ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር ኢትዮጵያውያን ግን ገደል ይግቡ!

አምባገነኑ ህዝቤ!

ይፈቀድልን!

አገራችንኮ ምስጋና እንኳ ለማቅረብ ፈቃድ ይጠየቃል። “በዚህ አጋጣሚ ምስጋናዬን እንድገልጽ ይፈቀድልኝ” ይባላል። ህዝብም ያጨበጭብና ይፈቅዳል። ያቺ መከረኛ አገር ይሄኔኮ በታሪኳ “ሳያስፈቅዱ ማመስገን ክልክል ነው” የሚል ህግ ወጥቶባት ይሆናል። ለምስጋና ማስፈቅድ የሆነ ለትችትማ ዝም ነው። ለማናኛውም እስኪ እኛም በሰውና በአገር ጉዳይ አንዳንድ ጥቃቅን ነገሮችን አስቦ ለማሳሰብ ይፈቀድልን!

ለምሳሌ “ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር ኢትዮጵያውያን ግን ገደል ይግቡ!” መሳዩ እምነታችን ይመርመርልን! እንዲህ ያለ እምነት ሳናውቀው በውስጣችን ማደሩንም ስንቶቻችን እንደምናውቅ ይጠየቅልን።

ሰሞኑን የጻፉልን ኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያም ቢያንስ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ አቋማቸው ደስ ይላል። በኢትዮጵያ አንድነት ስም ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ቢጨርሱም ይፈቀድላቸዋል። ኢሳያስ አፈወርቂ ለሰው ህይወት ምህረት ባይኖራቸውም ቢያንስ አገራቸውን ይወዳሉ ይባልላቸዋል። “ቢወዳት አንቆ ገደላት” እንዲሉ ኤርትራን አንቀው ይዘዋታል። አቶ መለስ ዜናዊም በልማት በሰላምና በሰጥቶ መቀበል ስም ኢትዮጵያውያንን እየገደሉ እያሰሩ ለስደት እየዳረጉ መሆኑን እያየን ነው። ደጋፊዎቻቸው አባይን እየገደቡ ያሉ ለአገር አሳቢ መሪ ያደርጓቸዋል። ለአገር ሰላም ሟች ናቸው። “አገር ከምትሸበር ዜጎቿ ቢሸበሩ ይሻላል” እያሉን ነው። እነዚህ ሰዎች አርጅተውም አይቆጩም። ኮ/ል መንግሥቱ ባሁኑ መጽሐፋቸውም ስላስገደሉት ሰው ሳይሆን ስለሞተባቸው አገር ስለተቀለበሰው አብዮታቸው ነው ተጨንቀው የሚታዩት። እነ ጄኔራል አማንን እነ ኮ/ል አጥናፉን ስለማስገደላቸው አልተቆጩም። ዘንድሮም “አብዮት ልጆቿን በላች!” እያሉ ነው። ለማን ብላ ይሆን የምትበላው?  ለአገር ብላ ነዋ – ስቱፒድ!

እንደ መንግስቱ ያሉት መሪዎቻችን አገር እንጂ ሰው አይደሉም። ሰው ቢሆኑ ኖሮ ይቅርታ እንኳ ባይጠይቁ፣ መጸጸታቸውን ቢያሳውቁ ፣ በበጃቸው ውግዘት ማቅለያ በሆናቸው ነበር። ግን አገርና ሰውን መውደድ ላይ ያለው ልዩነት ስላልገባቸው ሊሆን ይችላል። ከህሊናቸው ጋር አስተቃቅፎ የሚያስተኛቸው ያደረግኩት ነገር ሁሉ “ለአገሬ” ስል ነው ለኔ “ለመንግሥቱ” ብዬ አንዲትም ነገር አላደረግኩም… ብለው ሊሆን ይችላል። ግን ሳቅና ትዝታን ከተጋሩት ወዳጆቻቸው ስንቶቹን ፈጅተዋል?  ሌሊት ሌሊት ስንቶቹ ይመጡባቸዋል? አገር እኮ ከአብሮ አደግ፣ ከባልደረባ ፣ ከወዳጅ ዘመድ ጋር ቁጭ ብለው ሲያወጉበት ነው። እንጂ ብቻውን ምን ይሠራል? ለነገሩ እሳቸው አገር ትተው ሰው ቢሆኑ ይበጃቸው ነበር። ሰው ልብ አለው ያዝናል- ይጸጸታል- ይማራል- ይሸነፋል- ይለወጣል…

