ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስራ አስኪያጅ ሆነው ተሾሙ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ አድርጎ ሾሟል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስራ አስኪያጅ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞትን ተከትሎ የግድቡን ግንባታ ኢንጂነር ኤፍሬም ወ/ኪዳን ላለፉት ሁለት ወራት በጊዚያዊነት ሲመሩት ቆይተዋል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ዶ/ር አብርሃም በላይ ዛሬ ለፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ እና ምክትል ሥራ አስኪያጆች ሹመት ሰጥተዋል፡፡

በዚህም መሰረት ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ሥራ አስኪያጅ፣ ኢንጂነር ኤፍሬም ወልደኪዳንና አቶ ፍቃዱ ከበደ ደግሞ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሥራውን እንዲመሩ መመደባቸውን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የውጭ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ለኢዜአ አስታውቋል፡፡

በራሳችን ሃገራዊ አቅም ያጋመስነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ለስኬት እንዲበቃ መላው ህዝብ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ (ENA)