እጅግ ዝቅተኛ መጠን ያለው ሕዝብ የተሳተፈበት የኬንያ ምርጫ ውጤት ይፋ ሆነ

https://www.bbc.com/amharic/41805702

እጅግ ዝቅተኛ መጠን ያለው ሕዝብ የተሳተፈበት የኬንያ ምርጫ ውጤት ይፋ ሆነ

  • 30 ኦክተውበር 2017

uhuru kenyata won hte repeat election in 2017Image copyright
TONY KARUMBA

በድጋሚ እንዲካሄድ በፍርድ ቤት የታዘዘው የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዝቅተኛ የመራጮች ቁጥር የተሳተፉበት ሲሆን ለሰዎች ሞት ምክንያት የሆነ ግጭትንም አስተናግዷል።

በአራት አካባቢዎች በምርጫው ዕለት የተቃዋሚ ደጋፊዎች ከፖሊስ ጋር በመጋጨታቸው ምርጫው ላልተወሰነ ጊዜ ድረስ እንዲዘገይ ተደርጓል።

ቢሆንም የኬንያ ምርጫ ቦርድ ኃላፊ ዋፉላ ቼቡካቲ ዕለተ ሰኞ አመሻሽ ላይ የምርጫውን ውጤት ይፋ አድርገዋል።

በዚሀም መሠረት የጁቢሊ ፓርቲን ወክለው የተወዳደሩት ፕሬዝደንት አሁሩ ኬንያታ ምርጫውን በድጋሚ 98 በመቶ ድምፅ በማምጣት አሸንፈዋል።

በምርጫው ለመሳተፍ ከተመዘገበው 19 ሚሊዮን ያህል ሕዝብ መካከል 38 በመቶ ወይንም ከ8 ሚሊዮን በታች የተሳተፈ ሲሆን ከዚህም መካከል 7 ሚሊዮን አካባቢ መራጭ አሁሩ ኬንያታን መምረጡን ቦርዱ አስታውቋል።

በወርሃ ነሓሴ በተደረገው ምርጫ ከተመዘገቡት መራጮች መካከል 77 በመቶ ያህሉ እንደተሳተፉ የሚታወስ ነው።

Image copyright
SIMON MAINA

ቦርዱ ምርጫው ነፃ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ እንደነበርም አስታውቋል።

ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲው ናሳ በምርጫ ውጤቱ ካልተስማማ በሰባት ቀናት ውስጥ ቅሬታውን ለሃገሪቱ ፍርድ ማሰማት እንዳለበትም ታውቋል።

አስፈላጊ መስፈርቶች አልተሟሉም በሚል ምርጫውን ውድቅ ያደረጉት የናሳው መሪ ራይላ አዲንጋ ግን በነገው ዕለት ቀጣይ እርምጃቸውን ይፋ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

Read more