ግንኮ በአገር ቀልድ የለም! ለአገር ብሎ በአቋም መገተር ያለ ነው። አቤት አገር ላይ ስንት ሰው ተንጠለጠለ? ዘንድሮም ይነግደበታል። “እሱ ክፉና አረመኔም ቢሆንም” አገሩን ይወዳል ይባላል። ስንት ክፉ ሾለከባት። እሱ በእርግጥ አልተማረም ክፉና ደንቆሮ አጭበርባሪ ቢጤ ነው ዝምብሎ በየመድረኩ ይጮኻል…ይባልና ማሳረጊያው ግን “አገሩን ስለሚወድ” ….ይባላል። አገር መውደድ ምንድነው? አገራቸውን የሚወዱ ጥቂት የቁርጥ ቀን ልጆች ብቻ ሆነው ሌላው ግን አገሩን እየጣለ ይሰደዳል። በእርግጥ የቁርጥ ቀን ልጆች አገራቸውንም ጥለው ይሰደዱና በስደትም ሆነው ይወዷታል። ግን ሰው አገሩን  ትቶ ለምን ይሰደዳል?

አገር ጥለው የሚሰደዱ ሰዎች የ13 ወር የፀሐይ ብርሃን ፍለጋ አይደለም። ሰዎቻችን በቀን አራትና አምስት ሰዓት ብቻ ፀሐይ የምትወጣበት አገር ተሰደው እየኖሩ፣ በረዶ እየቆፈሩ ነው። እርግጥ ነው ሰው አጥተው ሰው ፍለጋም አይደለም የሚሄዱት። የሚያስኬዳቸው አገራቸው ከሰው ስለማትቆጥራቸው ነው። አገራቸው ከሰው ሰው ስለምታማርጥ ነው። እናት አገራቸው ከወላጅነት ወደ እንጀራ እናትነት ስለተቀየረችባቸው ነው። አገር ውስጥ እየኖሩ አገር የሚናፍቁባት አገር ናት ኢትዮጵያ። ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖሩ ኢትዮጵያን መናፈቅ ምንድነው?

ሰዎች አገራቸውን ጥለው የሚሰደዱት አገራቸውን የማይወዱ ሰዎች ሥልጣን ላይ ስላሉ ነው ብለው ያስባሉ። ሊሆን ይችላል። እስከዛሬ ሊሆን ስለመቻሉ ብቻ ሳይሆን በእርግጠኝነት ብለነዋል። ግን ባይሆንስ? እስኪ ደግሞ በሌላ መልክ ገልብጠን እናስበው። ወይም እንድናስበው ይፈቀድልን?

ለምሳሌ መለስ የአባይ ግድብ ላይ “እያጭበረበሩ” ነው ብሎ ማሰብ ይቻል ይሆናል። ኢትዮጵያውያንን የሚጠሉትን ያህል አገራቸውን ይጠላሉ ብሎ ማሰብ ግን (ተደብቀው ሲያስቡት) ትንሽ ቸገር ይላል። ቢያንስ የመለስ አገር የት ነው ብሎ መጠየቅን ይጠይቃል። መለስ እኔ አውቃለሁ ለዚያች አገር የሚበጀውን እኔ አደርገዋለሁ። የጥበብ መጀመሪያውም ማለቂያውም እኔ ነኝ ባይ ናቸው። በዚያ ላይ የበላይና የበታች እንዲሆን የሚፈልጉት የህዝብ ክፍል ይኖራል። ያም ሆኖ ግን አገራቸውን ለማጥፋት ይሰራሉ ብሎ ለማሰብ እስካሁን ካጣፏት በላይ ሊያጠፏት ዘንድ የከለከላቸው አለ ብሎ ማመንን ይጠይቃል። ማንን ፈርተው? ያው እየረገጡን ነው። መለስ በራሳቸው መንገድ ታሪክ ሠርተው ለመሄድ እየፈለጉ ሊሆን ይችላል። ችግራቸው እንደሌላው ሁሉ አገርና ሰውን ለይተው ማየት አልቻሉም። መለስ ለኢትዮጵያውያንም ሆነ ከተፈለገም ለዛሬዎቹ የትግራይ ወገኖቻቸው ብርቱ ጥላቻ ሊኖራቸው ይችላል። ኤርትራ ላይ ብዙ ባይጨክኑም ኤርትራውያን ያይናቸውን ቀለም እንደሚደብራቸው የተናገሩበት ወቅት አለ። የበለጸገች ኢትዮጵያን የጠነከረች ኤርትራንም ሆነ ትግራይን የሚያልሙት ግን ለዚህኛው ትውልድ ሳይሆን በሀሳባቸው ላለ፣ ገና ለሚመጣ፣ ወይንም ባይኖርም ግድ ለሌላቸው አንድ የማያውቁት ህዝብ ሊሆን ይችላል። ማን ይሆን?

