በአንድ ወር ውስጥ የተስተዋለው የዋጋ ጭማሪ

Dereje

በአንድ ወር ውስጥ የተስተዋለው የዋጋ ጭማሪ

በአዲስ አበባ – የመንግሥት የሆነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ May 24, 2019 (ግንቦት 16/2011) እንደዘገበው። ከጋዜጣው ዘገባ ተቀናብሮ የተዘጋጀው ሰንጠረዥ ይህን ይመስላል። የጋዜጣውን ዘገባ ከሥር ማንበብ ይቻላል።

ዓይነት ከአንድ ወር በፊት አሁን
አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት 12 ብር 27 ብር
አንድ ኪሎ ነጭ ሽንኩርት 50ብር 100 ብር
አንድ ኪሎ ምስር 60 ብር 80 ብር፣
ፓስታ 18 ብር 20 ብር፣
አንድ ኪሎ እሩዝ 18 ብር 28 ብር
አንድ ኪሎ መኮረኒ 24 ብር 23 ብር
አንድ ኪሎ ጥቁር ጤፍ 21 ብር 24 ብር፣
አንድ ኪሎ ሠርገኛ ጤፍ 23 ብር 25 ብር
አንድ ኪሎ ነጭ ጤፍ 25 ብር 29 ብር
አንድ ኩንታል ዱቄት ከሸማቾች 796 ብር ከ20 ሳንቲም ከዱቄት ፋብሪካው በቀጥታ 2 ሺ ብር
የዳቦ እርሾ 400 ብር 2 ሺ ብር፤
ፓውደር 350 ብር 1 ሺ ብር
300 ግራም ዳቦ 3 ብር ከ80 ሳንቲም 4 ብር ከ50 ሳንቲም፤
ዳቦ 1 ብር ከ30 ሳንቲም 2 ብር ከ50ሳንቲም
1 ኩንታል የከብቶች መኖ 600 ብር 860 ብር
ግማሽ ሊትር ወተት 390 ብር 460 ብር

 

ኑሮ ተወደደ – መፍትሄ ያሻዋል!

ሶሎሞን በየነ May 24, 2019130

ባለፈው ሳምንት ጠዋት ከሳሪስ ወደ ስቴዲየም በባቡር ታጭቀን በመጓዝ ላይ እያለን በወራጅና በተሳፋሪ ወደ ባቡሩ ለመግባትና ለመውጣት በሚደረገው ግጥሚያ መካከል የሰው ጩኸትና የህጻናቱ የሰቀቀን ለቅሶ ለሰማውና ላየው ይዘገንናል። ተሳፋሪን መጫን እና ማውረዱን ጨርሶ ጉዞ ሲጀምር በባቡሩ የተሳፈረው ሰው አንዳንዱ በሀሳብ ጭልጥ ብሏል አንዳንዱ ብቻውን እንደ እብድ ያወራል። ተዛዝሎ ከሚጓዘው ተሳፋሪ መካከል ትንሽ በእድሜያቸው ጠናያሉ አባት ደግሞ እኔን ተደግፈው ቆመዋል፡፡

ምን እርሳቸው ብቻ እኔም እርሳቸውን እርሳቸውም እኔን ተደግፈው እንጓዛለን። አዛውንቱ በዝምታ ተዛዝሎ መጓዙ ስለሰለቻቸው ሰማህ ልጄ አሉና ለማዳመጥ መስማማት አለመስማማቴን ሳያረጋግጡ ወጋቸውን ቀጠሉ። «በጃንሆይ ጊዜ ንጉሡ ግብር ሲጨምሩ መጀመሪያ ሰው ሁሉ ተንጫጫ። ወሬ አቀባያቸው ‘ማህበረሰቡ እየተንጫጫ ነው’ ብሎ ለንጉሡ ወሬ አደረሰላቸው። ንጉሡም ሰው ተንጫጫ አሉና ለሁለተኛ ጊዜ ግብር ጨመሩ። ሰውም እንደለመደው ተንጫጫ። አሁንም ንጉሡ ለሦስተኛ ጊዜ ግብሩን ከፍ አደረጉ። ህዝቡም ማጉረምረም የለ መንጫጫት የለ ዝም አለ።

