አዲሱ ባቡር አረጀ!

ብዙ የተወራለት የአዲስ አበባው ባቡር ብዙ ተሳቢ ፉርጎዎች ሳይሆን ብዙ ችግሮችን እየጎተተ ይመስላል። ገና በአዲስነቱ ያስረጁት ችግሮች እየተዥጎደጎዱ ነው። የባቡር ኮርፕሬሽኑ ችግሮቹን እንዲያስተካክል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ- የሚል ዜናም ከሰሞኑ ተደምጧል።

ባቡሮቹ በሠዓታቸው አይደርሱም፤ ብዙ ተሳፋሪዎች ትኬት አይገዙም፤ የገዙትም ከከፈሉበት በላይ ርቀው ይጓዛሉ። እንደ የርቀቱ ሁለት፣ አራትና የስድስት ብር ቢያስከፍልም፣ ትኬት ሳይገዙ የሚጓዙ ተሳፋሪዎችን ለማገድ የተቆጣጣሪዎቹ ቁጥር አነስተኛ ነው። በትኬት አጠቃቀም ላይ አንድ ወጥ የትኬት ስርዓት አልተዘረጋም። ትኬቱ በወረቀት እንጂ በኤሌክትሮኒክስ የሚሠራ አለመሆኑም ሌላው ችግር መሆኑን ኮሮፖሬሽኑ አምኗል።
አሁን ያሉት 41 ባቡሮች ከእነዚህ ችግሮች ጋር በፌርማታዎች ላይ የሚታዩ ሰልፎችን መቀነስ አልቻሉም። በአንዳንድ አካባቢዎች ከባቡሩ የሚለቀቁ ተሳፋሪዎች የእግረኛ ማቋረጫ መንገድ ስላልተሰራላቸው አውሮ ጎዳናው አቋርጠው ስለሚሄዱ ብዙ የትራፊክ መጨናነቅ ማስከተላቸውም ሁሌም እንደተወራ ነው። የአገሪቱ መሪዎች ወይ አያስቡም ወይም ግድ የላቸውም ከሚያስብሉ ጥያቄዎች መካከል አንደኛው ሆኖ መታየቱም አልቀረም። አሳሩ ግን ገና ነው።

መለዋወጫው ለካ ተረስቷል!
ከ41ዱ ባቡሮች አንድ ሶስተኛው ተበላሽተው ቆመዋል። የኮርፖሬሽኑ የኦፕሬሽን አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ሰርካ ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት ባቡሮች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ከመለዋወጫዎቻቸው ጋር ባለመሆኑ ባቡሮቹን በሙሉ አቅም መጠቀም አልተቻለም። በኢትዮጵያ ቢሮክራሲ ቋንቋ “በሙሉ አቅም መጠቀም አልተቻለም” ከተባለ ችግር አለ ማለት ነው።
እሳቸው እንደሚሉት “ከቻይናው ኩባንያ ጋር የባቡር አቅርቦቶችን ለማስመጣት በተፈረመው መነሻ ውል የመለዋዋጫ እቃዎች ማስገባት አልተካተተም” – አልተካተተም- ሲሉ ተረስቷል ላለማለት ነው። መለዋወጫን ያህል ነገር ግን በእርግጥ ተረስቷል። አሁን ግን ከኩባንያው ጋር ስምምነት ስለተደረሰ ግዥ የተፈጸመባቸው የባቡር መለዋወጫ እቃዎች ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ናቸው።
ገና ከመናሻው ቅያሱ ራሱ አላማረበትም። ሰፕቴምበር 2015 ላይ የተጀመረው ባቡር በአብዛኛው በቻይናውያን የገንዘብ ድጋፍ የተሠራ ነው። 475 ሚሊዮን ዶላር የወጣበት ሲሆን 85 ከመቶ የሚሆነውን የሸፈነው የቻይናው ኤክዚም ባንክ ነው። ሥራው የተሠራው ደግሞ በቻይናው የምድር ባቡር ኢጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ነው። ለተጨናነቁ የአፍሪካ ከተሞች መፍትሔ መሆኑ በጊዜው አስደንቆ እነ ናይሮቢና ሌጎስ ሳይቀሩ ሀሳቡን እስከመቅዳት መድረሳቸው ሁሉ ተወርቶለት ነበር። 39 ጣቢያዎች ያሉት እና የ34 ኪሎሜትር ሐዲድ የተዘረጋለት ቀላሉ የከተማ ባቡር ከመሃል አዲስ አበባ ተነስቶ ደቡቡ እና ምስራቁን የከተማይቱ ክፍል እንዲያገናኝ ነበር የታሰበው። እንደ ዓላማው በቀን 120 ሺ ሰዎችን ያጓጉዛል ሁሉ ተብሏል። ስለሆነም ብዙ የትራንስፖርት ችግር እንደሚቀርፍ ታምኖ ነበር። ግን እንኳን ሊያቃልል የነበረውንም የከተማውን ትራፊክ እጅግ አባባሰው እየተባለ ነው።

ከሀሳቡ ሳይሆን ከፕላኑ ነው!

ገና ከመነሻው ፕላኑ ራሱ ልክ አልነበረም የሚሉ ተቺዎች አሁን ድረስ አልተለዩትም። ለምሳሌ ከከተማ አውቶብስ መስመሮችም ጋር አልተቀናጀም። ምክንያቱም በብዙ ከተሞች እንደሚደረገው አውቶብስና ባቡር በቅብብሎሽ ብዙ ሰው ያጓጉዛሉ። ይህ ባለመኖሩ እግረኞች ከባብሩ ጣቢያ ለመድረስ በእግሯቸው ብዙ መንገድ ይኳትናሉ። ሲወጡም እንደዚያው ነው። በዚህ ላይ የባቡሩን ጣቢያ ከመንገድ ወስዶ የሚቀላቅል የእግረኛ ማቋረጫ የለም። የሐይዌው ላይ አሸከርካሪዎች ሳይቀሩ መንገደኞችን እየቆሙ ማሳለፍ አለባቸው። አንዳንዴ ትርምሱ ጊዜ ይወስዳል። ያ መሆኑም የባቡሩ መምጣት የከተማውን ትራፊክ እንደመቅረፍ ይበልጥ ያጨናነቀው ሆኖ ተገኝቷል። ሰውም ባቡሩም መኪኖቹም አልፈጠኑም!
ያም ሆኖ እንደተባለው ካሉት ባቡሮች አንድ ሶስተኛ ያህሉ አይሰሩም። የተቀሩትም አቅም ኖሯቸው አልሮጡም። ሌሎቹም በጊዜ አይመጡም። አዲሶቹ አሮጌዎች ሆነዋል።
የባቡሩ ኮርፖሬሽን ቃለ አቀባይ አቶ አወቀ ሙሉ “ ድሮውንም ቢሆን እኛ የከተማውን የትራንስፖርት ችግር እናቃልላለን አላልንም” ብለዋል። እንደሳቸው እምነት 4 ሚሊዮን በላይ የሆነው የአዲስ አበባ ህዝብ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው። ቢሆንም ግን የአዲስ አበባው ባቡር ከተጀመረ “እስካሁን 50 ሚሊዮን መንገዶችን ማጓጓዝ መቻሉን” ገልጸዋል። አባባላቸው እሱንስ ቢሆን ማን አገኝ ይመስላል። (ለደስታ)

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*