ሳይንስና ቴክኖሎጂ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው – ጠ/ ሚ/ር ሃይለማሪያም ደሳለኝ:: ህዳር 09፤2010

ሳይንስና ቴክኖሎጂን ማሳደግ ሃገሪቱ ከድህነት ለመውጣት ለምታደርገውን ጥረት ቀልፍ መሳሪያ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም በ8ኛው ሀገር አቀፍ የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሽልማት ስነ ስርዓት ላይ እንደገለጹት የሽልማት ስነ ስርዓቱ መልካም ስራ የሰሩ ዜጎችን ይበልጥ ለማነሳሳት ያለመ ነው፡፡

በተሸላሚዎች የተፈጠሩት ግኝቶች ለሃገራችን ዜጎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡

ለሃገራችን እድገትና ለድህነት ቅነሳ ዓላማም ከሌሎች ሃገራት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ልምድ በመቅሰም የሳይንስ፤ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ተቀርፆ በትግበራ ላይ እንደሚኝም ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም አብራርተዋል፡፡

የሁለተኛው የእድገትን ትራንስፎርሜሽን እቅዱ አካል የሆነውን ከግብርና መር ወደ ኢንደስትሪ መር ለማሸጋገር ለሚደረገው ጥረትም የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ ስለመሆኑ አያጠራጥርም ነው ያሉት፡:

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ አሁንም ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ላይ መድረስ እንደምትችል እንደ አክሱም፤ ገዳ ስርዓትና ሃረር ግንብ እና ላሊበላ ያሉ ቀደምት ታሪካዊ ስልጣኔዎች ማረጋገጫ ናቸው፡፡

ለተሸላሚዎቹ የተሰጠው ሽልማት የተሻለ ስራን ለመስራት የሚያነሳሳና መንግስትም ለዘርፉ የሚያደርገውን እገዛ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ደ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው አሁን ያለው ትውልድም በሳይንስና ቴክኖሎጂ የዳበረ እውቀት እንዲኖረውና ለሀገሪቱም የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ትኩረት ተሰጥቶ እይተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ልዩ ክህሎት ያላቸው ህጻናትንና ተማሪዎች ከመደበኛ የትምህርት ካሪኩለም ውጪ የልዩ ክህሎት ትምህርት እንዲያገኙ ለማድረግ ልዩ ትምህርት ቤት እየተገነባ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ከሁሉም የሃሀገሪቱ የተውጣጡ የማምረቻ ተቋማት፤ የምርምር ስራን የሰሩ ግለሰቦች፤ ከአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የተመረጡ መምህራንና ተማሪዎች ሽልማት የተበረከተላቸው ናቸው፡፡

በአጠቃላይም 145 ግለሰቦች ሽልማታቸውን ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ተረክበዋል፡፡ Read more http://gcao.gov.et