ፍሬነገር – ከጠቅላይ ሚ/ር ኃ/ማርያም መግለጫ

ስለ ኦሮምያን ሶማሌ ክልሎች ግጭትና ስለ ውጭ ምንዛሪ እጥረት በሰሞኑ መግለጫቸው ከተናገሩት የሚከተሉት ፍሬነገሮች ይገኙበታል።

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልሎች አጎራባች ዞኖች አካባቢ በተከሰተው ግጭት በጣም አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ በርካታ የሰው ህይወት ጠፍቷል። ከፍተኛ ንብረት ወድሟል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ተፈናቅለዋል።  የሞቱበትና የተፈናቀሉበት ሁኔታ አለ።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት በቅርቡ ባደረገው ስብሰባ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል እቅድ አውጥቷል።  የፖለቲካ አመራሩ ከላይ እስከታች በግጭቱ ውስጥ የተሳተፉ አካላትንና ይህንን ጉዳይ በዘላቂነት ለመቆጣጠር የሚያስችል የጸጥታና የህግ ማስከበር ሥራ ማከናወን እንዳለበት ወስነን እቅድም አውጥተን ከዚህ ሳምንት ጀምሮ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

በህገወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት በተለይም ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደረጉ አብዛኞቹ በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል። የቀሩትም በቀጣይ በምንሠራቸው ሥራዎች በቁጥጥር ስር የሚውሉ ይሆናሉ። ወደህግም ቀርበው ተጠያቂ ይደረጋሉ።

የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል ግጭቶች መከሰታቸው ምክንያቱ በኦህዴድና ሶህዴፓ መካከል ችግሮች ስለነበሩ ሳይሆን የክልሉ አመራሮች በተለይም የመንግሥት አመራሮች አካባቢ የተያዘው አቋም የተሳሳተ በመሆኑ ነው። የተሳሳተ አቋም ያልኩበት ዋናው ምክንያት ማንኛውም የሀገሪቱ ከፍተኛ አመራር በየትኛውም አካባቢ ያለ ህዝብ የኔ ህዝብ ነው ብሎ ህዝብን በእኩል ዓይን የማየት ግዴታ አለበት። ይሄ የኔ ህዝብ ነው፤ ያ ሌላ ህዝብ ነው ብሎ የሚከፋፍል አመራር ካለ በመጀመሪያ ደረጃ የተሳሳተና ለግጭት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው። ስለዚህ ይሄ የሶህዴፓና የኦህዴድ ችግር ብቻ ሳይሆን በመላው የኢህአዴግ መዋቅር ያሉ አመራሮች የተሳሳተ አስተሳሰብ በሚኖራቸው ጊዜ የሚይዙት አቋምና አመለካከት ነው። እዚህ አቋምና አመለካከት ላይ በድርጅታችን ባህል መሰረት ሰፊ ትግል አካሂደናል፤ ይሄ ስህተት መሆኑም በሁሉም ዘንድ መግባባት ተፈጥሯል። ይሄ በአመራሩ አመለካከት ላይ ያለ ችግር እንጂ የኦህዴድ ወይም የሶህዴፓ የተለየ ችግር ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፤ አይገባምም።

ይሄ በጣም መሰረታዊ ነው። በተለይም ሀገራችን የጀመረችውን የልማት፣የመልካም አስተዳደር ማስፈን ጉዞ በተጠናከረ ሁኔታ ለማስቀጠል ካስፈለገ በየትኛውም አካባቢ ያለ አመራር ከኢትዮጵያ አንደኛው ጫፍ ወደሌላኛው ጫፍ ያለውን ህዝብ፤ የአፍሪካ ቀንድ ህዝብ፣ የመላው አፍሪካ ህዝብ፣ የመላው ዓለም ህዝብ እንደ ህዝብ በአንድ ዓይን በእኩል ዓይን መታየት አለበት። ስለዚህ የተለየ ጠበቃ ሆኖ ሊቆም የሚችል ሊኖር አይገባም።