ተቃዋሚ ፖለቲከኞችም እንዲሁ ናቸው። የሚወዱት አገር እንጂ ሰው ያላቸው አይመስሉም። ሰው ሁሉ የየራሱ ህዝብ ያለው ይመስላል። ይህኛው ህዝብ ተራበ፣ ታሰረ፣ ተገደለ – ግፋ ቢል ጥቂቱ ሻማ ያበራል እንጂ የተቀረው አይቶና ስምቶ ዝም ነው። ብዙ ሰበበኛ ደግሞ ከመለስ በኋላ ያለው ትውልድ (ህዝብ) ያስጨንቀዋል። ያኛው ህዝብ ከሚጠፋ ይኸኛው ህዝብ ገደል ቢገባ ይሻላል ማለት እስኪቀረው ድረስ ይተነትናል። ወይም አገር ከሚበታተን ይህ ህዝብ ቢደኸይ ቢሰደድ በረሃብ ቢያልቅ ይሻለዋል። መለስና ደጋፊዎቻቸውም እንዲሁ ናቸው። ስለትግራይ የሚያለቅሱ ትግሬዎችን ግን እያስለቀሱ ነው። ሌሎችም አገር ከሚደኸይ ይኼኛው ህዝብ ተፈናቅሎ ህንዶቹ ቢያለሙት ይሻላል ባይ ናቸው። በልቡ የሚደግፋቸውም አገር መለወጡን ፎቆና መንገድ መዘርጋቱን ይቆጥራል። አዎ ሰው እየደማ አገር እየለማ የውጭ ምንዛሪ እየገባ ነው። ሰው ደግሞ እየወጣ ነው። እድገቱ ሁሉ “ሰው ውጣ ዶላር ግባ!” እየሆነ ነው። “አዲስ አበባን አታውቃትም፣ ሰው ግን ደህይቶ ያሳዝናል” ባይ ጅላጅል ተንታኝ ሞልቶናል። “እዚህ ውጭ አገር ነው እንጂ እዚያ ምንም የለም፣ሰላም ነው” የሚል ማጭበርበሪያም አለ። እስክንድንር ነጋ ያለው እዚህ ሳይሆን እዚያ ነው። ቃሊቲም ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ያለው። ኑሮም የተወደደው እዚያው ነው!

