''የፅንስን ቆዳ ያቀላል'' የተባለው መድሃኒት አደገኛ ነው ተባለ

https://www.bbc.com/amharic/43222376

ጋና ውስጥ ያሉ እርጉዝ እናቶች በማህፀናቸው ያሚገኝ ፅንስ ቀይ የቆዳ ቀለም እንዲኖረው በሚል የሚወስዱት ኪኒን አደገኛ እንደሆነ ባለሙያዎች አስጠነቀቁ።

የህክምና ባለሙያዎች እንዳሉት ነፍሰጡር እናቶች የሚወሰዱት ህገ-ወጥ መድሃኒት በሚወለዱት ህፃናት ውስጣዊና ውጫዊ አካል ላይ ችግርን ሊያስከትል ይችላል።

የጋና ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን እንዳለው እነዚህን ኪኒኖች የፅንስን የቆዳ ቀለም ለማቅላት መጠቀም አደገኛ መሆኑን አመልክቷል።

ጨምሮም ”የፅንሰን የቆዳ ቀለም ሊያቀላ የሚችል ምንም አይነት መድሃኒት በባለስልጣኑ እውቅና እንዳላገኘ ህብረተሰቡ ማወቅ አለበት” ብሏል።

ባለስልጣኑ እንዳመለከተው በአየር ማረፊያዎች በኩል በተጓዦች ሻንጣ ውስጥ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚገባውን ይህን መድሃኒት የሚወስዱ ነፍሰጡሮች ቁጥር በአሁኑ ወቅት እየጨመረ ነው።

ምንም እንኳን ሁሉን አቀፍ መረጃ ባይሰበሰብም፤ በገበያ ውስጥ በተደረገ ቅኝት እና በባለድርሻ አካላት በኩል በተገኘ መረጃ እንደተመለከተው፤ በተለያዩ የኑሮ ሁኔታ ላይ በሚገኙ ሴቶች መድሃኒቱ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ለማወቅ እንደቻለ ባለስልጣኑ ገልጿል።

የፀጥታ ተቋማትና ፖሊስ ይህንን ህገ-ወጥ መድሃኒት ይዘው የሚገኙ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ ለማቅረብ በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ።

Read more