ንጉሡ ሲያሰልሉ በህዝቡ መካከል የሚሰማ ወሬም ሆነ ጉርምርምታ እንደሌለና ፀጥታ እንደሰፈነ ሰሙ፡፡ ንጉሡ «አሁን ነው መፍራት» ብለው ግብሩ በአፋጣኝ እንዲቀንስ አደረጉ፡፡›› ብለው አጫወቱኝ፡፡ ቀጠል አድርገው ዕቃ ለመግዛት ወደ መርካቶ እያመሩ እንደሆነም ነገሩኝ። በሰበብ በአስባቡ አንዴ ጣራ ከነካ የማይወርደው የገበያ ጉዳይ እንዳማረራቸው እና በቅርብ በአንድ ወር ውስጥ ያስተዋሉትን የዋጋ ጭማሬ አስመልክቶ አጫወቱኝ። የዋጋ ጭማሪው እኚህን አባት ብቻ አልነበረም ያማረረው፤ ሳሪስ አትክልት ተራ ያገኝኋቸው የሁለት ልጆች እናትና የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑትን ወይዘሮ ማስተዋል ወንዴም በኑሮ አማርሯቸው ነበርና ያስተዋሉትን አጫወቱኝ።

እርሳቸውም ከቀናት በፊት አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት 12 ብር ገዝተው እንደነበር፤ አሁን ላይ 27 ብር እንደገዙ፤ ከቀናት በፊት በ50 ብር የገዙት አንድ ኪሎ ነጭ ሽንኩርት አሁን ላይ 100 ብር በመሆኑ በገበያው ዋጋ መናር እየተበሳጩ ገቢያቸው የፈለጉትን ለመግዛት እንዳላስቻላቸው ገለፁልኝ። ሳሪስ አካባቢ በሚገኝ አንድ መደብር ለልጆቻቸው ለምሳና ቁርስ የሚሆን ሸቀጥ ሲገዙ ያነጋገርኳቸው የመዲናዋ ነዋሪ ወይዘሮ ሶፊያ መሐመድ፤ ከሳምንት በፊት አንድ ኪሎ ምስር 60 ብር፣ ፓስታ 18 ብር፣ አንድ ኪሎ እሩዝ 18 ብር እንዲሁም አንድ ኪሎ መኮረኒ 24 ብር እንደገዙና አሁን ላይ አንድ ኪሎ ምስር 80 ብር፣ ፓስታ 20 ብር፣ አንድ ኪሎ መኮረኒ 28 ብር እንዲሁም አንድ ኪሎ እሩዝ 23 ብር መግዛታቸውን፣ ኑሮው እየተወደደ መሆኑን ነገሩኝ። አቶ ሀብታሙ ዘሩ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ሀና ማርያም አካባቢ ቤት ተከራይተው፣ ወፍጮ ቤት ከፍተው እህል በመሸጥና በመፍጨት ሥራ ላይ ተሰማርተዋል።

እህሉን በጅምላ ከሚያመጡበት ቦታ በከፍተኛ ዋጋ የጨመረ መሆኑን ገልፀው፤ ነጭ ጤፍ በጅምላ የሚያመጡበት ዋጋ በፊት በወፍጮ ቤቱ እየተሸጠበት ካለው ዋጋ ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ የማጓጓዣና ሌሎች ወጪዎች ተጨምሮ ምርቱን ለመሸጥ እጅግ መቸገራቸውን ተናግረዋል። ጤፍ በጅምላ ከሚያመጡበት ቦታ በመወደዱ ምክንያት በእጃቸው ያለውን ጤፍ የተወሰነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ እየሸጡ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሀብታሙ፤ በኪሎ 21 ብር የነበረውን ጥቁር ጤፍ 24 ብር፣ 23 ብር የነበረውን ሠርገኛ ጤፍ 25 ብር እንዲሁም 25 ብር የነበረውን ነጭ ጤፍ 29 ብር እየሸጡ እንደሆነ ገልፀዋል።

