የመሬት ይዞታ አማራጮች በኢትዮጵያ

ቀደም ሲልም ሆነ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የመሬት ነገር አከራካሪና አነታራኪ ጉዳይ ነው። ከ1966 ዓ.ም በፊት የነበረው የመሬት ይዞታ በተለይ ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ውጭ በነበሩት ሁሉም አካባቢዎች የራሱ ሆነ ባሕሪይ የነበረው ሲሆን “የርስት፤ የጉልት” ግንኙነትን ያማከለ ነበር። በዚህም በንጉሱ ዘመን የነበረው የመሬት ይዞታ ብዙሀኑን አርሶ አደር የሚያገልል፤ የባለቤትነትም ሆነ የመጠቀም መብት ዋስትና የማይሰጥ እና በ“ጭሰኝነት” እንዲያድር የሚያስገድደው ነበር።

የ1966ቱን አብዮት ተከትሎ የመጣው ለውጥ ቀደም ሲል የነበረውን የርስት ጉልት ግንኙነት በመሻር በ“መሬት ለአራሹ አዋጅ” አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። በጊዜው ወደ ሥልጣን የመጣው የደርግ ሥርዓት መሬትን የሕዝብ ኃብት ለማድረግ በሚል አዋጅ ቁጥር 31/67 ታወጀ። አዋጁም መሬት አይሸጥም አይለወጥም የሚለውን ጥብቅ የሆነና የመሬት ጉዳይን ከሌሎች ንብረቶች የሚለየውን ገደብ ይዞ ብቅ እንዳለ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በ1987 የጸደቀው የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥትም “የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው ሲል ያስቀምጣል። መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው።” (አንቀጽ 40(3)) ይህ የሕገ መንግሥት ድንጋጌ የገጠር መሬት በእጁ ያለ ባለይዞታ መሬቱን መሸጥም ሆነ መለወጥ እንደማይችል በግልጽ አስፍሯል።

ሆኖም፤ የመሬት የባለቤትነት ጉዳይ አሁንም እንዳከራከረ ነው። ገሚሱ መሬት መሸጥና መለወጥ አለበት ሲል፤ ከፊሉ ደግሞ መሸጥ የለበትም፤ መሬት የህዝብና የመንግስት ሀብት ብቻ ነው መሆን ያለበት ሲል ይደመጣል።

መሬት እንዲሸጥና እንዲለወጥ መፈቀድ የለበትም የሚሉ ወገኖች ሁለት የመከራከሪያ ሀሳብ ያነሳሉ። አንደኛው መሬት ይሸጥ ይለወጥ ተብሎ ቢፈቀድ አርሶ አደሩ መሬቱን ሸጦ ከተማ ይሰደዳል፤ የሚል ስጋት ያስቀምጣሉ። ይህም ፍልሰትን የሚያባብስና የስራ አጥን ቁጥር የሚጨመር ይሆናል ሲሉ ይሞግታሉ።

ሌላኛው መከራከሪ ሀሳባቸው ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊና መሰረተ ልማት ባልተስፋፋባቸው አካባቢዎች መሬት የግለሰቦች ቢሆን መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት ግለሰቦች ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚጠይቁ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅና ስራውን እንዲጓተት ያደርጋል ባይ ናቸው።

መሬት ይሸጥ ይለወጥ ተብሎ ቢፈቀድ አርሶ አደሩ መሬቱን ሸጦ ከተማ ይገባል የሚለውን የስጋት ሀሳብ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ከፍተኛ ባለሙያ ዶክተር ሰይድ ኑሩ ይተቹታል። ግብርና እንደ ሌሎች መስኮች ሁሉ ጥረትና ክህሎት ይጠይቃል። ስለዚህ በግብርና ያልተሳካለት ሰው መሬትን ሽጦ ወደ ከተማ መሄዱ ስለማይቀር አማራጭ ስራ እንዲያገኙ ማድረግ እንጂ መሬት ባለቤትነቱን መንፈግ ተገቢ አይደለም ይላሉ።

ለምሳሌ ያህል በኢትዮጵያ ብዛት ያላቸው ገበሬዎች ያላቸውን መሬት በግብርና ሙያ የተሳካላቸው ገበሬዎች በህገ ወጥ መልኩ ሸጠው ከተማ ይገባሉ። ይህ ነባራዊ ሀቅ ነው። በከተማም አስር ቆርቆሮ ቤት ሁለትና ሶስት ሚሊዮን ብር ይሸጣል። ይህ ዋጋ የቤቱ ሳይሆን የመሬቱ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም። ስለዚህ መሬት መሸጥና መለወጥ እንዲቻል ህገ መንግስቱና የመሬት ፖሊሲው መሻሻል እንደሚኖርበት ጠቁመዋል።

