በአፍሪካ መዋዕለ-ንዋይ የማፍሰስ ዕድሎችና ፈተናዎች

https://www.bbc.com/amharic/news-43207880

በመገናኛ ብዙሃን ብዙ ጊዜ ስለ አፍሪካ ሲዘገብ የሚነገረው ረሃብ፣ ጦርነትና እልቂት የሞላባት ክፍለ ዓለም መሆንዋ ብቻ ነው።

እውነቱ ግን በአሁኑ ወቅት አፍሪካ፤ በውጪ ለሚኖሩ የብዙ ባለሃብቶች ትልቅ ኢንቨስትመንት ማዕከል መሆኗ ነው።

ዶክተር ሓርነት በክረጽዮን አፍሪካውያኖች ይህን ዕድል በደንብ እንዲጠቀሙበት የሚያስችል ‘አፍሪካ ቢዝነስ ጃምፕስታርት’ የተሰኘ ፕሮጀክት በመንደፍና ተግባራዊ በማድረግ ብዙዎች ወደ አህጉሪቱ እንዲመጡ ለማድረግ ተግታ እየሰራች እንደሆነ ትገልፃለች።

“የአፍሪካ ቢዝነስ ጃምፕስታርት ዋና ዓላማ በተለይም በአሜሪካና አውሮፓ የሚኖሩ አፍሪካውያን በተለያዩ ዘርፎች በአህጉሪቱ እንዲሰማሩ ለማበረታታትና ስልጠና ለመስጠትም ነው” ትላለች ዶከተር ሃርነት።

ስልጠናዎቹና የንግድ ዕድሎቹ አፍሪካ ውስጥ ለሚኖሩም ጭምር ክፍት መሆኑን ገልጻለች።

በአሁኑ ወቅት ንግድና ኢንቨስትመንት በአፍሪካ እያደገ መሆኑን በመጠቆም፤ አፍሪካውያን ታዛቢ ብቻ ከመሆን አልፈው በተፈጠረው ዕድል ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ በር መከፈቱን ዶክተር ሓርነት በአፅንኦት ትናገራለች።

አፍሪካ ቢዝነስ ጃምፕስታርት የአፍሪካውያንን ዕውቀት በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለማሳደግ ዋነኛና መሰረታዊ ዓላማው አድርጎ በመስራት ላይ ይገኛል።

እስከ ዛሬ ይደረግ የነበረው የኤርትራዊያንና የኢትዮጵያዊያን ኢንቨስትመንት ተሞክሮንና ጥናትን መሠረት ያደረገ እንዳልነበረ ዶክተር ሃርነት ይገልፃሉ።

“ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያንን ስንመለከት በፊት የነበሩትን ሃበሾች ዱካ በመከተል በአንጎላ፣ በደቡብ ሱዳን ወይም በኡጋንዳ መነገድ ነው የሚወዱት።”

ሆኖም ግን እንደ አንጎላና ደቡብ ሱዳን ያሉት ሃገራት ውስጥ ንግድና የኢንቨስትመንት ዋስትና የሌለውና ለአደጋ የተጋለጠ ነው። በማለት ዶክተር ሓርነት በተነፃፃሪ ዋስትና ያላችው ሃገሮችን ጠቅሳለች።

“እንደታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ቦትስዋናና ጋናን የመሳሰሉ ሃገራት የተሻለ ዕድልና ዝቅተኛ ስጋት ያለባቸው ናችው። ስለዚህ አስፈላጊ ጥናት በማካሄድ ከአንጎላና ከደቡብ ሱዳን የተሻለ አማራጭ አለ።”

በኤርትራና በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በሚመለከት ደግሞ፤ በተለይ ኤርትራ ውስጥ ለንግድ የሚመች ሁኔታ የሌለ መሆኑን የምትገልፀው ሓርነት የንግድ ፈቃድም እንደማይሰጥ አመልክታለች።

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ውስጥም በቀላል መንገድ ንግድ መጀመር አይቻልም። ምክንያቱም የንግድ ፍቃድ በቀላሉ ስለማይገኝ። በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ለሌላቸው ሰዎች የሚታሰብ አይደለም። እንደ እርሻ፣ የውጭ ንግድና ማምረት በመሳሰሉ አንዳንድ ኢንዳስትሪዎች በኩል ግን ብዙ ዕድል እንዳለ ትናገራለች።

ላለፉት 4 ዓመታት አፍሪካ ቢዝነስ ጃምፕስታርት ብዙ ሰዎችን በአንድነት በማሰባሰብ ሩዋንዳ ውስጥ የጥናታዊ ጉዞ እንዲያደርጉና ሃገሪቱ ውስጥ ያሉትን ዕድሎች በቅርብ እንዲዳስሱ አድርጓል።

“ከእኔ ጋራ የተጓዙ ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያንን በጣም ነው የተገረሙት። ምክንያቱም ከዚህ በፊት የነበራቸው ተሞክሮ አንጎላ ወይም ደቡብ ሱዳን ብቻ በመሆኑ ነው።”

“በሩዋንዳ ንግድ መክፈት በጣም ቀላል ነው። በ24 ሰዓታት ውስጥ የንግድ ፍቃድ ያለችግር ማግኘት ይቻላል። ሰለዚህ ሩዋንዳ ለመላው አፍሪካ ምሳሌ መሆን ትችላለች።”

ዶክተር ሓረነት ጀርመን ተወልዳ ያደገች የሁለት ልጆች እናት ስትሆን በምግብ ዋስትናና የገጠር ዕድገት ዘርፍ ምሩቅ ነች።

ለ13 ዓመታት በተባበሩት መንግሥታትና የአውሮፓ ህብረት እንደዚሁም በኦክስፋም ውስጥ የበላይ አማካሪ በመሆን በታላቋ ብሪታንያ፣ በኤርትራ፣ በሱዳንና በጀርመን ሰርታለች።

አሁን ደግሞ የአፍሪካ ያልተነካ ሃብት ጥቅም ላይ ለማዋል በሚል ሃሳብ ነው ትኩረትዋን ወደ አፍሪካ ያደረገች።

Read more