ይህን ግን ፈንጪ ተቆጪ ሳይኖርና ዘና ብሎ መጫወት ቢፈቀድ ኖሮ ጥሩ ነበር። አንዳንድ ሀሳቦችን ጨምቆ መጫወት ቢቻል ስንት ነገር ገሀድ በወጣ ነበር ያሰኛል። እውነት እንደጎደለው ሰው ጩኸት ከምናበረታ ዘና ብለን እናውጋው። መነሻችን ሁሉም ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚኖረው ቦታ ነው የሚጨነቀው እንጂ ብን ብትንትን ብላ የጠፋች ኢትዮጵያን የሚመኝ የለም ብለን እንነሳ። ሻእቢያም ሆነ ተገንጥለን ሄደናል ያሉት ኤርትራውያን ሳይቀሩ ኤርትራዊነታቸውን የሚፈልጉት ኢትዮጵያ ውስጥ እንጂ ኤርትራ ውስጥ አይመስልም። ትገንጠል ወዳላችኋት ኤርትራ ሂዱ ሲባሉ “ግድ የለም ኤርትራ እኮ አገር ሳትሆን መንፈስ ናት” ማለት የቀራቸው ብዙ መሆናቸውን ሳንስተውል አልቀረንም። መገንጠልን ምኑንም ከምኑ እንደሚያደርገው ያልተገለጠለት ኦነግ እንኳ ሳይቀር፣ ድንገት ሥልጣን ላይ ቢወጣ፣ ወዲያው በማግስቱ “አሁን የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ስለተመለሰ…” በማለት የመገንጠል ቀዳሚ ጠላት ሆኖ ሊገኝ ይችላል። “ከፈለጋችሁ ሥልጣኑን ሰጥተን እንየው” አይባል ነገር መከራ ሆኖ ነው እንጂ  እንደዚህ ነው የሚመስለው። ለነጻ አውጪዎቻችን ሁሉ ነጻነት ማለት ሥልጣን ነው። ሆኖ ያየነውም በአያያዛቸው የታዘብነውም ይህንን ነው። ሰውና ሰውነት የውሳኔዎቻቸው ሁሉ መሠረት አይደለም። ለምሳሌ የብሔር ብሔረሰቦች ፖለቲካ ቀዳሚ መገለጫ ከሆኑት ነገሮች መካከል ቋንቋ አንዱ ነው። ቋንቋውን ነጻ የወጣበት ቀርቶ የተግባባበት ግን አልታየም። አንድ ትግርኛ ሁለት ህዝብ፣ አንድ ኦሮምኛ 50 ድርጅት፣ አንድ አማርኛ 50ሺ አክቲቪስት፣ አንድ ሶማልኛ እልፍ ነጻ አውጪ ፈጥሯል። ምክንያቱም የነገሮች እንጂ የሰውና የሰዎች ፖለቲካ የለበትም። አሰብን እናስመልሳለን ኤርትራውያንን ግን እናባርራለን። ልዋጭ ልዋጭ አሰብን በሰው!

አገሩን የሚወድ ከበቂ በላይ ሰው አለ። የጠፋው የአገሩን ሰው የሚወድ ሰው ነው። ስለዚህ የአገር ፍቅር ላይ ሳይሆን የሰው ፍቅር ላይ ብዙ መሥራት የግድ ነው። ሰው የመውደድ አብዮት ያስፈልገናል። ከምንዋጋ ብናወጋ፣ ከምንተላለቅ ብንተዋወቅ፣ ለለውጥ ከምንሟማት ስለለውጥ ብንጨዋወት… ቅኝቱን ብናስተካክለው በመፍትሄ እንባረካለን። ግን ምን ያደርጋል አገር ወደን ሰው ጠላን! ማንም ከማንም ጋር አልቆም አለ። በማህበር አስበን በማህበር አድመን በአንዲት ፍረጃ ስንት ሰው ገደልን! በግፍ ከማህበር እንዳንወጣ ስንቶች በፍረሃት አቀረቀርን! አምባገነን መሪ አምባገነን ህዝብ…ብዙ ውግዘትና ጫጫታ!

ባለ አምላክ አማኙም እምነቱን እንጂ ተከታዩን አያስብም። ሙስሊሙ እስልምናን ነጻ ለማውጣት ሙስሊሙን ሳይቀር እየገደለ ነው። ክርስቲያኑም አገሩን ከሰው ነጥሎ እንደሚወድ ፖለቲከኛ ህንጻው ቤተከርስቲያን እንጂ ምእመኑ አያስጨንቀውም ። “ቀኝህን ሲመታህ ግራህን ስጠው” ቀርቶ “ቀኝህን ሳይመታህ ግራውንም ጨምረህ አጠናግረው” ማለትን እያየን ነው። ጠላትህን እንደራስህ አድርገህ ውደደው ያን ጳጳስ ግን እንደ ሰይጣን አድርገህ አውግዘው። ቤተከርስቲያን ማለት ሰው ነው ይባላል። ሰው ግን ከቤተክርስቲያን እየተባረረ ነው። ወይም ሰዎች ከቤተክርስቲያን የመገንጠል መብታቸውን እያስከበሩ ነው። ነፍሱ እስኪጠፋ ወዶ የመረጣቸውን ህዝብ መውደድ አቅቷቸው ከሜዳ ጥለውት የጠፉና የተጠፋፉ ፖለቲከኞችም ስንቶች ናቸው። ምክንያቱም ፍቅራቸው ከሰው ሳይሆን ከአገር ስለነበረ አገር እንዳይጠፋ ስጋት ነበራቸው። ሰውማ ጠፍቷል። ይኸው “አገር ከሚጠፋ ሰው ቢጠፋ ይሻላል” የሚል ፖለቲካ ታቅፈን ቀርተናል። ሰው የሚሆን ሰው እያጣን መሪ ጠፋ እያልን ነው! ሰው ካልወደድን ሰው ካልተከተልን መቸም ዛፍና ጥጃ አይመሩንም!

