አፍሪካ በፈረንጆች 2018 ዓመት ከአራት በመቶ በላይ እድገት ታስመዘግባለች-የአፍሪካ ልማት ባንክ::

http://www.ethiopia.gov.et/-/-2018-

አዲስ አበባ ጥር 20/2010 አፍሪካ በ2018 ዓመት ከአራት በመቶ በላይ እድገት እንደምታስመዘግብ የአፍሪካ ልማት ባንክ በትንበያው አስታውቋል።

እድገቱ በተጠናቀቀው 2017 ከነበረው 3 ነጥብ 6 በመቶ ዓመታዊ እድገት የ 0 ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ ይኖረዋል።ባንኩ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው 30ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ጎን ለጎን ትላንት የምጣኔ ኃብት ምሁራን፣የአፍሪካ ሕብረት ተወካዮችና የመንግስት ተወካዮች በተገኙበት የትንበያ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።

ሪፖርቱ የአፍሪካ አገራት አመታዊ ምርት (ጂ.ዲ.ፒ) ውጫዊ ጫናዎችን ተቋቁሞ በ2018 እና 2019 በአማካኝ በ4 ነጥብ 1 በመቶ እድገት እንደሚኖራቸው አስቀምጧል።በባንኩ ታሪክ ትንበያ ሲያቀርበ የመጀመሪያው ሲሆን የአፍሪካን ምጣኔ ሃብት ሽግግር ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት ከህብረቱ ጋር ትብብሩን ለማጠናከር ይረዳልም ተብሏል።

የባንኩ ዋና የምጣኔ ሃብት ባለሙያና አስተዳደርና እውቀት ስራ አስኪያጅ ሰለስቲን ሞንጋ እንገለጹት በሪፖርቱ ላይ ፖሊሲ አውጪዎች ለምክረ ሃሳብ በቂ ጊዜ እንዲኖራቸው በማሰብ በጥር ወር ቀድሞ ቀርቦላቸው ነበር።የአፍሪካ ህብረት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኮሚሽነር ፐሮፌሰር ቪክቶር ሃሪሰን በበኩላቸው የአፍሪካ አገራት ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እድገት በሪፖርቱ የተሰጠውን ምክረ ሃሳብ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል ሲሉ አስገንዝበዋል።

የአህጉሪቱ ምጣኔ ሃብት እድገት አሁንም ሁሉን አቀፍ አለመሆኑን ያነሱት ኮሚሽነሩ ሴቶችና ወጣቶች በስራ አጥነት ችግር እየተጎዱ መሆኑን ገልጸዋል።ፕሮፌሰር ሃሪሰን እንደሚሉት አባል አገራቱ የስራ ሁኔታን በማስተካከል የግሉ ዘርፍ በልማት ውስጥ እንዲሳተፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በኢትዮጵያ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ዶክተር አርከበ እቁባይ በበኩላቸው ባንኩ በዚህ ወቅት የትንበያ ሪፖርት ማቅረቡ ለአፍሪካ መሪዎችና ለምጣኔ ሃብት ሽግግር ጠቀሜታ እንዳለው እምነታቸውን ገልጸዋል።የአፍሪካ አገራት የአገር ውስጥ ሃብትን ጥቅም ላይ በማዋል፣ መሰረተ ልማትን በማሟላት እንዲሁም መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት ቀጣይነት ወዳለው እድገት መሄድ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

አገራቱ የስራ ፈጠራ ፖሊሲ ማዘጋጀት እንዳለባቸው የገለጹት ዶክተር አርከበ በቋሚ የስራ እድል ፈጠራና ችሎታ ማሳደግ እንዲሁም ጥራትና ብዛት ላይ ማተኮር እንደሚገባም ተናግረዋል።የአፍሪካ ምጣኔ ሃብት ትንበያ በአፍሪካ ልማት ባንክ በየአመቱ የሚወጣ ሲሆን በአህጉሪቱ 54 አገራት ትላልቅ የምጣኔ ሃብት ኢንዱስትሪዎች ላይ ግምገማ በማድረግ የአጭርና የመካከለኛ ጊዜ ትንበያ ይሰጣል። ተጨማሪ ለማንበብ www.ena.gov.et