የጥምር ዜግነት ጥያቄ እና ዳያስፖራው በኢትዮጵያ

አዲስ አበባ፦ የኢፌዴሪ ህገ መንግ ሥት አንቀጽ 38 የመምረጥና የመመረጥ መብት ያለው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ብቻ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ የኢትዮጵያ የዜግነት አዋጅ ቁጥር 378/1996 ዓ.ም. አንቀጽ 4 ንኡስ አንቀጽ 7 አንድ ሰው የኢትዮጵያ ዜግነት በህግ ለማግኘት ‹‹የቀድሞ ዜግነቱን የተወ መሆኑን ወይም የኢትዮጵያን ዜግነት ቢያገኝ የቀድሞ ዜግነቱን ለመተው የሚችል መሆኑን ወይም ዜግነት የሌለው መሆኑን ማስረዳት መቻል አለበት ይላል፡፡

ይህ አዋጅ በኢትዮጵያ ጥምር ዜግነትን የሚከለክል ቢሆንም ሊፈቀድ እንደሚገባ ግን ፖለቲከኞች ይጠይቃሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህም በውጭ አገር ይኖሩ የነበሩ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ አገር ውስጥ ገብተው ሰላማዊ ትግል እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የአብዛኛዎቹ ፓርቲዎች መሪዎች ደግሞ የውጭ አገር ዜግነት ያገኙ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር አቶ ስለሺ ጥላሁን፣ መንግሥት ጥሪ ሲያደርግ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ጥምር ዜግነትን መፍቀድ ይኖርበታል ይላሉ፡፡

ሌላው በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ 11 የሚሆኑ የአፍሪካ አገሮች ጥምር ዜግነት ፈቅደዋል፡፡ ለምሳሌ ግብጽ ለዳያስፖራው ብቻ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዘጋጅታለች፡፡ ብዙም የመሰደድ ችግር የሌለባቸው የአፍሪካ አገሮች ጥምር ዜግነት ከፈቀዱ ለምን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿ በገፍ የተሰደዱባት ኢትዮጵያስ ለምን ጥምር ዜግነትን አትፈቅድም ሲሉ ይጠይቃሉ? ሌሎች አገሮች የጥምር ዜግነትን መብት ሲፈቅዱ ዳያስፖራው በባለቤትነት መንፈስ አገሩን ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንዲጫወት ነው የሚሉት አቶ ስለሺ ምክንያቱም ዳያስፖራው ለድጋፍና ለኢንቨስትመንት እየተፈለገ በፖለቲካው ደግሞ አትሳተፍም ሊባል አይገባም፡፡

የፖለቲካ ድርጅቶች አባላትንና አመራሮች ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ዳያስፖራው የጥምር ዜግነት ባለቤት ማድረግ ብዙ ጥቅም አለው፡፡ ጥምር ዜግነት የፈቀዱ አገራት በሁሉም ረገድ ተጠቃሚ ሆነዋልም ሲሉ ያክላሉ፡፡ ፓስፖርታችሁን ቀዳችሁ ብትመጡ ምንድነው ችግሩ ብለናቸው ሲመልሱም፣ በአገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች ግጭቶች ይታያሉ፡፡ ለውጡም እንዲቀለበስ የሚፈልጉ ቡድኖች አሉ፡፡ አገሪቱ ወዴት አቅጣጫ እንደምትሄድ ገና አልታወቀም፡ ፡ ቀዳችሁ ኑ የሚባለው ነገር ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ምክንያቱም ዳያስፖራው ዜግነት በአገኘበት አገር ኢንቨስትመንትና ቤተሰብ አለው ሲሉ አውስተዋል፡፡

አቶ ኤፍሬም ማዴቦ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ቃል አቀባይ ‹‹የውጭ አገር ዜግነት ያለው ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቶ በፓርቲዎች መሳተፍ ይችላል፡፡ ነገር ግን መምረጥና መመረጥ እንደማይችል በህገ መንግሥቱ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ የውጭ አገር ዜግነት ያለው ሰው ጥምር ዜግነት ተፈቅዶለት መምረጥና መመረጥ ከቻለ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገብቶ የአገር መሪ መሆንን ጨምሮ ከፍተኛ ሥልጣን ሊያገኝ ይችላል፡፡ ምክር ቤት ተመርጦ የሚገባ ሰው ሁሉ ትልልቅ አገራዊ ውሳኔዎች ላይ ይወስናል፤ ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆነ ደግሞ በሌሎችም ውሳኔዎች ላይ ተጽእኖ ያደርጋል፡፡