በአሁኑ ጊዜ መሬት ያለው ሰው መሬቱ ባለበት ነው የሚጠቀምበት እንጂ መሬቱን አሳልፎ የመሸጥ መብቱ በህገ መንግስቱ አልተጠበቀለትም የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ምሁር ዶክተር አጥላው አለሙ፤ ይህ ማለት ገበሬውም ሆነ የከተማው ነዋሪ በመሬታቸው አስተማማኝ መብት የላቸውም።

ስለዚህ መሬቱን ለሌሎች አሳልፎ የመሸጥም ሆነ የመስጠት መብት ሊኖራቸው ይገባል የሚል አቋም አላቸው። ምክንያቱም አንድ ሰው የመሬት ባለቤት ካልሆነ መንግስት መሬቱን በፈለገ ጊዜ ሊነጥቀኝ ይችላል በሚል ስጋት በመሬቱ ላይ ዘላቂ ስራ መስራት አይችልም።

የመሬት ሀብቱን በትክክለኛው መንገድ ሊጠቀምበት አይችልም። በህገ መንግስቱ መሬት የመንግስትና የህዝብ ነው ስለሚል መሬት ያለውን ሰው መንግስትም ሆነ ግለሰቦች መሬትን የመሸጥና የመለወጥ መብት ስለሌለህ በሚል በዝቅተኛ ዋጋ ገንዘብ ከፍለው ሊያስለቅቁት ይችላሉ ።

ለምሳሌም በአዲስ አበባ ዙሪያ ይህ እውነታ የሚስተዋል መሆኑን አውስተዋል። መንግስት አነስተኛ ካሳ በመክፈል ብዙ ገበሬዎችን በማፈናቀሉ የፖለቲካ ቀውስ ማስከተሉን በአብነት አንስተዋል። በአንጻሩ መሬት እንዲሸጥና እንዲለወጥ መፍቀዱ የመሬት ባለቤቱ እንደ ማንኛውም ንብረቶቹ በገበያ ዋጋ ሽጦ ይጠቀምበታል። የመሬት ይዞታ ያለው ሰውም እውነተኛ የመሬቱ ባለቤት ይሆናል።

ገበሬው በሌላ ሙያ ተሰማርቶ ህይወቱን እንዳይቀይር ያደርጋል። በግድ ከመሬቱ ጋር ተጣብቆ እንዲኖር ሳይሆን መሬቱን ሸጦ ከተማ ገብቶ በሌላ መስክ መስራት እንዲችል ዕድል ያመቻቻል።መሬቱን እንደ ማንኛውም ሀብት ሊጠቀምበት የሚችልበት ሁኔታ ይፈጥራል።

መሬት ካለው ተፈጥሮአዊ ባሕርይም ሆነ ግዙፍነት የተነሳ በአገራችን ፖለቲካል ኢኮኖሚ ማዕከል ሆኖ እስካሁን ዘልቋል። በተለይም አብዛኛው ሕዝብ በእርሻ እየተዳደረ ባለበት አገር የመሬት ጉዳይ የኢኮኖሚ መሣሪያ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ የሆነ ጠቀሜታ አለው።

‹‹መሬት መሸጥ መለወጥ የሚችል ሀብት መሆን አለበት›› የሚሉት ዶክተር አጥላው በአሁኑ ጊዜ ግን መሬትን የእኔ ነው የሚለው መንግስት ብቻ ነው። መሬት የህዝብና የመንግስት ነው የሚለውም ለራሱ ጥቅም እንጂ ለገበሬው አስቦ አይደለም። እስካሁን ስልጣን ላይ የወጡት የኢትዮጵያ መሪዎች ገበሬውን መሬቱን እወስድብሃለሁ፤ አለበለዚያ የምለውን ታደርጋለህ የሚል ስርዓት የሚከተሉ ነበሩ። ካድሬው የሚለውን ሀሳብ ያልተቀበለ ገበሬ ከመሬቱ ስለሚፈናቀል ይህ እንዳይከሰትበት ሰጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛ ለማድረግ ነው ብለዋል።

ይህም የሚያሳየው መንግስታት መሬትን እንደፖለቲካ መሳሪያ ይጠቀሙበት እንደነበር ነው። ነገር ግን፤ አንድ ሰው የመሬት ባለቤትነቱ ከተረጋገጠ በሹመኞች የፖለቲካ ጭቆና ስር አይወድቅም። ሌላው መሬትን መሸጥና መለወጥ ቢፈቀድ ሙስናን ያስቀራል። በመሬት አስተዳደር ላይ የሚታየውን አገልግሎት አሰጣጥ ችግር ያስወግዳል። ሆኖም፤ በአሁኑ ጊዜ መሬት የሚሰጠውና የሚነሳው መንግስት ስለሆነ ለሙስና የተጋለጠ ነው። አሁንም ቢሆን ሰዎች በህገ ወጥ መልኩ በገጠርም ሆነ በከተማ መሬት ይሸጣሉ። ህግ ወጥ አሰራሮችን ማስቀረት የሚቻለው ግን መሬት ባለቤትነቱ ሲረጋገጥለት ብቻ ነው።

