ኢትዮጵያ የኩባንያውን ጤፍ የማቀነባበር መብት ለማሰረዝ የጀመረችውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ትቀጥላለች:: ህዳር 7/2010

አዲስ አበባ  የሆላንዱ ኩባንያ ከአውሮፓ ፓተንት ቢሮ ያገኘውን ጤፍ የማቀነባበር የባለቤትነት መብት ለማሰረዝ ኢትዮጵያ በጀመረችው ዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንደምትቀጥል ተገለጸ።

 ኩባንያው ያገኘውን የፓተንት መብት ማሰረዝና የኢትዮጵያን የጤፍ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ የተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ ዛሬ በአዲስ አበባ ስብሰባውን አካሂዷል።

 በ2006 ዓ.ም የተዋቀረው ኮሚቴው የሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ የውጭ ጉዳይ፣ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ጨምሮ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩትና የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣንን አካቷል።

 የዛሬ የኮሚቴው ስብሰባ ድርጅቱ ያገኘውን የጤፍ ባለቤትነት መብት ለማሰረዝ ሲደረግ የቆየውን እንቅስቃሴ በተጠናከረ መልኩ  ለማስቀጠል ታስቦ የተካሄደ ነው።

 እ.ኤ.አ በ2005 በኢትዮጵያና ሄልዝ ኤንድ ፐርፎርማንስ ፉድ ኢንተርናሽናል በሚባል የኔዘርላንድ ድርጅት መካከል በተደረገ ስምምነት በ12 ዓይነት የኢትዮጵያ የጤፍ ዝርያዎች ላይ ምርምር እንዲያደርግ ተፈቅዶለት ነበር።

 ስምምነቱ ለድርጅቱ ጤፍ መሰል አዲስ ምርት እንዲያበለፅግና ምርቱንም ለአውሮፓ ገበያ እንዲያቀርብ የሚፈቅድ ነበር ተብሏል።

 በዚህም ድርጅቱ ከሚያገኘው ጥቅም ቀላል የማይባለውን ድርሻ ለኢትዮጵያ እንዲያጋራ ነው ስምምነት የተደረሰው።

 ነገር ግን ከስምምነቱ የተጠበቀው ውጤት ባለመገኘቱ ኢትዮጵያ እስካሁን ያገኘችው 4 ሺህ ዩሮ ብቻ በመሆኑ የምርምር ፕሮጀክት ስምምነቱም ተቋርጧል።

 ድርጅቱ እ.ኤ.አ 2009′ ኪሳራ ደርሶብኛል’ በሚል ሰበብ ስራውን አቁሟል፤ ነገር ግን ቀደም ብሎ ከአውሮፓ የፓተንት ቢሮ ጤፍን  በዱቄት፣ በቡኬትና ሌሎች ጤፍ መሰል መልኩ አቀነባብሮ የመሸጥ መብት አግኝቷል።

 በመቀጠልም ድርጅቱ ከመዘጋቱ በፊት ያገኘውን የፓተንት መብት ሙሉ በሙሉ ፕሮ ግሬን ኢንተርናሽናል ለተባለ ድርጅት መሸጡን የገለፀ ቢሆንም የድርጅቱ ገዥዎች ከሰርኩ ያለው ድርጅት አመራሮች ናቸው።

 አዲስ የተቋቋመው ድርጅት የጤፍ ፓተንትም በታላቋ ብሪታኒያ፣ ቤልጂየም፣ ጣልያን፣ ኦስትሪያና ጀርመን ተቀባይነት አግኝቶና በአውሮፓ የፓተንት ቢሮ ፈቃድ ተሰጥቶት መጠቀም ከጀመረ ስድስት ዓመት ገደማ ሆኖታል።

 ኢትዮጵያም በአሁኑ ወቅት የድርጅቱ የጤፍ ማቀነባበር ፓተንት እንዲሰረዝ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።

 የሳይንስና ቴክኖሎጆ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ እንደተናገሩት ድርጅቱ ያገኘውን የጤፍ ማቀነባበር የባለቤትነት መብት ለማሰረዝ የተጀመረው የዲፕሎማሲ ስራ ይቀጥላል።

