የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ ማዕከላዊ ኮሚቴ በድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የእርምት እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።
በዚህ መሰረት የድርጅቱ ሊቀ መንበር አቶ አባይ ወልዱ ከድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ አባልነታቸው ተነስተው በድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንዲያገለግሉ ወስኗል።
በተጨማሪም የድርጅቱ የስራ አስፈጻሚ አባል አቶ በየነ ምክሩም ወደ ድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ዝቅ ብለው እንዲሰሩ መወሰኑን ድርጅቱ በመግለጫ አስታውቋል።
ከዚህ ባለፈም የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ወይዘሮ አዜብ መስፍንን ከስራ አስፈጻሚ አባልነታቸው እና ማዕከላዊ ኮሚቴው ታግደው እንዲቆዩ መወሰኑንም ገልጿል።
ድርጅቱ ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች ሁለት የስራ አስፈጻሚ አባላትን ማስጠንቀቂያ የሰጠ ሲሆን፥ ማዕከላዊ ኮሚቴው እያደረገ ያለውን ሂስና ግለ ሂስም እንደቀጠለ ነው።
ማዕከላዊ ኮሚቴው ይህን ያደረገው በድርጅቱ አመራር ዘንድ ከመድረካዊ ተልዕኮ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የታዩ ድክመቶችን ገምግሞ ለማረም መሆኑም ተገልጿል።
የሁሉንም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ሂስና ግለ ሂስ ግምገማ በያዝነው ሳምንት እንደሚያጠቃልል ይጠበቃል።