መንግስት መሬት ይሸጥ ይለወጥ ቢባል መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት እቸገራለሁ የሚል ሀሳብ ይነሳል። በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ የተባሉት ዶክተር አጥላው፤ ለአገር ልማት ለሚውል መሬት መንግስት ተገቢውን ካሳ ሰጥቶ ማስነሳት ይችላል። የሚል አንቀጽ ማካተት ይቻላል። መሬት የግለሰቦች መሆኑን በማከበር ተገቢውን ካሳ እየሰጡ ማስነሳት ይቻላል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ መሬት ይዞታ ላይ ብዙ ጥናት ያደረጉት አቶ ደሳለኝ ራህመቶ በኢትዮጵያ የመሬት ይዞታ ተግዳሮት ገጥሞታል፤ ዛሬ ከፍተኛ የሚታረስ መሬት እጥረት በመኖሩ በርካታ የገጠር ወጣቶች መሬት የላቸውም። ወጣቶች ቤተሰቦቻቸውን ካላችሁ መሬት ላይ አካፍላችሁ ስጡን በሚልም መሬት በገጠር የፀብ ምንጭ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት በመጨመር ረገድ ተጨባጭ ለውጦች ቢኖሩም የምርት ዕድገቱ የመጣው ግብርናውን ዕድገት በዘላቂ ለማዘመን ታስቦ ሳይሆን ማዳበሪያ ከውጭ ገዝቶ በማሰራጨት በመሆኑ ‹‹የተውሶ ዕድገት ነው›› ሲሉ ገልጸውታል። የግብርናው ምርታማነት ዕድገት ቢያሳይም ዛሬም ምግብ አምራቹ የምግብ ዋስትናውን መረጋገጥ አልቻለም ያሉት ምሁሩ፤ በድርቅ የሚጠቃውና የምግብ ዋስትና ፕራግራም ተጠቃሚ የሆነውን አርሶ አደር ቁጥር ባለፉት አስር ዓመታት ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን አመልክተው ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ህዝቡን በማሳተፍ ህገ መንግስቱና የመሬት ይዞታን/ስሪትን ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል።

በአቶ ደሳለኝ ሀሳብ ስለመሬት ይዞታ ሲነሳ የመንግስት፤ የወልና የግል የሚሉ ሀሳቦች ይጠቀሳሉ። ይህም ማለት ሙሉ በሙሉ በመንግስት ይዞታና ቁጥጥር ስር ያሉ፤ የሕዝብ የጋራ መጠቀሚያዎችና መገልገያዎች እንዲሁም ከመኖሪያ ቤት ጀምሮ እስከ ኢንቨስትመንት የሚደርስ የግል ይዞታን ያጠቃልላል። ይህም ከግለሰብ ገበሬ ጀምሮ የከተማውንም ነዋሪ የሚጨምር፤ ባለሀብቱንና መንግስትንም በየደረጃውና በየመልኩ ተጠቃሚ የሚያደርግ፤ የመሬት ስሪት ነው።

የግል ባለቤትነት የመረጋገጡ የመሬት ስሪት ገበሬውም ከመሬቴ እነቀላለሁ የሚል ስጋት ይቀርለታል። የከተማ ኗሪውም የራሴ የሚለው ይዞታ ይኖረዋል። ባለሀብቱም ከመንግስትም ይሁን ከግለሰቦች መሬት በተመጣጣኝ ዋጋ በማግኘት ኢንቨስትመንቱን ሊያካሄድ ይችላል ባይ ናቸው። መንግስትም ቢሆን _ለተለያዩ የህዝብ አገልግሎቶችና መሰረተ ልማቶች ማስፋፊያ የተጠበቁና የሚታዩ ይዞታዎች ይኖሩታል። ህጉ መስተካከል ካለበትም እነዚህ ጉዳዮች ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሆን አለበት ባይ ናቸው።

የፋይናንስ ባለሙያ አቶ ዛፉ እየሱስ ወርቅ ዛፉ መሬት የህዝብና የመንግስት የሚለው ህግ መንግስት ሊሻሻል ይገባል የሚል እምነት አላቸው። ምክንያታቸውም መሬት የግለሰቦች ባለቤትነት ቢሆን ኢንቨስትመንትን ያበረታታል።

አዲስ ዘመን መጋቢት 25/2011

በጌትነት ምህረቴ