በስዊድን ያሉ የስደተኛ ልጆች ሚስጥራዊ ህመም

https://www.bbc.com/amharic/news-41780127

  • 30 ኦክተውበር 2017

በሪዛይኔሽን ሲንድረም የተጠቃች ልጅ

ስዊድን ለሃያ ዓመታት ምንነቱ ካልታወቀ በሽታ ጋር እየታገለች ነው። ‘ሪዛይኔሽን ሲንድረም’ የሚባለው በሽታ ጥገኝነት የጠየቁ ልጆችን ብቻ ነው የሚያጠቃው።

በሽታው ሙሉ ለሙሉ እንዳያወሩ ወይም እንዳይራመዱ ወይንም ዓይናቸውን እንዳይከፍቱ የሚያደርግ ነው።

ጥያቄው ግን በሽታው ለምን በስዊዲን ብቻ ተከሰተ?

አባትዋ ከተሽከርካሪ ወንበር ላይ ሲያነሳት የዘጠኝ ዓመቷ ሶፊ ህይወት አልባ ነበረች።

በተቃራኒው ግን የቆዳዋና የጸጉሯ አንጸባረቂነትና ጠንካራነት ከጤነኛ ህጻናት ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም የሶፊ አይኖች ተከድነዋል።

ዕድሜዋ በአስራዎቹ ቢገኝም ከውስጥ ሱሪዋ ውስጥ ደግሞ የጽዳት መጠበቂያ (ዳይፐር) አድርጋለች።

ላለፉት 20 ወራት ስትመገብበት የነበረው ቱቦ ደግሞ በአፍንጫዋ በኩል ተተክሎላት ይገኛል።

ሶፊና ቤተሰቦቿ ከቀደሞዋ ሶቪየት ህብረት የመጡ ጥገኝነት ጠያቂዎች ናቸው።

እ.አ.አ ታህሳስ 2015 የመጡት እነሶፊ በማዕከላዊ ስዊድን በሚገኝ የስደተኞች ማቆያ ውስጥ ይኖራሉ።

“የደም ግፊቷ የተስተካካለ ነው” ይላሉ ዶክተርስ ኦፍ ዘ ዎርልድ ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት የሚያገለግሉት ዶ/ር ኤልሳቤት ሃልትክራንትዝ። “የልብ ምቷ ግን ከፍተኛ ነው። ዛሬ ብዙ ሰዎች ሊጠይቋት ስለመጡ ምላሽ እየሰጠች ነው” ብለዋል።

ሃልትክራንትዝ ሶፊ ሳታስብበት በተፈጥሮ የምትሰጣቸውን አካላዊ እንቅስቃሴዎችና ምለሾች ያጠናሉ። ሁሉም ነገር ግን በትክክለኛው መንገድ ይሰራል። ሆኖም ልጅቱ መንቀሳቀስ አትችልም።

ጡረታ ከመውጣታቸው በፊት ከአንገት በላይ ሃኪም የነበሩት ዶ/ር ሃልትክራንትዝ፤ ሶፊ አፏን እንኳን መክፈት አለመቻሏ ያሳስባቸዋል። ይህ አደገኛ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም በመመገቢያ ቱቦዋ ላይ ችግር ካለ መተንፈስ ሊያስቸግራት ይችላል።

ታዲያ መደነስ የምትወደው ልጅ እንዴት ለመንቀሳቀስ የሚሆን ጉልበት እንኳን አጣች?

“ጉዳዩን ለቤተሰቦቿ ሳስረዳ፤ የሶፊ ሰውነት ንቁ ከሆነው የአዕምሮዋ አካል ጋር ያለው ግንኙነት ተቋርጧል በሚል ነው” ብለዋል ሃልትክራንትዝ።

እነዚህን ህጻናትን የሚረዱት የህክምና ባለሙያዎች የሚስማሙበት ጉዳይ በሽታው የሚፈጥረው ተጽዕኖ ልጆቹ ራሳቸውን ከተቀረው ዓለም እንዲያርቁ ያደርጋቸዋል።

ለችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት ደግሞ ቤተሰቦቻቸው ወይም ቤተሰቦቻቸው እጅግ አስቸጋሪ ከሆነ ችግር የሸሹና ከባድ ግጭትን የተመለከቱ ናቸው።

የሶፊ ወላጆች ገንዘብ በህገወጥ መንገድ በማግኘት እና ከማፊያዎች ጋር ባላቸው መጥፎ ግንኙነት አስፈሪ ታሪክ አላቸው።

እ.አ.አ መስከረም 2015 ላይ የፖሊስ ዩኒፎርም በለበሱ ሰዎች መኪናቸው እንዲቆም ተደረገ።

“ተጎትተን ወጣን። እኔና እናቷ ስንደበደብ ሶፊ መኪና ውስጥ ሆና ሁኔታውን ስትከታተል ነበር” ሲል ሶፊ አባቷ ጉዳዩን ያስታውሳል።

