የቀይ ሽብር ተከሳሹ ሄግ ፍርድ ቤት ቀረበ

https://www.bbc.com/amharic/news-41806711

  • 30 ኦክተውበር 2017

የቀይ ሽብር ሰለባዎች ፎቶImage copyright
Getty Images

የቀድሞው የኢትዮጵያ ወታደራዊ መሪ ረዳት ነበር የተባለው ግለሰብ የጦር ወንጀል የፍርድ ሂደት በኔዘርላንድስ ሄግ መታየት ጀመረ።

የ63 ዓመት ዕድሜ ያለው አቶ እሸቱ አለሙ የተባለው ግለሰብ ወታደራዊው መንግሥት ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ተቀናቃኞቹን ለመምታት ባካሄደው ‘የቀይ ሽብር’ ዘመቻ ወቅት 75 ሰዎች እነዲገደሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል ተብሎ ነው የተከሰሰው።

የቀድሞው ኮሚኒስት መሪ መንግሥቱ ኃይለማሪያም ረዳት ነበር የተባለው ይህ ግለሰብ በሰዎች ላይ ሰቆቃን በመፈፀምና በከፋ አያያዝ ውስጥ እንዲቆዩ በማድረግ ጭምር ተከሷል። ነገር ግን የቀረቡበትን ክሶች በሙሉ እንዳልፈፀመ ተናግሯል።

በቀረቡበት አራት የጦር ወንጀሎች ከ300 የሚበልጡ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ስም ዝርዝርም ቀርቧል።

ኢትዮጵያ ውስጥም በሌለበት በቀረበበት ክስ ሞት ተፈርዶበታል።

አቃቤ ሕግ እንደሚለው ኢትዮጵያዊና የደች ጥምር ዜግነት ያለው አቶ አለሙ ጎጃም ክፍለ ሃገር ውስጥ የመንግሥቱ ኃይለማሪያም ቀንደኛ ደጋፊ በመሆን አገልግሏል።

በኔዘርላንድስ ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደቱ ሲከፈት አቶ እሸቱ አለሙ ”አቃቤ ሕግ የተሳሳተ ሰው ላይ ነው ክስ እየመሰረተው” ሲል ተናግሯል።

”አቃቤ ሕግ አደረግከው ብሎ ያቀረበውን ክስ ስሰማ በጣም ነበር የደነገጥኩት፤ የቀረቡብኝን ክሶች በሙሉ አልፈፀምኩም” በማለት ነበር ጉዳዩን ለሚመለከቱት አራት ዳኞ የተናገረው።

አቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ እንዳለው አቶ አለሙ ”በአንድ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ 75 የሚሆኑ እስረኞች እንዲገደሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል።” የሟቾቹም አስከሬን በአንድ የጅምላ መቃብር ውስጥ እንዲቀበር አድርጓል ይላል ።

በተጨማሪም አቶ አለሙ ”ሰላማዊ ሰዎችን እና ትጥቅ የፈቱ ተዋጊዎችን ያለፍርድ እንዲታሰሩና በጭካኔ አያያዝ ስር እንዲቆዩ አድርጓል” የሚል ክስ ቀርቦበታል።

በክሱ እስረኞች እጅና እግራቸው ታስሮ እንዲንጠለጠሉ በማድረግ የውስጥ እግራቸው በዱላ እንዲገረፉ አድረጓልም ተብሏል።

በዚህ የፍርድ ሂደትም የሰቆቃው ሰለባዎች ናቸው የተባሉ ሰዎች በምስክርነት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Read more