … የሚል ህዝብ ምን ዓይነት ነው? ከአቅሜ በላይ ምን ማድረግ እችላለሁ ብሎ ነገር ምንድነው? ከህዝብ አቅም በላይ ማን አቅም ሊኖረው ነው? ደግሞ አገር ውስጥ ያለው ጨንቆት ነው ይባል ውጭ ያለውስ? ከጀመረኝ ይጨርሰኝ ብሎ ተስፋ እንዴት ያለ ነው?

ጮሌነትም አለ። አንዳንዴም ነገሩ ሁሉ “ከተሳካላችሁ ጥሩን ካልሆነላችሁ ጥፉ!” የሚል ብልጠት ያለበት ይመስላል። መሪዎቹ ተከፋፈሉ ብሎ ቋንቋም አይሰራም። ያልተከፋፈለ ህዝብ የተከፋፈሉ መሪዎች ሊኖሩት አይችሉም። መሪዎች ሰዎች ግለሰቦች ናቸው። ሰዎች ከፋፈሉኝ የሚል ምክንያት የጅል ነው። ሁለት ሰዎች ከተሰማሙ ሶስተኛውን ሰው በድምጽ ብልጫ ሊያሸንፉት ይችላሉ። ድምጽ መቁጠር ካልተለመደ ግን ማን እንዳሸነፈ ማን እንደተሸነፈ ማን ብዙሃን ማን አነስተኛ እንደሆነ ማወቅ አይቻልም። ቁጥር መውደድ አንዱ መፍትሄ ነው። ነገረ ሥራችን ሁሉ ግምት ነው። ህዝቡ የሚደግፈው ያንን ነው ወይም ይህንን ነው ማለት እንወዳለን። ራሳችንን እንደህዝብ እናያለን። ዝምብሎ ሃይሉ ብርሃኑ- ብርቱካን- ልደቱ- ክህደቱ ከማለት እስኪ ከመካከላችን የሃይሉ ደጋፊዎች በቁጥር ስንት ናቸው? የብርሃኑስ? የብርቱካንስ? እያሉ ለይቶና ተለያይቶ መተዋወቅ ይረዳል። ኢህአዴግን የጠላ ሁሉ ወዳጄ ነው በሚል ወይም በስመ ተቃዋሚ ሁሉንም የምንደግፍም አንጠፋም። አንድ ቢሆኑልን የሚለው አመለካከት የሚመጣው ከዚህ ነው። እኛ አንድ እንሁንና እነሱ አርባ በሆኑ!

ተቀማዋሚ የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ መሪዎቻችን የምናየው እንደ ቡፌ ምግብ ነው። ከሁሉም ትንሽ ትንሽ ማንሳት እንፈልጋለን። የምፈልገውን መርጠን ከመብላት፣ አሁን ምናለበት ሁሉም ክትፎ ቢሆኑልን ወይም ቀይወጥ ቢሆኑልን ማለት ይመስልብናል። የምርጫ ችግር አለብን። የራሳችንን መፍጠር ካልቻልን መምረጥ ግዴታችን ነው። ወይ ብርሃኑን ወይ ጨለማውን! ሁሉን ትቶ ዝም ማለት ደግሞ መብታችን!

ከዚያ የብርሃኑ ሀሳብ ምንድነው? የኃይሉስ እንዴት ነው? በሁለቱ መካከል ያለው መሠረታዊ ልዩነት ምንድነው ማለት ጥንካሬ ነው። ስዎቹ እንጂ ሀሳቦቻቸው አያስጨንቁንም። ልዩነቶቻቸው አይገቡንም። ምክንያቱም ፍላጎታችን ሁሉ የአቶ መለስ መንግሥት መወገድ ብቻ ነው። አቶ መለስ ደግሞ ለምንድነው የምወገደው? ምንድነው የምትፈልጉት እያሉን ነው? ተነጋገሩ የተባልን ቀን የምንፈልገውን ሁሉ አሟልተው ከተገኙ ምን ልናደርጋቸው ነው? በፍጹም ሊያሟሉልን አይችሉም የሚል ጀብድ አይሰራም። ሥልጣን ላይ ያለ ሰው ለሥልጣኑ ሲል የማይለው ነገር አይኖርምና ነጥቦቻችንን አጥርተን ማወቅ ይኖርብናል። አሁን የተያዘው አቅጣጫ ይህ ይመስላል። ቀና ስንል ነጥቦቻችን ሁሉ የተመለሱ መስለው እንዳያስደነግጡን፣ በብልጠት እንዳበለጥ፣ በውሸት እንዳንሞኝ ልንዘጋጅ ይገባናል። “አንዳንድ ጊዜ ግን ሳስበው ከእነዚህ ተቃዋሚችኮ መለስ ይሻለኛል” የሚሉ ገልቱዎች ቀስ በቀስ ብቅ እያሉ ነው። ስለዚህ የመደራጀት ጠቀሜታው መሪ ለማፍራት መንግሥት ለመገልበጥ ብቻ ሳይሆን ነገርንም ተወያይቶና አጥርቶ ለማወቅ ይጠቅማልና ራሳችንን በመረጃ በኢንፎርሜሽን የምናንጽበት ድርጅት፣ፕሮግራሙን በደንብ የነደፈ መተዳደሪያ ደንቡን ያገዘፈ ከመሪዎቹ፣ ይልቅ ህግና ደንቡ ደስ የሚለን፣ ብሎም ጽናትና ዋስትና የሚሰጠን ድርጅት ያስፈልገናል።

መደራጀት ማለት በአገር ፍቅር መቃጠል ወያኔን ማብጠልጠል አይደለም። ወይም አብዮት ማቀጣጠል አይደለም። ዘመኑ አብዮት የሚወድ አይመስልም። የተፈነቀለ፣ የገነፈለ፣ የተቀጣጠለ ህዝብ ማየት ፋሽኑ ያለፈበት ይመስላል። ቢኖርም ወይም ኖሮ ቢያውቅም በስንት ዘመን አንዴ የሚታይ ነው። ስለዚህ ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ነውና የሚስማማንና የሚበጀንን እየመረጠን በማወቅና በመተዋወቅ እየተሰባሰብንና እየተደራጀን መንገዳችንን ብናቃና ይሻለናል። ጉልበትም የምናገኘው ያኔ ነው። (ዘኢትዮጵያ)