እነዚህ ሁሉ ድክመቶች ስላሉብን አንወርድም!!!

የአመራር ድክመት ያውም በከፍተኛና በሥራ አስፈጻሚ ደረጃ መኖሩን በሚታክት ዝርዝር ያዥጎደጎደው ኢህአዴግ እንደገመትነው የሚበላውን በልቶ በሥልጣን ለመቆየት የሀሳብ አንድነት ፈጥሮ መውጣቱን በዛሬው መግለጫው ገልጿል። መግለጫው ሥራ አስፈጻሚው “በመንስኤና መፍትሄዎቻቸው ላይ መክሮ የሃሳብ አንድነትና መተማመን ፈጥሯል፡፡” ካለ በኋላ “የተመዘገቡ ውጤቶችን አስጠብቆ ለማስቀጠል የሚያስችል ቁርጠኝነትና ጠንካራ መግባባትን አረጋግጦ ወጥቷል፡፡” ብሏል። “ሰፊና ዝርዝር የሁኔታዎች ግምገማ አካሂዷል” ካለው መግለጫ ቃል በቃል የተጠቀሱ ድክመቶችን ቁጥር ሰጥተን ብናቀናብራቸው እንዲህ እናገኛቸዋለን –

የተዘረዘሩ ድክመቶች

1. በከፍተኛው አመራር ደረጃ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ እጦት ስር እየሰደደ እንደመጣ አረጋግጧል፡፡
2. በከፍተኛ አመራር ደረጃ የተዛባ የስልጣን አተያይና አጠቃቀም ተከስቷል።
3. መርህ አልባ ግንኙትና አካሄድ ማስፈን የተለመደ ስልት ወደመሆን ተሸጋግሯል፡፡
4. በጠባብ ቡድናዊ ጥቅሞች ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ኢህአዴግና አባል ድርጀቶቹን ማዳከም አስከትሏል፡፡
5. የህግ የበላይነት የማስፈን ድክመት በሙስናም ሆነ በሌሎች ጥፋቶች ውስጥ የተዘፈቁ ግለሰቦችን በወቅቱ መጠየቅ ሳይቻል ቆይቷል፡፡
6. ዜገች በህገመንግስቱ ዋስትና ያገኙ መብቶቻቸውን የሚጥሱ ሰዎችን በህግ ተጠያቂ ማድረግ ሳይፈፀም ቆይቷል፡፡
7. የህዝብና የአገር ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተነደፉ ፕሮጄክቶት ዙሪያ የሚታዩ የአፈፅፀምና የስነምግባር ችግሮችን አስተማማኝና ውጤታማ በሆነ መንገድ የማረምና የማስተካከል ጉድለት ታይቷል፡፡
8. ፕሮጄክቶች፣ የጊዜ የዋጋ ንረትና የሃብት ብክነት የሚታይባቸው ሆነዋል፡፡
9. ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቱና የድርጅትና የመንግስት ከፍተኛ ሃላፊዎች በተናጠልና በጋራ፣ ስትራተጅያዊና ታክቲካዊ አመራር የመስጠት ሃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው የተፈጠረ ችግር ነው፡፡
10. ከፍተኛ አመራሩ ችግር አስቀድሞ የመለየት፣ ተንትኖ የማወቅ፣ የመፍቻ መንገዶች የመተለምና በዚሁ መሠረት የመፍታት ብቃቱ ወቅቱና መድረኩ ከሚጠይቀው ደረጃ ጋር አብሮ ባለማደጉ የተወሳሰበውን አገራዊ መድረክ በብቃት የመምራት ጉድለት እንደነበረበት የጋራ አቋም ተይዟል፡፡
11. ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው መላ የአገራችን ህዝቦች በከባድ ተጋድሎአቸው ያስመዘገቡዋቸውን ድሎች ጠብቆና አስፍቶ ለማስቀጠል አልቻለም፤
12. በድርጅታችን ውስጥም ሆነ በአገራችን ውስጥ የሚታዩ ልዩ ልዩ ችግሮችን በጊዜና በከፍተኛ የሃላፊነት መንፈስ ለመፍታት አልቻለም።
13. 14. 15…… እያለ ይቀጥላል……