ሰዎቹ የሶፊን እናት ሲለቋት ልጇን ይዛ ከአካባቢው ታመልጣለች። የሶፊ አባት ግን ማምለጥ አልቻለም ነበር።

“እኔን ይዘውኝ ከሄዱ በኋላ ምን እንደተፈጠረ ግን አላስታውስም” ይላሉ የሶፊ አባት።

የሶፊ እናት ልጇን ወደ ጓደኛዋ ቤት ይዛት ሄደች። ትንሿ ልጅ በጣም ተበሳጭታ ነበር። እያለቀሰች “እባካችሁ ሂዱና አባቴን ፈልጉት” እያለች ግድግዳውን በእግሮቿ እየደበደበች ትጮህ ነበር።

ከሶስት ቀናት በኋላ አባት ድምጹን ካለበት ያሰማ ሲሆን፤ ከሶስት ወር በኋላ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስዊድን እስከሚያቀኑ ድረስ በተለያዩ ጓደኞቻቸው ቤት እየተዘዋወሩ ቆይተዋል። ሲደርሱም ለአራት ሰዓታት በስዊድን ፖሊሶች ቁጥጥር ስር ነበሩ። የሶፊ ጤንነትም ወዲያው ነበር በፍጥነት እያሽቆለቆለ የሄደው።

“ከሁለት ቀናት በኋላ ቀደም ሲል ከእህቶቿ ጋር የምትጫወተውን ያህል እየተጫወተች አለመሆኑን ተገነዘብኩ” ትላለች በቅርቡ ሌላ ልጅ የምትጠብቀው የሶፊ እናት።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቤተሰቡ በስዊዲን እንደማይቆይ ተነገረው። የስደተኞች ቦርድ ስለጉዳዩ ሲያወራን ሶፊ ጉዳዩን ሙሉ ለሙሉ የሰማች ሲሆን ከዚያ በኋላ ግን መናገርም ሆነ መብላት አቆመች።

‘ሪዛይኔሽን ሲንድረም’ ስውዲን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሪፖርት የተደረገው እ.አ.አ በ1990ዎቹ ነበር። ከ2003 እስከ 2005 ባሉት ሁለት ዓመታት ከ400 በላይ ህሙማን ተገኝተዋል።

ብዙ ስዊድናዊያን በስደተኞች ምክንያት ስጋት በገባቸው ወቀት የእነዚህ “ምንም ፍላጎት የሌላቸው ህጸናት” ጉዳይ ትልቅ ፖለቲካዊ ትኩሳት ሆኗል።

ልጆቹ አውቀው ነው አልታመሙም የሚሉና ወላጆቻቸው መኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ልጆቻቸውን እየመረዙ ነው የሚሉ ሪፖርቶችም ወጥተዋል። ሆኖም እነዚህን ታሪኮች ማረጋገጥ አልተቻለም።

አጭር የምስል መግለጫ

የሶፊ እናት፣ እህትና አባት

ባለፉት አስር ዓመታት በሪዛይኔሽን ሲንድረም የተጠቁ ህጻናት ቁጥር ቀንሷል።

እ.አ.አ በ2015 እና 2016 በበሽታው የተጠቁ ህጻናት ቁጥር 169 መሆኑን የስዊድን ብሄራዊ የጤና ቦርድ አስታውቋል።

ከተወሰነ የዓለም ክፍልና ብሄር የመጡ ህጻናት በበሽታው የመያዛቸው ነገር ከፍተኛ ነው። በተለይ ደግሞ ከቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት፣ ባልካን፣ ሮማ እና በቅርቡ ደግሞ የያዚዲ ስደተኛ ልጆች ናቸው በብዛት የሚጠቁት።

ከስደተኛ ቤሰተብ ውጭ ያሉ እና ኤስያዊን በበሽታው የመያዛቸው ዕድል አነስተኛ ሲሆን አፍሪካዊያን ግን በችግሩ አልተጠቁም።

ከሶፊ በተለየ ሁኔታ ሌሎቹ በችግሩ የተጠቁት ህጻናት ለዓመታት በስዊዲን የኖሩ፤ ቋንቋውን የሚናገሩ እና ከኖርዲክ አኗኗር ጋር ራሳቸውን ያዋሃዱ ናቸው።

ከዚህ ቀደም ለምሳሌ በናዚ ማቆያ ጣቢያ ያሉ ሰዎችን ጨምሮ ሪዛይኔሽን ሲንድረንምን የሚመስሉ የተለያዩ ሽታዎች ተከስተዋል። በእንግሊዝም እ.አ.አ በ1990ዎቹ ፕሪቫሲቭ ሬፉሳል ሲንድረም የተባለ ተመሳሳይ በሽታ ተከስቶ ነበር። የተጠቂዎች ቁጥር አነስተኛ ከመሆኑም በላይ አንድም ስደተኛ በችግሩ አልተጠቃም።