ስለ ውጭ ምንዛሬ እጥረት

ላለፉት ሃያ ዓመታተ በተከታታይ ስድስት ጊዜ የውጭምንዛሬ ተመን ለውጥ በሚያደርግበት ጊዜ ተሞክሮዎቹን በማየትና አገራችን አሁን ከደረሰችበትን የኢኮኖሚ ደረጃ በደንብ መፈተሽ ያለብን መሆኑን አይተናል።

የውጭ ምንዛሬ ተመኑን ተከትሎ በአገር ውስጥ ደግሞ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ከውጭ የሚገቡ የፋብሪካ ምርቶች ዋጋ በውጭ ምንዛሬ ተመን መሻሻል ልክ ስለሚያድግ ኅብረተሰቡን ሊጎዳ ይችላል። ይህን ለማረጋጋት የሚያስችሉ ዕርምጃዎችን ወስደናል። ከዚህ በፊትም ስናደርግ እንደነበረው በዋና ዋና የፍጆታ እቃዎች ላይ የአቅርቦት ማሻሻል ማምጣት አለብን ብለን ሠርተናል። ከዚህ አኳያ ሌሎቹ ዋና ዋና የፍጆታ እቃዎች አቅርቦት በታቀደው መሰረት እየሄደ ያለም ቢሆን ከስኳር አኳያ ያጋጠመን ከፍተኛ ችግር እንዳለ እንገነዘባለን።

የተፈጠረውን ጉድለት ለማካካስ ጥረት እያደረግን እንገኛለን። ከውጭ የስኳር ምርት ካስገባንም በኋላ በስርጭቶች አካባቢ ወደ ኅብረተሰቡ በቀላሉና በፍጥነት ሊደርስ ባለመቻሉ የተፈጠረ መስተጓጎልም አለ። ይህንንም በጥቂት ቀናት ውስጥ ማስተካከል እንደምንችል አይተናል። ስኳር ለአንድ ወር በተዛባ ሁኔታ ሲሰራጭ ከቆየ በኋላ ወደዋናው መስመር ለማስገባት በሚደረግ ጥረት የተወሰኑ መመሰቃቀሎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ የታወቀ ነው።

ህዝቡ ብዙ ቀናትና ሳምንታት በስኳር እጥረት እየተሰቃየ ከቆየ በኋላ አሁን ምንአልባትም እጥረት ይገጥመኛል በሚል ከፍተኛ የሆኑ ሰልፎችና የመሳሰሉት ሁኔታዎች ቢፈጠሩ የሚገርም አይሆንም።

የፋብሪካ ሸቀጦችን አሁን ባለው ሁኔታ ከውጭ እቃዎችን ለማስገባት ቢያንስ ሁለት ወር ይፈጃል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ማንም የንግዱ ህብረተሰብ ከውጭ ያስገባበት ሁኔታ በሌለበት በነባር እቃዎች ላይ ዋጋ መጨመር ህገወጥ ነው። ህገወጥነትንም ለመከላከል መንግሥት እርምጃዎችን መውሰድ ጀምሯል። በዚህም መሰረት ዋጋቸውን ወደነበረበት የመለሱ አሉ። እንዲሁም ጊዜ በመጠበቅ ሱቃቸውን ዘግተው እቃ ላለማቅረብ የወሰኑ አሉ። እነዚህን ተከታትለን እርምጃ የምንወስድ ይሆናል።

በተለይ ደግሞ የብረት ዋጋ ወደ39 በመቶ እንዲያድግ ያደረጉ የብረት አምራቾችና ነጋዴዎች ጋር ውይይት አካሂደናል። እናስተካክላለን ብለው ከሄዱ በኋላ አላስተካከሉም። ስለዚህ የማያዳግም እርምጃ በዚህም አካባቢ የምንወስድ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ እገልጻለሁ። የንግድ ፈቃዳቸውን እስከመንጠቅ ከዚያም አልፎ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ወደፍርድ ቤት አቅርበን የምናስቀጣቸው መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል።