ኦነግ ወታደሮቹን ትጥቅ እንዲያስፈታ ተጠየቀ

 

ዳዊት እንደሻው
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አሁንም አስታጥቆ እያንቀሳቀሰ ያለውን ጦሩን ትጥቅ እንዲያስፈታ፣ ወታደሮቹንም በአስቸኳይ መንግሥት ወዳዘጋጀው ካምፕ እንዲያስገባ ተጠየቀ፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግሥት የገጠርና ፖለቲካ አደረጃጀት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ፣ በግል የማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ እንዳሠፈሩት ግንባሩ ከዚህ ቀደም የተደረሰውን ስምምነት አክብሮ መንቀሳቀስ አለበት፡፡

አቶ አዲሱ ግንባሩ በአፋጣኝ ወደ ተግባር እንዲገባ ጠይቀው፣ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች በጊዜ መጨረስ ያለባቸውን ጉዳይ ባለመጨረሳቸውና ባለመደማመጣቸው፣ ክፍተትና ስህተት በመፍጠር ሕዝቦች እንዲሞቱና እንዲፈናቀሉ ማድረግ የለባቸውም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ለዚህም በኦነግ ስም ታጥቀው በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱትን በትዕግሥትና በብስለት እያየን ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የኦነግ አመራር የሆኑት አቶ ቶሌራ አደባ በበኩላቸው፣ አሁንም ትጥቃቸውን ያልፈቱ የኦነግ ወታደሮች እንዳሉ አምነዋል፡፡

‹‹በሰሜን፣ በምሥራቅ፣ በመካከለኛውና በደቡባዊ የኦሮሚያ ግዛቶች የታጠቁ የእኛ ወታደሮች አሁንም ድረስ አሉ፤›› ሲሉ አቶ ቶሌራ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹ከመጀመርያው ስምምነት ስናደርግ በሰላማዊ መንገድ ለመታገልና የትጥቅ ትግሉን ለማቆም ነው፤›› ያሉት አቶ ቶሌራ፣ ‹‹ወታደሮቻችንን ትጥቅ ለማስፈታት ከመንግሥት ጋር አሁንም እየሠራን ነው፤›› ብለዋል፡፡ (Reporter)