የቤንሻንጉል ጥቃት ሰለባዎች ወደመኖሪያቸው መመለስን ፈርተዋል።

https://www.bbc.com/amharic/41799605

የቤንሻንጉል ጥቃት ሰለባዎች ወደመኖሪያቸው መመለስን ፈርተዋል።

  • 30 ኦክተውበር 2017

MapImage copyright
Google

ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 16 ቀን በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ካማሽ ዞን ሃሮ ዴዴሳ ቀበሌ የተቀሰቀሰውና ለሕይወት መጥፋት እንዲሁም ለንብረት መውደም ምክንያት የሆነው ግጭት ግላዊ ጠብ የጫረው ነው ቢባልም ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጥቃቱ ሰለባዎች ግን ማንነታቸው ላይ

ያነጣጠረ መሆኑን ይናገራሉ።

በተለያዩ ጊዜያት ከምዕራብ ጎጃም ዞን ለስራ ወደአካባቢው አቅንተው ኑሯቸውን በመሰረቱ የአማራ ተወላጆች እና በጉሙዝ ብሔረሰብ አባላት ውጥረቶች እና ግጭቶች አዲስ ያለመሆናቸውን የሚያስረዱት የጥቃቱ ሰለባዎች ከሁለቱም ወገን ሰዎች መሞታቸውን ይገልፃሉ፤ ከሟቾቹ መካከል

የኦሮሞ ተወላጆችም ይገኙበታል ተብሏል።

በግጭቱ ማግስት የአማራ ክልል የብዙኃን መገናኛ ድርጅት የቤንሻንጉል ክልል የኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑትን አቶ መንግስቱ ቴሶን ጠቅሶ ባቀረበው ዘገባ ክስተቱን ወደግል ጠብ ዝቅ አድርጎት እንደነበር ይታወሳል።

በ1997 ዓ.ም ከከሰላ አካባቢ ስራ ፍለጋ ወደስፍራው ካቀና በኋላ ኑሮውን በቀበሌው ደናባ ጎጥ የመሰረተው የ36 ዓመቱ ባይህ ታፈረ በግጭቱ የተገደሉ ሰባት ሰዎችን አስከሬን መመልከቱን ይናገራል፤ ሟቾቹ ስድስቱ የአማራ አንዱ ደግሞ የጉሙዝ ተወላጆች ናቸው።

ባይህ በደረሰባቸው ድብደባ ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ የገጠማቸውን የስምንት እና የአስራ አንድ ዓመት ልጆቹን በነቀምት አጠቃላይ ሆስፒታል በማስታመም ላይ የሚገኝ ሲሆን በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት “ወደአገራችሁ እንመልሳችኋለን” የሚል ዛቻ ከአገሬው ሰው ጎልቶ ይሰማ ነበር ይላል፤

ይህ መንፈስም ከሌሎች ቦታዎች የመጡ ናቸው የተባሉ ሰዎች ላይ ጥቃት እንዲነጣጠር ምክንያት ሆኗል ሲል ያምናል።

“በየጠላ ቤቱ፣ በየአረቄ ቤቱ ብናባርራችሁ መንግስት መለሳችሁ፤ አሁንም ግን ዋጋችሁን እንሰጣችኋለን ይሉናል” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል፤ “መንግስት መሳሪያችን ቢነጥቀንም ቀስትና ጩቤ አለን ሁሉ እንባላለን።” ይላል ባይህ

የቤንሻንጉል ክልል በሕገ መንግስቱ መሰረት “ነባር ሕዝቦች” ናቸው በሚል ዕውቅና የሰጣቸው ለበርታ፣ ጉሙዝ፣ሽናሻ፣ ማዖ እና ኮሞ ብሔሮች ሲሆን “መጤ” ናቸው ከሚባሉ የሌላ ብሔር ተወላጅ ሕዝቦች ጋር ግጭቶች ሲፈጠሩ አሁን የመጀመሪያው አይደለም።