“እስከምናውቀው ድረስ ከስዊድን ውጭ ችግሩ አልተከሰተም” ሲሉ የህጻናት ሃኪም ሆኑት አስትሪድ ሊንድግረን አስታውቀዋል። ሪዛይኔሽን ሲንድረምን ለመረዳት እንቅፋት የሆነው በጉዳዩ ላይ ጥናት አለመደረጉ ነው ይላሉ። በልጆቹ ላይ ምን እንደተከሰተ ማንም ክትትል አላደረገም። የምናውቀው በህይወት መኖራቸውን ብቻ ነው።

አጭር የምስል መግለጫ

ካርልሻመር፡ በሽታው ከስደተኝነት ጋር ሳይሆን ካለፈ ስቃይ ህይወት ጋር የሚያያዝ ነው

ለሶፊ ወላጆች ግን ይህ ከባድ ነው። ባለፉት 20 ወራት በልጃቸው ላይ ምንም ለውጥ አላዩም። ሙሉ ለሙሉ ጊዜያቸውን በሶፊ ፕሮግራም የተያዘ ነው። ጡንቻዎቿ ሙሉ ለሙሉ እንዳይዝሉ አነስተኛ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማሰራት፤ በተሸርካሪ ወንበር ይዘዋት መዞር እና መመገብ ደግሞ የሚጠበቅባቸው የዕለት ተዕለት ተግባር ነው።

በደቡብ ስዊድን የምትገኘው ስካራ ከተማ መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ ህጻናቱን ከሪዛይኔሽን ሲንድረም ማዳን ይቻላል።

“ከእኛ ዕይታ አንጻር ይህ በሽታ የሚከሰተው ከስደት ጋር በተያያዘ ሳይሆን ቀደም ሲል ካጋጠመ ችግር ወይም አደጋ ጋር የሚገናኝ ነው” ሲሉ የሚገልጹት በሶልሲዳን ህጻናት ማቆያ የግርይኒንግ ሄልዝ ከፍተኛ የማህበረሰብ ሠራተኛ አኒካ ካርልሻምሬ ናቸው።

ህጻናት በወላጆቻቸው ላይ ጥቃት ወይም ማስፈራሪያ ሲመለከቱ በህይወታቸው ያለው ወሳኙ ግንኙነት ይቆራረጣል ይላሉ በሶለስደን የሚገኙ የህጻናት ተንከባካቢዎች።

“ከዛ በኋላ ህጻናቱ እናቴ ልትንከባከበኝ አትችልም የሚል ግንዛቤ ይይዛሉ። በዚህም በወላጆቻቸው ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ጥገኛ የነበሩ በመሆናቸው ተስፋ ይቆርጣሉ። ይህ ሲከሰት ድጋፍ ለማግኘት ወደማን እና ወዴት ሊያዩ ይችላሉ?” ይላሉ ካርልሻመር።

ይህ የቤተሰብ ትስስር በድጋሚ ሊገነባ ይገባዋል። ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ግን ልጆቹ እንዲያገግሙ ማድረግ ነው። የሶልሲዳን የመጀመሪያ እርምጃም ልጆቹን ከቤተሰቦቻቸው መለየት ነው።

“ያላቸውን ለውጥ ለቤተሰቦቻቸው እንነግራቸዋል። ሆኖም ልጆቹ በሠራተኞቻችን ላይ እንደዲደገፉ ስለምንፈልግ እንዲያወሯቸው አንፈቅድም። ልጆቹን አንዴ ከለየናቸው በኋላ ግን የመጀመሪያውን ምልክት ለማየት ጥቂት ቀናት ብቻ ናቸው የሚያስፈልጉት። ይላሉ።

ስለስደተኞች የሚካሄዱ ውይይቶችም በልጆች ፊት አይወሩም።

“በራሳቸው መጫወት እስከሚችሉ ድረስ እኛ እንጫወትላቸዋለን፤ እንደንሳለን፤ ሙዚቃ እንሰማለን። ለምሳሌ ጥቂት ኮካ ኮላ አፋቸው ላይ ጠብ እያደረግን የጣፋጭን ጣዕም እንዲቀምሱ እናደርጋቸዋለን። ገና ምግብ በአፍንጫቸው እየወሰዱ ራሱ ማዕድ ቤት ወስደን ምግቡን እንዲያሸቱ እንደርጋለን”

“በህይወት የመቆየት አቅማቸው አብሯቸው እንዳለ እናምናለን። ግን እነርሱ አቅማቸውን ዘንግተውት ሊሆን ይችላል።በእርግጥ ይህን ማድረግ ከፍተኛ ኃይል ይፈልጋል ምክንያቱም ልጆቻቸው በራሳቸው መኖር እስኪጀምሩ እኛ እንኖርላቸዋለን”

አንድ ጨቅላ ለማገገም የሚፈጅበት ረጅሙ ጊዜ ስድስት ወር ነው።

(የቤተሰቦቿን ማንንት ለመጠበቅ የሶፊ ስም ተቀይሯል)

Read more