ፌዝና ቧልት
1. ስርዓቱ ለበላይነትና የበታችነት የማይመች ሆኖ ተዋቅሯል፡፡ በተግባርም እኩልነት እንጂ የባላይነትም ሆነ የበታችነት የማይፈጠርበት ስርዓት ተገንብቷል፡፡ ለሩብ ምእተ አመት በእኩልነትና በሰላም የዘለቀው ስርዓታችን የዚህ ውጤት እንደሆነ ስራ አስፈፃሚያችን በድጋሚ አረጋግጧል፡፡ በመሆኑም በማንኛውም ሽፋን ይህንን የእኩልነት ስርዓት ለማዳከም የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት እንደሌለውና ሊመከት እንደሚገባው ወስኗል፡፡

ፍሬ ነገር
1. የዚህ ሁሉ ውርጅብኝ ሰለባ ለመሆን ከተዘጋጀው ኦህዴድ በህዝብ የተወደዱና እነሱም የተዋደዱ (ያልተገባ ጉድኝት ፈጥረዋል” የተባሉት ይባረራሉ። በመግለጫው እንደተጠቀሰው “ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በየትኛውም ክልል ሆነ ብሄራዋ ድርጅት የሚከሰቱ መርህ አልባ ጉድኝቶች በጥልቅ እየተፈተሹ ሊወገዱ እንደሚገባ ወስኗል፡፡” (መርህ አልባ ጉድኝቶች= ምሳሌ- ለማ እና አብይ ወይም እነ ለማ እና ገዱ አንዳርጋቸው ወይም ኦህዴድና ብአዴን ማለትም ይሆናል)
2. እያንዳንዱ ብሔራዊ ድርጅት በከፍተኛ አመራር ደረጃ የሚታይበትን ድክመት በጥልቀት ገምግሞ በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ የተመሰረተ የማስተካከያና የእርምት ርምጃ እንዲወስድ ወስኗል፡፡ (አንጋፋዎቹ እነ አባዱላ ኦህዴድን እነ በረከት ብአዴንን ይገመግማሉ ፣ እነ ገዱና ጓደኞቻቸው ያበቃላቸዋል)
3. “የሁከትና የግርግር መልእክት በህዝብ ሚዲያ የሚሰበክበትን እድል ለመዝጋት የሚያስችሉ የተቀናጁ እርምጃዎችን እንደሚወስድ በዚህ አጋጣሚ ይገልፃል፡፡ (ያልተከፈተው ሚዲያ በሌለበት ይዘጋል ማለት ነው )
4. ለተፈፀመው ስህተትና ለደረሰው ጉዳት ከፍተኛ አመራሩ ሃላፊነቱን እንደሚወስድ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ለደረሰው ጉዳት ሙሉ ሃላፊነቱን ከመውሰድ በተጨማሪ ለመላ የአገራችን ህዝቦችና የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎችን ልባዊ ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ (ይህ ማለት እንግዲህ ይቅርታ ብለናልና አትጨቅጭቁን ማለት ነው ወይም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ይቅርታ የጠየቀ መንግሥት ሲባል ይከርማል)
5. ይህ ሁኔታ እንዳይደገምም ኢህአዴግ እንዳለፉት አመታት ሁሉ በቁርጠኝነትና በፅናት እንደሚንቀሳቀስ ቃል ኪዳኑን ያድሳል፡፡ ለማናቸውም ፈተና ሳይንበረከክ ከድል ላይ ድል በማስመዝገብ የመጓዝ እንቁ ታሪክ ያለው ድርጅታችን ኢህአዴግ አሁን በአገራችን የሚታየውን ሁኔታ እንደሚያስተካከልና የድል ጉዞውን እንደሚያስቀጥልም ቃል ይገባል፡፡ (ቃል ኪዳኑን ያድሳል ማለት – “ተሐድሶ” ወይም ህዳሴ ከሚለው ዝነኛ ቃል ጋር የህዳሴውን ግድብ ለማጠናቀቅ ወደፊት እንደማለት ነው!)