የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን 21ኛ መደበኛ ጠቅላ ጉባኤ ላይ ከቀረቡት መመሪያዎች ውስጥ በቀጣይ አትሌቶች ከፌዴሬሽኑ እውቅና ውጭ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ መሳተፍ እንደማይችሉ ይገለጿል።
ይህ የተደረገው “በዋናነት በፌዴሬሽኑ እውቅና በሌላቸው ማናጀሮች ወደ ውጭ ሂደው ከተወዳደሩ በኋላ ገንዘባቸውን የሚነጠቁ አትሌቶችን ጥቅም ለማስጠበቅ እንዲሁም አበረታች መድሀኒት ተጠቅመው የሚሮጡ አትሌቶች በብዛት ከፌዴሬሽኑ እውቅና ውጭ ሂደው በሚወዳደሩት ላይ የሚከሰት በመሆኑ “ችግሩን ለመካለከል ነው” ተብሏል።
ሌላው መመሪያው ላይ የተካተተው አትሌቶች “ለብሄራዊ ቡድን ከተመረጡ በኋላ የተለየ ምክንያት ከሌላቸው በስተቀር ፌዴሬሽኑ በቀጠረው አሰልጣኝ የመሰልጠን ግዴታ አለባቸው” የሚል ነው።
አሰልጣኙን የደበደበና ለመደብደብ ሙከራ ያደረገ፣ ስልጠናቸውን በአግባቡ በማይከታተሉ አትሌቶች ላይ እንደየጥፋታቸው ክብደት ከውድድር እንዲታገዱና ማስጠንቀቂያ የሚያሰጡ ዝርዝር ጉዳዮች በስነ-ምግባር መመሪያው ላይ ተካተዋል።
አትሌቶችን በመወከል የተገኘው አትሌት ሞስነት ገረመው የቀረቡት መመሪያዎች ከመጽደቃቸው በፊት ከአትሌቶች ጋር መወያየት እንደሚያስፈግ ገልጿል።
ይሁን እንጂ የፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሻለቃ አትሌት ሀይሌ ገብረ ስላሴ ደንቦችና መመሪያዎች የተዘጋጁት አትሌቱን ለመበደል ወይም ጥቅማቸውን ለመንካት አይደለም ። ይህ መመሪያም አትሌቶች ህግና ደንብ አክብረው እንዲሮጡና ከዚህ በፊት ከነበረው “በተሻለ ሁኔታ ጥቅማቸውን ለማስጠብቅ ነው” ብሏል።
ስለዚህ አትሌቶቹን በጉዳዩ ላይ መወያየተቻው “ብዙም አስፈለጊ አይደለም” ብሏል። (ENA)