ሳዑዲ ሴቶች በስታዲየሞች ውድድሮችን እንዲመለከቱ ልትፈቅድ ነው

https://www.bbc.com/amharic/news-41799655

  • 30 ኦክተውበር 2017

Saudi women sit in a stadium to attend an event in the capital Riyadh on 23 SeptemberImage copyright
AFP

አጭር የምስል መግለጫ

ሴቶች ለመጀመሪያ በሪሃድ ንጉስ ፋህድ ስታዲየም ተገኝተው ብሄራዊ ቀንን ማክበራቸው ከሃገሪቱ ወግ አጥባቂዎች የሰላ ትችት ገጥሞታል

ሳዑዲ አረቢያ ሴቶች በስታዲየሞች ተገኝተው ስፖርታዊ ውድድሮችን እንዲመለከቱ ልትፈቅድ መሆኑን ባለሥልጣናቱ ገለጹ።

በሪያድ፣ ጂዳህና ዳማም ባሉ ስታዲየሞች የቤተሰብ አባላት በጋራ መግባት ይችላሉ።

ከፍተኛ የጾታ መድልዎ ያለባት ሳዑዲ፤ ሴቶች መኪና እንዳያሽከረክሩ የሚከለክለውን ህግ ካነሳች በኋላ የፈቀደችው ሌላኛው ነጻነት ነው ተብሏል።

ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን የሃገራቸውን ማህበረሰብ ለማዘመን እና ኢኮኖሚውን ለማሳደግ እየሰሩ ነው።

የሳዑዲ የስፖርት ኃላፊዎች እንዳሉት “ቤተሰቦችን ከመጪው ጥር ጀምሮ ለመቀበል እንዲቻል” ስታዲሞች ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው።

ለውጡን ተከትሎ ምግብ ቤቶች፣ካፌዎች እና የመቆጣጠሪያ መሣሪያዎች በስታዲየሞቹ ውስጥ እንደሚሠሩም ታውቋል።

እስካሁን ድረስ ስታዲየሞቹ ወንዶችን ብቻ ነበር የሚያስተናግዱት።

ለውጦች

እነዚህ ማሻሻያዎች የ32 ዓመቱ ልዑል መሐመድ በነዳጅ ሃብት ላይ ጥገኛ የሆነችውን ሃገራቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለመለወጥ የተያዘው የራዕይ 2030 ዕቅድ አካል ነው።

ከመጪው ሰኔ ጀምሮ ሴቶች መኪና ማሽከርከር እንደሚችሉ ባለፈው ወር ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

የሙዚቃ ዝግጅቶችንና ሲኒማዎችንም ማሻሻያው በቅርቡ እንደሚያካትታቸው ይታወቃል።

Image copyright
AFP

አጭር የምስል መግለጫ

የሃገሪቱ ሴቶች አሁንም ቢሆን ከፍተኛ እገዳ ተጥሎባቸዋል

ባለሙያዎች ግን ዕቅዱ ፈተናዎች ሊገጥሙት ይችላሉ ይላሉ።

ሴቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ወር በሪሃድ ንጉስ ፋህድ ስታዲየም ተገኝተው ብሄራዊ ቀንን ማክበራቸው ከሃገሪቱ ወግ አጥባቂዎችና በማህበራዊ ድረ-ገፆች የሰላ ትችት ገጥሟቸዋል።

የሃገሪቱ ሴቶች አሁንም ቢሆን ከፍተኛ እገዳ ተጥሎባቸዋል።

ሴቶች ጠንካራ የአለባበስ ህግን የሚከተሉ ሲሆን ከቤተሰባቸው ውጭ ከሚገኝ ወይንም ከማይታወቅ ወንድ ጋር መታየት አይፈቀድላቸውም።

ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ፣ ለመሥራትና የጤና አገልግሎት ለማግኘት ከወንዶች ጋር መሄድ ወይንም የወንዶችን ፈቃድ እንዲያመጡ ይጠበቅባቸዋል።

Read more