ለ16ኛው ዘላቂ የልማት ግብ መሳካት የፖለቲካ ቁርጠኛነት መኖር ወሳኝ ነው::የካቲት 20/2010

http://www.ethiopia.gov.et/-/-16-20-2010

16ኛውን ዘላቂ የልማት ግብ ለማሳካት በግምገማ፣ ክትትልና ሪፖርት ተግባራት የፖለቲካ ቁርጠኛነት መኖር ወሳኝ መሆኑን በኢትዮጵያ የተመድ ተወካይ አሁና ኤዛንኮዋ ኦኖቺ ገለጹ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከኢትዮጵያ ፕላን ኮሚሽን ጋር በመሆን ለባለድርሻ አካላት ስለ ዘላቂ ልማት ግቦች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቷል።

በኢትዮጵያ የተመድ ተወካይ አሁና ኤዛንኮዋ ኦኖቺ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ዘላቂ የልማት ግቦችን ከብሔራዊ ፖሊሲዎች ጋር በማጣመር ለመተግበር እንዲሁም ትብብርና አካታችነትን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚቻለው ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሲኖር ነው።ከዘላቂ የልማት ግቦች አንዱ የሆነውን ‘ሰላም፣ ፍትህና ጠንካራ ተቋማት’ን በቅድሚያ ማረጋገጥ ካልተቻለ ቀሪዎቹን ግቦች ማሳካት እንደማይቻልም ገልፀዋል።እንደ ተወካይዋ ገለጻ ‘የሰላም፣ የፍትህና የጠንካራ ተቋማት’ መስፈንና መገንባት ለሌሎች የድህነት ቅነሳ፣ ጤናማ ህብረተሰብ የመፍጠር፣ የትምህርት ጥራት መጠበቅና የሌሎችም ግቦች መሰረት ነው።በመሆኑም ይህንን ግብ ችላ በማለት ሌሎቹን ግቦች ማሳካት እንደማይቻል ነው ተወካይዋ ያረጋገጡት።

የአገር ሰላም ባልተጠበቀበት፣ ፍትህ ለዜጎች ማረጋገጥ ባልተቻለበትና ግቦቹን ማሳካት የሚችሉ ጠንካራና የተሳሰሩ ተቋማት ባልተመሰረቱበት ሁኔታ በዘላቂ ልማት የተያዙ ሌሎች ግቦችን ለማሳካት ከባድ ይሆናልም ብለዋል። 

የፕላን ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጌታቸው አደም በበኩላቸው ኢትዮጵያ ፈጣንና ዘላቂነት ያለው ልማት ለማረጋገጥና በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ ለ’ሰላም፣ ፍትህና ጠንካራ ተቋማት’ መኖር ቅድሚያ መስጠትን ከግንዛቤ አስገብታ በመንቀሳቀስ ላይ ናት ብለዋል።መንግስት ለዚህ ምላሽ ለመስጠት፣ መልካም አስተዳደር ለማስፈንና የህዝቡን ተሳትፎ ለማረጋገጥ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ አካቶ ለማሳካት ጥረት እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። 

አገራዊ እቅዱን ከዓለም አቀፉ ግብ ጋር በማስተሳሰር ሂደት ፈቃደኝነትን ካሳዩና በኒውዮርክ የአገራዊ ምልከታ ሰነድ ካቀረቡ 44 አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ እንደሆነችም ጠቅሰዋል።በአብዛኞቹ አገራት በተለይ በአፍሪካ ዘላቂ የልማት ግቦችን ያለማስተሳሰርና ሚዛናዊ ትኩረት ያለመስጠት ችግሮች እንደሚታዩ የገለጹት ደግሞ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ የዘላቂ ልማት ግብ አስተባባሪ አሌክሳንድራ ካሳዛ ናቸው።

በመሆኑም በአህጉሪቷ ‘ሰላምና ፍትህ እንዲሁም ጠንካራ ተቋማትን’ መመስረትን ችላ ብለው ሌሎቹ ላይ ብቻ ጥረት ማድረጋቸው የሚፈለገው ውጤት እንዳይመጣ እንቅፋት ሆኗል ባይ ናቸው።ዘላቂ ልማት ለማምጣት ከተፈለገ በቅድሚያ የልማቱ ፈጻሚና ተጠቃሚ ዜጎች ሰላማቸው ሊረጋገጥና ፍትህም እንዲያገኙ መስራት የመጀመሪያውና ለሌሎቹ ግቦች ተደማሪ ኃይል ነው ብለዋል።

ይህን ለማድረግ ደግሞ ጠንካራ ተቋማትን መመስረት እንደሚያስፈልግ ነው ያስረዱት። የተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦች 17 ሲሆኑ፤ ከሚሊኒየም የልማት ግቦች ቀጥሎ አባል አገራት እ.አ.አ እስከ 2030 እንዲያሳኩ የተቀመጡ ግቦች ናቸው። 
 http://www.ena.gov.et