አገሩም መሄድ ጠልቶ ሰውንም ሸሽቶ ፣ሀበሻ የሌለበት ቦታ መርጦ፣ ተደብቆ የሚኖር ሰው ቤቱ ውስጥ ግን ትልቅ የኢትዮጵያ ባንዲራ ለጥፎ ይኖራል። የአክሱም ላሊበላና ጎንደርን ህንጻ ፖስተር ለጥፎ በህይወት ዘመኑ ግን አንዴ እንኳ ሄዶ ሊያያቸው አይፈልግም። እንኳን ከውጭ ኢትዮጵያም ከሚኖረው ስንቱ እንደሚጎበኘው አይታወቅም። አገር ራሱ ወሬ ነው። ሰው ተጠልቶ ባንዲራ አቅፎ መኖር የአገር ፍቅር ሊሆን ይችላል። የሶስት ወር ህጻን የጎዳዳና ተዳዳሪ በሆናባት ኢትዮጵያ የ3ሺ ዓመት ታሪክ ጣፋጭ ዲስኩር ሲሆን ያሳስባል። ጎበዝ ታሪኩም ይጣፍጠን ግን ህጻኑም ይታየን!

 

ለብዙዎች ኢትዮጵያ ሰው ሳትሆን መሬት ናት። ደግነቱ መሬት የሰው ሳይሆን የመንግሥት ነው ተብሏል። መንግሥትስ የማን ነው? መንግሥትማ የአገር ነው። አገር የማን ነው? አገርማ የማንም አይደለም የሁሉም ነው። ሁሉም ሲባል እነማንን ነው? ህዝብን ማለት ነው። ይሄ ህዝብ ከምን ይሆን የተሠራው? ኢትዮጵያ ከምትባል አገር ነው የተሰራው እንጂ ከሰው አይመስልም። ታዲያ ለምንድነው ሰው ለአገር የሚሞተው?

 

አገር ማለት ምድሩ- ዱር ሽንተረሩ- አየሩ -ወንዙና የባህል ጓዙ ሁሉ ነው። ከሰው መብት ይልቅ የድንበር ጥሰት ህዝብን የሚያስቆጣው ክብር የተሰራው ከሰው ሳይሆን ከግዑዝ ነገር ስለሆን ይሆናል። ማን ያውቃል? ለማናኛውም እስኪ ደግሞ አገርን ትተን ሰውን እናስብ። በአገር ጉዳይ ተብሎ ከሰው ከምንጣላ አገር ገደል ገብታ ከሰዎቻችን ጋር መዋደድ እንልመድ። አገሩን ከሚወድ ክፉ ሰው አገሩን የማይወድ ቅንና የዋህ ሰው እንምረጥ። አገሩን ከሚወድ ገዳይ አገሩን የሚጠላ አቻቻይ እንምረጥ። በአገር ስም ከሚጣላ በአገር ስም የሚፋቀር ህዝብ ይኑረን። እስኪ ደግሞ የፖለቲካ አቋም ትተን የሰውነትና የባህርይን አቋም እናጢን! “እኔኮ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ነው እንጂ ከሱ ጋር ጸብ የለኝም እንዲያውም ስንት ነገር አብረን ያሳለፍን ነን” የሚለውን የጅል ተረት እንመርምረው? የአንድነት ኃይሎች በተገነጣጠሉባት አገር ሌላ ተገንጣይ ለምን ያስፈራናል? እገነጠላለሁ የሚለውን ወንድማችንን “መገንጠሉን ኋላ ትገንጠላለህ በል አሁን ና ግን ምሳችንን አብረን እንብላ!” ማለትን እንልመድ። እስኪ ምናልባት ይህን መንገድ ደግሞ እንሞክረውና የሚመጣውን ነገር እንይ! ሰው ተለያይቶ የአገር አንድነት ምን ያደርግልናል? የሰው አንድነት አይበልጥም? ለተዋደደ ሰው ሳይቤሪያም አገሩ ነው። ለማይዋደድ ሰው ኢትዮጵያ ምኑን ናት? (ዘኢትዮጵያ)