 ኮሚቴው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ፓተንቱ እንዲሰረዝ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የተሄደበት ርቀት የሚፈለገውን ያህል አለመሆኑንና የዲፕሎማሲ አማራጩን አሟጦ መጠቀም እንደሚገባ ከስምምነት መደረሱን ገልጸዋል።

 በዚህም መሰረት የፓተንት መብቱን ከያዘው የሆላንዱ ኩባንያ ፕሮ ግሬን ኢንተርናሽናል ጋር ድርድር እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ አገራት በሚገኙ ኤምባሲዎቿና ከወዳጅ አገራት ጋር በመሆን ድርድር እንደምታደርግና የዲፕሎማሲ ስራው በአንድ ወር ጊዜ እንደሚጀመርም ነው ሚኒስትሩ የጠቆሙት።

 በድርድሩ ኢትዮጵያ የጤፍ መገኛ መሆኗን የሚያሳዩ ጥናቶች፣ ሰነዶችና መረጃዎችን ለድርጅቱ አመራሮች አቅርቦ በማስረዳት አገሪቷ የምርቱ መገኛ መሆኗንና የፓተንቱ መብት ባለቤት አለመሆኑን እንዲቀበል የማድረግ የድርድር ስራ እንደሚከናወን አስረድተዋል።

 የድርጅቱ የጤፍ ፓተንት መብት የማስመዝገብ ጥያቄ በጃፓንና በአሜሪካ የፓተንት ቢሮ ውድቅ መሆኑን አስታውሰው ተቋማቱ ጥያቄውን ውድቅ ያደረጉበት የተለያዩ መረጃዎች በድርድሩ ወቅት ለኩባንያው እንደሚቀርብ አክለዋል።

 የሆላንድ መንግስት ከሶስት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ የምትከተለውን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ እንደሚደግፍና ከአገሪቷ ጎን መሆኑን ማረጋገጡንም ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን አስታውሰዋል።

 የዲፕሎማሲው መንገድ ካልተሳካ መንግስት በሚወስነው ውሳኔ ኢትዮጵያ ድርጅቱን በፍርድ ቤት እንደምትከስና ሂደቱንም ለማሸነፍ  ከፍተኛ እድል እንዳላት ተናግረዋል።

 በህጋዊ መንገድ የፍርድ ሂደቱን ማሸነፍ የሚቻልበት በቂ መረጃ እንዳለና በክሱ የሚከፈለው ገንዘብ ጤፍ ለአገሪቷ ብሔራዊ የማንነት መገለጫ ከመሆኑ አንጻር ከግምት ውስጥ የሚገባ እንዳልሆነም አመልክተዋል።

 የድርጅቱ የፓትንት ባለቤትነት ኢትዮጵያ ጤፍና የጤፍ ምርቶችን ለአውሮፓ ገበያ ለማቅረብ እንቅፋት እንደሆነባት ገልጸው የፓተንቱ መሰረዝ አገሪቷ ወደ አውሮፓ ገበያ የጤፍ ምርቷን ለመላክ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ጠቅሰዋል። 

 የጤፍ የፓተንት ጉዳይ መንግስት ብዙ ትምህርት የወሰደበትና በቀጣይ በጄኔቲክ ሀብቶች ዙሪያ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የሚደረግ ስምምነት በከፍተኛ ጥንቃቄና በትኩረት እንዲሆን የሚያደርግ እንደሆነም ገልጸዋል።

 የጤፍ ምርታማነትን በማሳደግ ለተለያዩ አገራት ኤክስፖርት የማድረግ ጉዳይ በቀጣይ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ እንደሆነም የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

 ኢትዮጵያ የጄኔቲክ ሀብቶቿ እንዲጠበቁ የሚያስችሉ ዓለም አቀፍ አዋጆችና ስምምነቶችን በመቀበል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማስፀደቅ ስራ በዚህ ዓመት በትኩረት አቅጣጫነት ከተያዙ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው እንደሆነም ተናግረዋል። Read more http://www.ena.gov.et