ብአዴን ሙስና ፈጽመዋል ተብለው የተጠቆሙ አመራሮችን መቅጣት ጀምሬያለሁ አለ

ብአዴን ሙስና ፈጽመዋል ተብለው ጥቆማ የተደረገባቸውን 857 መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮች በማጣራት ተጠያቂ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለምነው መኮንን የሕዳር 11 በዓል አከባበርን አስመልክተው ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሉት፣ ብአዴን አመራሩ የተሰለፈበትን ዓላማ የመሳት ችግር አጋጥሞት ነበር።

በተለይ ከሙስናና ብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘ ሕዝቡ በመሪዎቹ ላይ ከባድ ጥርጣሬ አሳድሮ ስለነበር ብአዴን ችግሩን ለማጣራት ሰፊ ሥራ ሰርቷል።

በእዚህም መሠረት 117 የሚሆኑ ከፍተኛ አመራሮች ተጠያቂ ሆነው መገኘታቸውን ገልጸው፣ ከእነዚህ ውስጥ 42 በመቶ የሚሆኑት መሬት ያለአግባብ በመውሰድ፣ ከግብር ስወራና በዝምድና ከመቅጠር ጋር በተያያዘ ችግር ውስጥ መግባታቸው ተረጋግጧል።

ሙስና እንደሚፈጽሙ ጥቆማ ከደረሰባቸው 740 መካከለኛ አመራሮችም 355ቱ መሬትን ደራርበው በመውስድና በመሰል ችግሮች ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውን አስታውቀዋል።

በሙስና ችግር ውስጥ የተገኙትን ከኃላፊነት ቦታቸው የማንሳትና ዝቅ ብለው እንዲመደቡ እንዲሁም በሙስና ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በህግ እንዲታይ በመደረግ ላይ መሆኑን አብራርተዋል።