ታላቁ ሩጫ ማኅበራዊ ትስስር በመፍጠርና በአገር ገፅታ ግንባታ ጉልህ ሚና እያበረከተ ነው:: ህዳር 9/2010

አዲስ አበባ   ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከርና በአገር ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ኢዜአ ያነጋገርናቸው የሩጫው ተሳታፊዎች ተናገሩ።

 በየዓመቱ ኅዳር ላይ የሚካሄደውና በብዙዎች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዘንድሮ ለ17ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቁ የጎዳና ላይ ሩጫ ሲሆን የተሳታፊዎቹም ቁጥር ከዓመት ዓመት እየጨመረ ነው።

 በተለይ የሩጫውን ተሳታፊዎች የእርስ በእርስ ግንኙነት በማጠናከርና የአገሪቱን መልካም ገጽታ በመገንባት ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የገለጹት።

 የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ አየለ በበኩላቸው ውድድሩ የአንድነትና የአብሮነት ስሜት የሚፈጥር ከመሆኑ ባሻገር የስፖርት ቱሪዝምን በማስፋፋት በኩል ጉልህ ሚና አለው ይላሉ።

 በ2009 ዓ.ም በተካሄደው የታላቁ ሩጫ ውድድር 300 የውጭ አገር ዜጎች ተሳትፈዋል፤ ዘንድሮም 20 ከሚሆኑ አገራት 500 ሰዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

 ህዳር 17 ቀን 2010 ዓ.ም “100 ሚሊዮን ምክንያቶች ለሴት ልጆች በጋራ ለመሥራት” በሚል መሪ ሃሳብ በሚካሄደው ታላቁ ሩጫ 44 ሺህ ሰዎች ይሳተፋሉ።

 በዚህም በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች ዙሪያ ለሚሰሩ የበጎ አድራጎት ማኅበራት ድጋፍ የሚውል ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል።

 ባለፉት አምስት ዓመታት በተመሳሳይ መሪ ቃል በተካሄዱት ውድድሮች ከ9 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ 32 ድርጅቶችን መደገፍ እንደተቻለ ተነግሯል።

 ባለፈው ዓመት በተካሄደው 16ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 42 ሺህ ሰዎች ተሳትፈዋል። Read more http://www.ena.gov.et