አቶ ከድር አወል በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ሀና ማርያም ቀለበት አካባቢ ማሂር የሚባል ዳቦ ቤት ከፍተው በመሥራት ላይ ይገኛሉ። በዳቦ ቤቱ የተደረገውን የዋጋ ጭማሬ አስመልክቶ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ያነጋገርናቸው ሲሆን፤ እርሳቸውም የዋጋ ማስተካከያ ያደረጉት የዱቄት ዋጋ በመወደዱ ምክንያትና ለዳቦ ግብዓት የሚሆኑ ቅመማ ቅምም ዋጋ መናር እንደሆነ ገልፀዋል። ቀደም ሲል ዱቄት በሸማቾች በኩል የሚያገኙበት መንገድ እደነበረ ገልፀው፤ አሁን ላይ በሸማቾች በኩል በበቂ ሁኔታ ባለመቀረቡ ከሸማቾች አንድ ኩንታል ዱቄት 796 ብር ከ20 ሳንቲም ይገዙ የነበረውን አሁን ላይ ወደ ገበያ ሳይገባ ከዱቄት ፋብሪካው በቀጥታ 2 ሺ ብር እንደሚገዙ ተናግረዋል።

እንዲሁም 400 ብር የነበረው የዳቦ እርሾ 2 ሺ ብር፤ 350 ብር የነበረው ፓውደር አሁን ላይ 1 ሺ ብር መድረሱ ለዋጋ ጭማሬው ምክንያት ሆኗል ብለዋል። በአጠቃላይ ዘይት፣ ስኳርና ሌሎች የዳቦ ቅመማ ቅመሞች ዋጋቸው በእጥፍ በመጨመሩ ሥራውን ትቶ ከመቀመጥ ትርፍ ባይኖረው እንኳን ሥራውን ላለማቋረጥ እየነገዱ መሆኑን ተናግረዋል። ባለሀብቱ ይህንን ሁሉ ወጭ ለመሸፈን የግድ የዋጋ ማስተካከያ ለማድረግ እንደተገደዱ ገልፀው፤ 300 ግራም ዳቦ 3 ብር ከ80 ሳንቲም ይሸጡ የነበረውን አሁን ላይ 4 ብር ከ50 ሳንቲም፤ 1 ብር ከ30 ሳንቲም ይሸጡ የነበረውን ዳቦ 2 ብር ከ50 ሳንቲም እየሸጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በቃሉ ሄኖክና ጓደኞቻቸው ህብረት ሥራ ማህበር የወተትና የወተት ተዋጽኦ አቀራቢ ኢንተርፕራይዝ ከግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ያደረገው የዋጋ ማስተካከያ ምክንያቱ ምን እንደሆነ የማህበሩ አባል የሆኑት አቶ በቃሉ በጋሻው እንደገለፁት፤ የእንስሳት መኖ መጨመሩ መሆኑን ተናግረዋል። እርሳቸው እንዳብራሩት፤ ከአሁን በፊት አንድ ኩንታል የከብቶች መኖ በ600 ብር እንደሚገዙ ጠቁመው፤ አሁን ላይ 860 ብር ገብቷል ብለዋል። በመሆኑም ሌላ አማራጭ ስላጡ የዋጋ ማስተካከያ ማድረጋቸውን ገልፀው፤ 390 ብር የነበረው ግማሽ ሊትር ወተት ከያዝነው ወር ጀምሮ ወደ 460 ብር ከፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙንኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ ይህ ወር በገባ ማግሥት የተከሰተውን የዋጋ ጭማሬ እንዳብራሩት፤ አንዳንዴ የዋጋ ንረት ከውጭ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የመጨመሩ ምክንያት ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ሊሆን እንደሚችል፤ ነገር ግን በያዝነው ወር ላይ የታየው የዋጋ ጭማሬ የህብረተሰቡን ኑሮ እያናጋ ያለው በአገር ውስጥ የሚመረቱ የግብርና ምርቶች ላይ በተከሰተው ጭማሪ መሆኑን፤ እነዚህን ምርቶች ለማምረት የውጭ ምንዛሬ የማይጠይቁና ሙሉ ለሙሉ ከሰው ጉልበት ጀምሮ በአገር ውስጥ ግብአት የሚመረቱ በመሆኑ የዋጋ ንረት ሊያጋጥም የሚችልበት ሁኔታ የለም ብለዋል።