ይህ ሰው ሙሉ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ከሌለው በአገር ደህንነት ላይ አደጋ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር እኔ በግሌ ዜግነቱን እስካልለወጠ ድረስ መምረጥና መመረጥም የለበትም ብዬ አምናለሁ፡፡ምክንያቱም ትልልቅ አገራዊ ውሳኔዎችን የሚወስን ሰው ኢትዮጵያዊ ብቻ መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ ››፡፡ ለምሳሌ‹‹ እኔ በዜግነት አሜሪካዊ ነኝ፡፡ እኔ ከአሜሪካ ጋር ላለመተባበሬ ኢትዮጵያ ምን ዋስትና አላት? በአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ቻይናውያን እንኳ ስንት የአሜሪካን ምስጢር አሳልፈው ለቻይና እየሰጡ አሜሪካውያንን ችግር ውስጥ ጥለዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች የአሜሪካ ዜጋ ሆነው ነው የአሜሪካን ምስጢር አሳልፈው የሚሰጡት፡፡

አገራችን የሚመሩና ትልልቅ ውሳኔ የሚሰጡ ሰዎች ከውጭ ተጽእኖ የጸዱ መሆን አለባቸው፡ ፡ በኢትዮጵያ ጥምር ዜግነት ቢፈቀድ እንኳን የሚከለከሉ መብቶች መኖር አለባቸው፡፡ ሁለት አገር ዜግነት ያለው ሰው በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ የመወሰን መብት ሊሰጠው አይገባም›› ሲሉ ሞግተዋል፡፡ የኦሮሞ ብሄራዊ ፓርቲ የድርጅትና የፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ተማም ባቲ፣ ጥምር ዜግነት የአገርን ደህንነት ስጋት ላይ ይጥላል የሚለውን የአቶ ኤፍሬም ሀሳብን አይቀበሉትም፡፡ ጥምር ዜግነት ቢፈቀድ አገሪቱን ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም፡፡ ለፖለቲከኞች የጥምር ዜግነት መፍቀድ የአገሪቱን ደህንነት ስጋት ላይ ይጥላል የሚለው ሀሳብም ውሃ አይቋጥርም፡፡ ምክንያቱም ሰው የተወለደበትና እትብቱ የተቀበረበትን አገር ጥቅም ለሌላው አገር አሳልፎ ይሰጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ስጋት ካለ እንኳ በፖለቲካ ለሚሳተፉ ሰዎች ጥምር ዜግነቱ ሲሰጥ በስምምነትና በውይይት ገደቦችን ማስቀመጥ ይቻላል እንጂ በደፈናው ጥምር ዜግነትን መከልከል ተገቢ አይደለም ባይ ናቸው፡፡

አቶ ተማም ጥምር ዜግነት የሚያገኙ ሰዎች በፖለቲካው መስክ የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብት ሊያገኙ አይገባም የሚለውን የአቶ ኤፍሬም ሀሳብ አይቀበሉትም፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ አንድ የውጭ አገር ዜግነት ያለው ሰው በአገሩ ፖለቲካ ለመሳተፍ ጥረት የሚያደርገው የዚህ አገር ጉዳይ ያገባኛል ብሎ ነው፡፡ ዕድሉ ቢፈቀድለት በሙሉ ልብ አገሩን ያገለግላል፡፡ ምክንያቱም የሌላ አገር ዜጋ የሆነው አገሩን ጠልቶ ሳይሆን ለደህንነቱ፣ ለቤተሰቡና ለሀብት ሲል ነው በማለት ይሞግታሉ፡፡ ዳያስፖራ በኢትዮጵያ ስለመወለዱ መረጃ ካለው የጥምር ዜግነት ቢፈቀድለት በሙሉ ልብ በአገሩ ጉዳይ መሳተፍ ይችላል፡፡ በተለያዩ አገራትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያኖች አሉ፡ ስለሆነም ዳያስፖራዎች የጥምር ዜግነት ቢሰጣቸው ባላቸው ሙሉ አቅም በአገራቸው ጉዳይ ላይ በፖለቲካው በኢኮኖሚውና በማህበራዊ የመሳተፍ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡

የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ፓስፖር ታቸውን ቀዳችሁ ቢመጡ መምረጥም መመረጥም ይችላሉ የሚል ሀሳብ ይነሳልና በዚህ ዙሪያ ምን ይላሉ ስንል ለአቶ ተማም ያቀረብነውን ጥያቄ ሲመልሱም እንደ ግለሰብ በዚህ ሀሳብ አልስማማም፡፡ ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ከውጭ የመጡ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ናቸው፡፡ ይህ ሀሳብ የሚነሳው እነዚህ መሪዎች የውጭ ዜግነታቸውን በመተውና ባለመተው ተቸግረው ከፖለቲካው እንዲገለሉ ለማድረግ ሊሆን ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

(አዲስ ዘመን- ቅዳሜ- የካቲት 30/2011 በጌትነት ምህረቴ)