በምንዛሪው ጦስ – በአዲስ አበባ 39 የንግድ ድርጅቶች ታሸጉ

በአዲስ አበባ 39 የንግድ ድርጅቶች፣ የዶላር ምንዛሪ ለውጡን ተከትሎ፣ ምርት በማከማቸት፣ ያለንግድ ፈቃድ በመነገድ፣ ዋጋ በመጨመር፣ አገልግሎቱ ያለፈበት መድኃኒት በማከማቸትና አየር በአየር በመሸጥ ምክንያት በሚል ታሽገዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገመቺስ መላኩ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ጨምረው እንዳመለከቱት፤ ህገ ወጥ የተባሉ 23 ነጋዴዎች ደግሞ መንግሥት በድጎማ የሚያቀርባቸውን እንደ ዘይት ስኳር ስንዴ የመሳሰሉትን መሰረታዊ ሸቀጦች ሲሸጡ ተገኝተዋል በሚል ሸቀጦቻቸው ተወርሰዋል።
ከመሰረታዊ ሸቀጦች ውስጥ ስኳር፣ ስንዴና ዘይት በመንግሥት በኩል እንደሚቀርቡና ነዳጅም እንደሚደጎም ኃላፊው ጠቅሰው፤ በነዚህ ምርቶች ላይ ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ እንደማይደረግ ተናግረዋል፡፡
እንደሳቸው አባባል በመንግስት አማካይነት እሚከፋፈለው ምርት ከውጭ ተገዝቶ አገር ውስጥ እስከሚገባ ድረስ ቢያንስ ሁለት ወራት ይፈጃል፡፡