
(ኤፍ ቢ ሲ) ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡ የተለያዩ ሸቀጦችን የያዙ ከ12 ሺህ በላይ ኮንቴነሮች ጂቡቲ ወደብ ላይ ተከማችተዋል።
በአስመጪነት የተሰማሩት ነጋዴዎች ከወር በፊት ከውጭ ለማስገባት ያዘዟቸውን ምርቶች የያዙ ኮንቴነሮች ጂቡቲ ወደብ ቢደርሱም እስካሁን እጃቸው አለመግባቱን ይናገራሉ።
ጉዳዩ የሚመለከተው የባህር ትራንዚትና ሎጂስቲክ አገልግሎት የስራ ሃላፊዎችን ቢጠይቁም ጠብቁ ከሚል ምላሽ ውጭ አለማግኘታቸውን ይናገራሉ።
ከዚህ ባለፈ ግን እቃቸው ቀናት ማስቆጠሩ ሳያንስ የባህር ትራንዚትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ለጅቡቲ መንግስት ሊከፍል የሚችለው የዲመሬጅ ክፍያ ተወራርዶ ወደ እነርሱ እንዳይመጣም ይሰጋሉ።
ጂቡቲ በስምንት ቀናት ውስጥ የኢትዮጵያ ገቢ እቃ ካልተነሳ ከስምንት ቀናት በኋላ በእያንዳንዱ ቀን እንደ ኮንቴነሩ ርዝማኔ እስከ 11 ዶላር ድረስ በቀን ለአንድ ኮንቴነር ታስከፍላለች።
የሚገባው አልያም የሚወጣው እቃ በትክክለኛው ሰዓትና ቦታ መድረስ ካልቻለ ትራንዚተሮችም ተቀጭ በመሆን የችግሩ ሰለባ ይሆናሉ፤ በተጨማሪም በማምረቻው ዘርፍ ላይም አሉታዊ ተፅእኖ እያሳረፈ ስለመሆኑ አስተያየት ሰጭዎች ይናገራሉ።
በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ የገቢ እቃዎችን በጊዜ ማንሳት ካለመቻል ጋር ተያይዞ፥ የዶላር የውጭ ምንዛሪ እየጨመረ ስለሚሄድ የእቃዎቹ ወደብ መከማቸት ሃገሪቱን ለተጨማሪ ወጪ ይዳርጋታል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በ2002 ዓ.ም ሰኔ ወር ላይ በፃፈው ደብዳቤ አስመጪዎች ለሚያስመጡት እቃ የባንክ ኤል ሲ ሲከፍቱ፥ በሁሉም የንግድ ባንኮች ለትራንዚት የሰባት በመቶ ቁጠባ በባህር ትራንዚትና ሎጂስቲክ አገልግሎት የውጭ ምንዛሪ የባንክ ሂሳብ ውስጥ ተቀማጭ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
ከዚህ ባለፈም የባህር ትራንዚትና ሎጂስቲክ አገልግሎትም የውጭ ምንዛሪ በሚያቀርብበት ጊዜ ከዚህ ሂሳብ ተቀናሽ እየሆነ እንዲፈፀምለት የሚል ትዕዛዝም አስተላልፏል።
ይህን መሰረት በማድረግም ድርጅቱ የወደብ ኪራይን ጨምሮ ለትራንዚትና የትራንስፖርት ሎጂስቲክ አገልግሎት ለሚሆኑ ወጪዎች የሚያውልበት አሰራር አለው።
የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ እንደሚሉት ግን ከግል የንግድ ባንኮች በስተቀር ይህን የውጭ ምንዛሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እየተገበረው አይደለም።
አብዛኛውና እስከ 100 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚደርሰው የውጭ ምንዛሪ ክምችት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደሚገኝ በመጥቀስ።
አሁን ላይም በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ጂቡቲ ወደብ ላይ የተከማቹ 12 ሺህ ኮንቴነሮችን ጉዳይ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት ቢደረግም እንዳልተቻለ ያነሳሉ።
ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክና ንግድ ባንክ ጋር በመሆን በጋራ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል እስከ 30 ሚሊየን ዶላር እንደሚለቀቅለት ቢነገረውም እስካሁን አልተፈጸመም ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው።
እስከ ታህሳስ ወር መጨረሻ የተጠቀሰው ገንዘብ ይለቀቃል ተብሎ እስካሁን ገቢ የተደረገው ግን 2 ሚሊየን ዶላር ብቻ መሆኑንም አስረድተዋል፤ ይህ መሆኑ ድርጅቱን ለእዳ እየዳረገው መሆኑን በማንሳት።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው ግን ለስራ የሚያስፈልገውን ያህል መጠን ንግድ ባንክ እየለቀቀ መሆኑን ይገልጻሉ፤ ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንጻርም እየመጠነ ይለቃል ነው ያሉት።
አስመጭዎች አሁንም እቃችንን እንፈልጋለን ቢሉም፥ በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስተያየቱን እንዲሰጥ የተደረገው ጥረት ግን አልተሳካም።