አቶ ወንድሙ «የመጀመሪያው መንስኤ የግብይት ስርዓት ችግር ነው ። የግብይት ስርዓቱ በጣም የተንዛዛ ሲሆን፤ ደላሎች በአምራችና ምርቱን ገበያ ላይ በሚያቀረበው ነጋዴ መካከል በመሆን ከነጋዴው ጋር በመመሳጠር ዋጋ ይወስናሉ። በገበሬው ምርት ላይ ፈላጭ ቆራጭ ይሆናሉ። ምርቱ ገበያ ላይ ሳይገባ ደላላው በስልክ ብቻ በመጠቀም ምርቱ ከተመረተበት ቦታ ሳይነሳ የዋጋ ድርድር በማደረግ ዋጋ ይዋዋላሉ።

«ከዚህ ባለፈ በህገወጥ ደላሎች ተዋናይነት ምርት የማዞር፣ የማሸሽ፣ የማቆየት እንዲሁም ቀን ጠብቆ ዋጋ በመጨመር በህገወጥ መንገድ ሀብት ለማካበት የሚደረግ ሴራ ሲሆን፤ አሁን ላይ የተስተዋለው የዋጋ ጭማሬ በምርት እጥረትና በአሳማኝ ምክንያት የተከሰተ ሳይሆን በደላሎች የተቀነባበረ በሰው ሰራሽ መንገድ የተፈጠረ የዋጋ ንረት ነው ብለዋል። ዳይሬክተሩ የግብይት ስርዓቱ ህገወጥነት የሚሰፍንበትና በየጊዜው ዋጋው እየናረ የሚሄድበትን ምክንያት ሲገልፁ « ህብረተሰቡ ግብይቱን በደረሰኝ ስለማይፈፅምና ግብይቱ በእውቀት ሳይደገፍ በተለምዶ የሚከወን በመሆኑ ለህገወጥ ደላሎች ተጋላጭ በመሆን ሁሌም የዋጋ ንረት እንዲኖር ምክንያት ሆኗል» ብለዋል።

አቶ ወንድሙ ይህን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ምርቶችን የመሸጫ መደብር ያላቸውና ተደራጅተው የሚሰሩ ነጋዴዎች ከእነዚህ ህገወጥ ደላሎች ጋር መመሳጠር የለባቸውም። ችግሩ የሚፈጠር ከሆነ በቅርበት ያለው የወረዳው ንግድና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት ደንብ አስከባሪ ወ.ዘ.ተ…. የመሳሰሉት ባለድርሻ አካላት በቅርበት ህገወጥ ዳላሎችንና አሰራሮችን ስለሚያውቁ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ሰላማዊ የንግድ ሂደት እንዲኖር የማድረግ ግዴታ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።

እንዲሁም ሸማቹ ማንኛውንምን ምርት ሲሸምት ከሸመትበት አካል ህጋዊ ደረሰኝ መጠየቅ አለበት። ደረሰኝ ከወሰደ በኋላ ጤፍ 2ሺ400 ብር ገዝቶ ከሆነ በሳምንት ልዩነት 200 ብር ከጨመረ ህጋዊ ደረሰኙን በመያዝ የዋጋ ጭማሬው ህጋዊነው አይደለም የሚለውን ለማወቅ ያስችለዋል። በመሆኑም ደረሰኙ የዋጋ ጭማሬው ያለ አግባብ የተደረገ ከሆነ በህግ ለመጠየቅ የሚያስችል ሲሆን፤ መንግስትም እርምጃ ለመውሰድ እንደሚያስችለው ጠቁመዋል።

ከደላሎች ጋር ተመሳጥረው በተገኙ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ በተጠናከረ መልኩ እየተወሰደ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመው፤ አሁን ላይም ቁጥጥርና እርምጃው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። ነገርግን በቅርበት የንግድ መደብሩን፣ ሱቁን እና ህገወጥ ደላላውን የሚያውቁት በወረዳ ያሉ የሚመለከታቸው የመንግስት መዋቅር ኃላፊዎች መወጣት ይኖርባቸዋል። ስለዚህ ከታች ችግሩ ካልተፈታ ከላይ ምንም ማድረግ ስለማይቻል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ኃላፊነት ባለበት መዋቅር ሊወጣ እንደሚገባ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።

አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2011