በ2006 ዓ.ም በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ጥቃትን በመሸሽ ከአካባቢው ተፈናቅለው በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም አካባቢ ሰፍረው የቆዩ ሲሆን፤ ቆይቶም ወደክልሉ እንዲመለሱ መደረጋቸው ይታወሳል።

የቤንሻንጉል ክልል የኮሚኒኬሽን ጽሐፈት ቤት ኃላፊው አቶ መንግስቱ የተከሰተው ግጭት የብሔር መልክ የለውም ይበሉ እንጅ፤ የሃሮ ደዴሳ ገብርዔል ቤተክርስትያን አስተዳዳሪ የሆኑት ቄስ እንኳሆነ ቸሬ “ምንም በማናውቀው ጉዳይ መደብደባችን ወገን ናችሁ ቢባል ነው እንጅ” በማለት

ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቄስ እንኳሆነ ከልጃቸው ጋር ወደስራ በሚሄዱበት ሰዓት በድንገት ጥቃት እንደደረሰባቸው ነው የሚናገሩት።

ከባድ ድብደባ ለሕይወቱ የሚያሰጋ ሁኔታ የዳረገው ልጃቸው ሆስፒታል ውስጥ ይገኛል።

ባይህ ጥቃት አድራሾቹ በሕፃናት ላይ እንደሚበረቱ ይናገራል፤ “ልጆቻችን እዚሁ ተወልደው ስላደጉ ጉምዝኛ ቋንቋ ችለዋል። እነርሱ ይሄንን አልወደዱትም፤ ቋንቋችንን ሰረቃችሁን ይላሉ” ብሏል።

እርሱና መሰል የአማራና የኦሮሞ ተወላጆች መሬት በመከራየትና እርሱን አርሰው የመሬት ባለቤት ከሆኑ የአካባቢው ተወላጆች ጋር ምርቱን በመካፈል እንደሚተዳደሩ ሲያስረዳ “ውል እንገባለን። በውሉ መሰረት ተስማምተን፤ ሽማግሌ አስቀምጠን ነው የምንሰራው። ውሉን ከፈፀምን በኋላ

የእነርሱን ድርሻ እንሰጣለን። የራሳችንንም እንወስዳለን። ይህ ሲሆን ግን ጎጃሜ እኛ አገር መጥቶ ለምን ይደሰታል ነው የሚሉት” ይላል።

በስራ መካከል ግጭቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ በሽማግሌዎች የማይፈታ ከሆነ በጎጥና በቀበሌ የአስተዳደር አካላት ፍትህን ማግኘት አዳጋች ነው ይላል።

ቄስ እንኳሆነ የቀጣይ ቀናት እርምጃቸውን ማሰብ አይፈልጉም፤ ትኩረታቸው ሁሉ የልጃቸው ጤና መመለስ ላይ ነው። “ከዚያ ወዲያ ያለውን እግዚያብሄር ነው የሚያውቀው ። ደውለን ስንጠይቅ አሁንም ብዙ ሰዎች ጫካ እንዳሉ ናቸው። ያለዕህል ውሃ መመለስ ፈርተዋል” በማለት ይናገራሉ።

ባይህ ደግሞ ወደነቀምት ከመጣ በኋላ የቅርብ ጎረቤቱን ጨምሮ አራት ሰዎች -ሁለት የአማራ ተወላጆች እና ሁለት ከእነርሱ ጋር አብረው የሚሰሩ የኦሮሞ ብሔር አባላት- በቢላዋ ተወግተው ተገድለው እንደተገኙ በስልክ ከወዳጆቹ መስማቱን ያብራራል።

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ያፈራውን ንብረት ሙሉ ለሙሉ እንደተዘረፈ የሚናገረው ባይህ ፤ ወደቤንሻንጉል ክልል የመመለስና ሕይወቱን ዳግም የመገንባት ፍላጎት የለውም።

“የቀረችኝን ነገር ለቃቅሜ ሕይወቴን ይዤ ከዚህ ቦታ መውጣት ነው የምፈልገው።” ይላል

Read more